Quantcast
Channel: የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views
Viewing all articles
Browse latest Browse all 266

እውነት ስትሰቀል

$
0
0

(የዴንቨር መድኃኔዓለም ካህናትና ምእመናንን ባሰብኩ ጊዜ ይህንን ጻፍኩ)

ሰሞኑን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዴንቨር ከተማ ተገኝተው የዴንቨር መድኃኔዓለምን በተመለከተ ‹ከእናት ቤተ ክርስቲያን ወጥቷል› ብለው መናገራቸውን ስሰማ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለምን በቅዱስ ያዕቆብ መንበር ሥር መሆን የለባትም /አለባተ በሚል ከ50 ዓመታት በፊት በፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግ አንድ ሕንዳዊ አባት የሰጡት ምስክርነት ትዝ ያለኝ፡፡ 
 
በሕንድ ፍርድ ቤት የሕንድን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለማየት ከ50 ዓመታት በፊት ክርክር በተደረገ ጊዜ የሶርያውን መንበር የተቀበሉ ምእመናን ከባድ ፈተና ላይ ወድቀው ነበር፡፡ በአንድ በኩል በሶርያ መንበር የነበሩ አበው ለሕንድ ቤተ ክርስቲያን ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው ምእመናኑ ይማረራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከመንበሩ መነጠሉ ጥንታዊውን መንገድና ሥርዓት አዛብቶ ለተኩላ ስለሚዳርግ ያስጨንቃቸዋል፡፡ 

በፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት አባ ያዕቆብ የተባሉ ሕንዳዊ መነኮስ ‹እኔ መንበረ ያዕቆብ ስል ስለ እምነቴና ስለ ሥርዓቴ እየተናገርኩ እንጂ በቦታው ዛሬ ስለተቀመጡት አባቶች አይደለም፡፡ እነርሱ እንደሰውነታቸው ይበረታሉ ወይም ይደክማሉ፤ ይሠራሉ ወይም ይሰንፋሉ፡፡ ያቺ የተቀደሰቺው የያዕቆብ መንበር ግን ምን ጊዜም ቅድስት ናት፡፡ እኔ ያቺን መንበር ሳስብ ለእምነታቸው የታገሉትን ቅዱሳን አበው፣ ለመንጎቻቸው የሞቱትን ሰማዕታት እረኞች፣ በአሕዛብ ተከብበው በየዘመናቱ የደረሰባቸውን መከራ አሳልፈው በእምነታቸው የጸኑትን ጠንካሮቹን አበው ነው የማስበው፡፡ መንበሪቱ ማንም ቢቀመጥባት የማትረክስ ናት፡፡ ወርቅ ላይ ምንም ዓይነት ጭቃ ቢቀመጥ የወርቁን ክብር አይቀንሰውም፡፡ እንዲያውም ወርቁ የጭቃውን ክብር ይጨምረዋል፡፡ ለእነዚያ አበው የተሰጠው ቃል ኪዳን እንዲሁ የሚጠፋ አይደለም፡፡ እኔ ከመንበረ ያዕቆብ አልለይም ስል ለዘመናት ከተከፈለው መሥዋዕትነት አልለይም፣ በሐዋርያዊት ትውፊት ከምትኖረው ቤተ ክርስቲያን አንድነት አልለይም፣ እነዚያ ብርቱዎች የታገሉለትን ዓላማ ለደካሞች ብዬ አላፈርስም ማለቴ ነው› ብለው ነበር ምስክርነታቸው የሰጡት፡፡ 
 
በዚህ ዘመን በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙ አበውና ምእመናንም ተመሳሳይ ፈተና ነው የሚገጥማቸው፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መሆን ማለት ድሎትና ምቾት አይደለም፡፡ የአባቶችን ጥበቃና እረኝነት ማግኘትም አይደለም፡፡ መከራ መቀበልና መሥዋዕትነት መክፈል እንጂ፡፡ ‹በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር መሆን› ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ያልገባው ኦርቶዶክሳዊ ፈተናው ከባድ ይሆንበታል፡፡ መንበሩን ከሰዎቹ፣ እምነቱን ከፖለቲከኞቹ፣ ሥርዓቱን ከዘረኞቹ መለየት ካልቻለ ፈተናውን አይቋቋመውም፡፡ ይሁዳን ብቻ የሚያይ ከሆነ ሐዋርያነትን ይጠላል፡፡
 
