ገድሉ፣ የኢትዮጵያን የ16ኛውን ክፍለ ዘመን አስተዳደራዊ መልክአ ምድር(ጂኦግራፊ) ለመረዳት በጣም ይረዳል፡፡ የገድሉ ጠቀሜታ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጥናት ቀላል ያልሆነ አስተዋጽዖ ያደርጋል፡፡ ብዙ ምስቅልቅል የነበረበትን፣ ብዙ ጦርነቶችና ደም መፋሰሶች የታዩበትን ሰፊ የሕዝቦች እንቅስቃሴና መፈናቀል የተከሰተበትን የ16ኛውን ክፍለ ዘመን ለመረዳት የሚያደርገው አስተዋጽዖ ከፍ ያለ ነው፡፡
በዚህ ውስብስብና ትርምስ የበዛበት ዘመን ቢኖሩም፣ እኒህ አባት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ጊዜያቸውን በመጠቀም በጣም ጠቃሚ የሆኑ መጻሕፍትን ከዐረብኛ ወደ ግእዝ መልሰዋል፤ የታወቀውን ‹አንቀጽ አሚን› የተባለውን ወጥ የሆነ ድርስታቸውን ጽፈዋል፡፡ ጽሑፎቻቸው ለግእዝ ሥነ ጽሑፍ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ በዚያ ቀውጢ ዘመን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሊያነቡዋቸውና ሊነበቡላቸው የሚገቡ አያሌ ጽሑፎች ስለአቀረቡ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልሶ መጠናከር የላቀ እርዳታ አድርገዋል፡፡
ገድሉን ስናነብ እነዚህንና ሌሎች ቁም ነገሮችን እናገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ ገድሉ ተተርጉሞ ግእዝ ለማያውቀው አንባቢ ሳይደርስ እስካሁን ቆይቷል፡፡ ጠቃሚነቱን በመገንዘብ፣ ሪቺ የተባለ ኢትዮጵያን ያጠና የነበረ የኢጣልያን ሊቅ ወደ ጣልያንኛ ተርጉሞ በጣም የተስፋፉ፣ ብዙ መጻሕፍትን ያጣቀሱ የግርጌ ማስታወሻዎችን አክሎ አሳትሞ ነበር፤ ይህ ትርጉም ከነግርጌ ማስታወሻዎቹ እጅግ ጠቃሚ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን አንባቢዎች መካከል ጣልያንኛውን የሚያውቅ አንባቢ ይኖራል ብሎ መገመት ስለማይቻል፤ የሪቺ ሥራ ብዙም በትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ ምሁራንና ተማሪዎችም ሆነ፣ ከዚያ ውጭ ላሉ አንባቢዎች አገልግሏል ማለት አይቻልም፡፡
ይህ የአሁኑ የዲ/ን ዳንኤል ክብረት ሥራ የገድሉን ትርጉም እና ገድሉ ውስጥ ያሉትን ለአሁኑ ትውልድ ግልጽ የማይሆኑትን ሐሳቦችና የሰውም የሆኑ የቦታ ስሞች የሚያብራሩ የግርጌ ማስታወሻዎች የታከሉበት በጣም ጠቃሚ ሥራ ነው፤ በአቡነ ዕንባቆም ሕይወት ታሪክም ላይ እና በዘመኑ በነበረው ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ የተደረጉ ምርምሮችን በማካተት ይህ መጽሐፍ ተዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉ ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት፡- ሃይማኖታዊና ዓለማዊ፡፡ ዲ/ን ዳንኤል በዚህ በኩል የተሳካ ሥራ ሠርቷል፤ ምክንያቱም ያዘጋጀው መጽሐፍ ለመንፈሳዊ አገልግሎትም ሆነ ለማስተማርና ለምርምር ሊያገለግል ይችላል፡፡
ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