አባቶቻችን ‹እስክንድርያ እናታችን፣ ማርቆስ አባታችን› ብለው ለ1600 ዓመታት ሲኖሩ በመንበረ ማርቆስ የተቀመጡት አበው ሁሉም  አስደስተዋቸው፣ የእስክንድርያው ቤተ ክህነት ሥራ አርክቷቸው አልነበረም፡፡ ለመንጋው የማይራሩ፣ በሲሞናዊነት የዘቀጡ፣ ከግብጽ መሪዎች ጋር ተመሳጥረው እረኝነታቸውን ለፖለቲካ የሸጡ አበው ነበሩበት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት 111 ጳጳሳት ሁሉ ደጋጎች፣ ሊቃውንት፣ ብርቱዎችና መንጋውን በትጋት የሚጠብቁ አልነበሩም፡፡ ሙስሊሞች ጳጳሳት ሆነው መጥተው ያውቃሉ፡፡ የግብጽ መሪዎችን ፈቃድ ለመፈጸም መስጊድ የሠሩ ግብጻውያን ጳጳሳት ነበሩ፡፡ ምንም ያልተማሩና ከምእመናኑ በዕውቀት ያነሱ ጳጳሳት ተልከው ያውቃሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን አባቶቻችን መንበሩንና ርእሰ መንበሩን አክብረው ኖረዋል፡፡ ለምን?
 
አባቶቻችን ‹እስክንድርያ እናታችን› ሲሉ እስክንድርያ የምትወክለውን የአትናቴዎስና የቄርሎስ፣ የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስና የዲዮስቆሮስ እምነት ማለታቸው ነው፡፡ እስክንድርያ ሲሉ ‹ወልድ ዋሕድ› የሚለውን የማይናወጽ ትምህርተ ሃይማኖት ማለታቸው ነው፡፡ እስክንድርያ ሲሉ በኒቂያ፣ በቁስጥንጥንያና በኤፌሶን የተወሰነውን የተዋሕዶ ትምህርተ ሃይማኖት ያገኙባትን መንበር ማለታቸው ነው፡፡ ለእነርሱ ‹ማርቆስ አባታችን› ማለት ከማርቆስ ጀምሮ ሳይቋረጥ የኖረውን ሐዋርያዊ የክህነት ቅብብል ያገኙበትን ቅዱስ መንበር ነው፡፡ መንበሩን ለማጽናት ከአረማውያን፣ ከአርዮሳውያን፣ ከንስጥሮሳውያን፣ ከልዮናውያንና ከሙስሊሞች ጋር የተደረገውን መሥዋዕትነት ነው፡፡ 
 
እነርሱ ታማኝ ሆነው የኖሩት ለዚህ ጽኑዕ እምነትና ሐሳብ ነው፡፡ ለዚህም ነው በዘመናት መካከል ዓላማው ያልገባቸው ሰዎች ሲነሡና በመንበሩ ላይ ሲቀመጡ፣ ኃላፊነታቸውን ትተው የንጉሥ ፈቃድ ፈጻሚዎች ሲሆኑ፤ መንጋውን ረስተው ለግል ጥቅማቸው ሲያደሉ የአባቶቻችን ሐሳብ ያልተቀየረው፡፡ 
 
ዛሬም ‹እናት ቤተ ክርስቲያን› ስንል አቡነ ጳውሎስ ወይም አቡነ ማትያስ ማለታችን አይደለም፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ስል አቡነ ዳንኤል ወይም አቡነ አትናቴዎስ ማለታችን አይደለም፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ስንል ንቡረ እድ እንትና ወይም ሥራ አስኪያጅ እንቶኔ ማለታችን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉም በእርሷ ሥር ሆነው የሚሠሩ፡፡ አንዳንዶች የሚጠበቅባቸውን አንዳንዶችም የማይጠበቅባቸውን የሚያደርጉ ተላላኪዎቿ ናቸው፡፡ አንዳንዶች መጥተውላታል፣ አንዳንዶችም መጥተውባታል፡፡ አንዳንዶች ተነሥተውላታል፣ አንዳንዶችም ተነሥተውባታል፡፡ አንዳንዶች ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ ይጽፋሉ፤አንዳንዶችም በሞት መጽሐፍ ይመዘገባሉ፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ግን ከእነርሱ ብቻ ሳይሆን ከድምራቸውም በላይ ናት፡፡ እነርሱ ያልፋሉ፤ እርሷ ግን ሁሉን ታሳልፋለች፡፡ እነርሱ ይቀራሉ፤ እርሷ ግን ትሻገራለች፡፡ 
 
እናት ቤተ ክርስቲያን ስንል ዐርባ ሺ  አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፣ 400 ሺ ካህናትን፣ 1100 ገዳማትን፣ ሃምሳ ሚሊዮን ምእመናንን፣ ከሦስት ሺ ዓመታት በላይ የዘለቀውን ታሪክ የጠበቀች ብሔራዊት ቤትን፣ እልፍ ቅዱሳንን ወደ መንግሥተ ሰማያት ያሻገረች ሰማያዊት መሰላልን፣ ከ200ሺ በላይ የሚደርሱ መጻሕፍትን ለትውልድ ያቆየች መዝገብ ቤትን ማለታችን ነው፡፡ ዮዲትን ያለፈቺውን፣ ግራኝን የተሻገረቺውን፣ ደርቡሽ አቃጥሎ፣ ጣልያን መዝብሮ ድል ሊያደርጋት ያልቻለቺውን ቤተ ክርስቲያን ማለታችን  ነው፡፡ መንበሯ ከርእሰ መንበሯ በላይ ነው፡፡ ሲኖዶሷም ከአባላቷ በላይ ነው፡፡ ለእኛ መንበሯ የታሪኳ፣ የቀኖናዋ፣ የትምህርተ ሃይማኖቷ፣ የቅርሷ፣ የባሕሏ፣ የስብከተ ወንጌሏ፣ የፈተናዋ፣ የምእመናኗ፣ የአጥቢያዎቿ፣ የአህጉረ ስብከቶቿ፣ የገዳማቷ፣ የመናንያኗ የአንድነታቸው መገለጫ (ትእምርተ አሐተኒ)፣ አንዲት ጉባኤ የመሆናቸው አይከን ማለታችን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከባለ ሥልጣኖቿ ሁሉ በላይ ነው፡፡ እርሷ ‹መልዕልተ ኩሉ› ናትና፡፡
ባለ ሥልጣኖቿ የሚሠሩት ስሕተትና ጥፋት ያሳዝነናል፤ ግን ተሥፋ አያስቆርጠንም፣ ያስለቅሰናል፣ ግን ከመንገድ አያስቀረንም፡፡ ከጥፋታቸው እንጂ ከአንድነቷ አያስወጣንም፣ እንደ ሸረሪት ቤታችን ሲቃጠል ትተን የምንጠፋ ሞኞች አይደለንም፡፡ ልጆቿ ነንና መከራዋን አብረን እንሳተፋለን፤ እንደ ባዕድ ባወጣ ያውጣሽ አንላትም፡፡ ድግስ እንደተጠራ ሰው ሲስተካከል ጥሩን ብለን ትተን አንሄድም፤ እንዲስተካከል በኣት አጽንተን እንጋደላለን እንጂ፡፡  
 
የቤተ ክርስቲያን ልጅነትን ማንም እንኩ ብሎ የሚሰጠን፣ ወይም ማንም አትችሉም ብሎ የሚከለክለን አይደለም፡፡ በዐርባ በሰማንያ ያገኘነው፣ በእምነትና በምግባር ተግተን፣ በመዋቅርና በሥርዓት ኖረን ያጸናነው ጸጋችን ነው፡፡ እኛ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስንል አባ ጊዮርጊስ እንዳስተማረን መስቀላዊቷን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች ከፓትርያርክ እስከ ምእመን፣ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ፡፡ ከግራ ወደቀኝ ከአሶሳ እስከ ቶጎ ጫሌ፣ ከዛላ አምበሳ እስከ ሞያሌ ያለቺውን ቤተ ክርስቲያን፡፡ ከላይ እስከ ታች - ከዐጸደ ነፍስ እስከ ዐጸደ ሥጋ፣ ከግራ ወደ ቀኝ - ከቶኪዮ እስከ ሎስ አንጀለስ፣ ከሜልበርን እስከ ጃማይካ ያለቺውን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች ከአርእስተ አበው እስከ ዓለም መጨረሻ የሚነሡ ክርስቲያኖች፤ ከግራ ወደ ቀኝ - ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የተበተኑ የእግዚአብሔር ልጆች ያሉባትን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ 
 
የምንኖረው በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የምንሠራው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የምንሞተውም በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የምንታመነውም ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እንዳትገነጠል፣ እንዳትከፋፈል፣ የምንታገለው ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እኛ ሲኖዶስ ስንል አባቶቻችን የራሳችን ጳጳሳት እንዲኖሩን ያደረጉትን ተጋድሎ እናስባለን፡፡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ብለው፣ ክብራቸውንም ትተው የአንበሳ ደቦል፣ የዝሆን ግልገል፣ የወርቅ እንከብል ይዘው እስክንድርያ ድረስ ጳጳስ ለማምጣት የደከሙትን ድካም እናስባለን፡፡ አሁን ያሉት አባቶች ቢያቀሉትም ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን ለማግኘት፣ አዲስ አበባ ላይ መንበረ ፕትርክና ለመመሥረት ሺ ዓመታትን የፈጀ ተጋድሎ ተደርጓል፡፡ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አስጠብቆ፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን እረኞች እንዲያገኙ እየታገሉ ያለፉትን አበው እናስባለን፡፡ 
 
ቀራንዮ ላይ ዮሐንስን መስሎ የመቆምን ያህል ከባድ ነገር የለም፡፡ ባልንጀሮቹ በሙሉ ሄደዋል፡፡ የሚወደው መምህሩ ራቁቱን ተሰቅሏል፡፡ ሽፍቶችና አልፎ ሂያጆች ይዘብቱበታል፡፡ ቀያፋና ሐና ድል አደረግን ብለዋል፡፡ ያንን ጌታ፣ ያንን ራቁቱን የተሰቀለ ጌታ፣ ተጠማሁ የሚለ ጌታ፣ ልብሶቹን ዕጣ የሚጣጣሉበትን ጌታ፣ በደም አበላ የተዋጠውን ጌታ - ጌታ ነው ብሎ እንደማመንና፣ ባመኑትም እንደመጽናት ያለ ምን ከባድ ነገር አለ? ጌታን ዓይን ሲያበራ፣ ጎባጣ ሲያቀና፣ ኅብስት ሲያበረክት፣ ሙት ሲያስነሣ፣ ማዕበል ጸጥ ሲያደርግ ማመን ቀላል ነው፡፡ ጌታን ተሰቅሎ ማመን ግን ከባድ ነው፡፡ ያ ቀን እውነት የተሰቀለችበት ቀን ነውና፡፡
ይህ ዘመን እውነት የተሰቀለችበት ዘመን ነው፡፡ በእናት ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ አንዳንድ አባቶችና አገልጋዮች ራሳቸው አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን ሊያፈርሱ ሲሠሩ፤ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ከሚጋደሉት ይልቅ አፍራሾቹ የቤት ልጆች ሲሆኑ፣ ከአማኞቹ ይልቅ ከሐዲዎቹ፣ ከጽኑዐኑ ይልቅ መናፍቃኑ በር ሲከፈትላቸው፣ ከልጆቿ ይልቅ ጠላቶቿ ሲሾሙ ‹እናት ቤተ ክርስቲያን› ብሎ መጋደል በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ እንደተገኘው እንደ ዮሐንስ መሆን ነው፡፡ እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር መቆም፡፡ 
 
ዕለተ ዓርብ ያልፋል፡፡ የቀያፋ ድንፋታ፣ የሐናም ኩራት ያከትማል፡፡ የተቀበረው እውነት ይነሣል፡፡ የሄሮድስና የጲላጦስ ማኅተም ይፈታል፡፡ የሸሹ ሐዋርያት ይመለሳሉ፤ የካደው ጴጥሮስ ንስሐ ገብቶ ይመጣል፡፡ የሸጠው ይሁዳም ተቀስፎ ይሞታል፡፡ ያን ጊዜ በመስቀሉ ግርጌ እውነት ስትሰቀል ከእውነት ጋር የቆመው ዮሐንስ ‹ሞትን ከማይቀምሱት ወገን› ይሆናል፡፡ የዓርብን ግርግር፣ የቅዳሜን ጸጥታ በትእግሥትና በጽናት የሚያልፍ ዮሐንስ ከተገኘ - አላውቅም ካለው ከጴጥሮስ ጋር ሆኖ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ይጠራል፡፡ 
 
እስከዚያ ግን እውነት ትሰቀላለች፤ ልጆቿም ራሳቸው ለማዳንና መከራውን ላለመቀበል ሲሉ ትተዋት ይሄዳሉ፡፡ እውነት ያለብነ ትተው ገንዘብ ያለበትን ይመርጣሉ፤ ምቾት ያለበትን ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እንደ ዮሐንስ የሚጸና ብጹዕ ነው፡፡

Viewing all articles
Browse latest Browse all 266

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>