Quantcast
Channel: የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views
Viewing all articles
Browse latest Browse all 266

ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ

$
0
0
ሠፈራችን አንድ ሠርግ ቤት ውስጥ ልጃገረዶቹ ተሰባስበው
‹ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ
ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ
ይጠቀለላል እንደ ሠርዶ
ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ›
እያሉ ያስነኩታል፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ እንዳቀነቀኑ እናትዬዋ ወገባቸውን እየሰበቁ ወጡና
‹‹አቁሙ፤ እርሱን ዘፈን አቁሙ›› አሉና ተቆጡ፡፡
‹‹ለምን እማማ?›› ልጃገረዶቹ ከዘፈን ትንፋሽ ባልወጣ ድምፃቸው ተንጫጩ፡፡
‹‹ምነው ሸዋ፤ የኔ ልጅ ከነ ፀጉሯ እንድትኖርልኝ እፈልጋለሁ ልጄ፤ ሐሳብ የለሽ ሁላ›› አሉ እማማ፡፡
‹‹ታድያ እኛ ዘፈንላት እንጂ ምን አረግናት›› ልጃገረዶቹ እየሳቁ ጠየቁ፡፡
‹‹እናንተ ምን ታደርጉ፡፡ ቴሌቭዥን አትከታተሉማ፤ ምን የዛሬ ልጆች ወይ ቃና ወይ ምርቃና ላይ ናችሁ፡፡››
‹‹ምን ተባለ ደግሞ እማማ፤ ተከለከለ እንዴ›› አለች አንዲት ወጣት አታሞውን እንደያዘች፡፡
‹‹ቻይናና ጃፓን ዶላር ሲያጡ የሴቶችን ፀጉር እንደሸጡ አልሰማችሁም›› እማማ በልጆቹ አለማሰብ ተናደዋል፡፡
‹‹ታድያ ቻይናና ጃፓን ቢሸጡ እኛ ምን አገባን፤ እንዝፈን ባካችሁ›› አለች ልጂቱ፡፡

‹‹ዛሬ ለጃፓንና ለቻይና የተባለውኮ ነገ ለኛም ይመጣል፡፡ ‹ድሮም ከቆሮንቶስ ተጀምሮ ነው እኛ ዘንድ የሚደርሰው› አሉ እትዬ ስንዱ›፡፡
‹‹በሞቴ እማማ ይህን ታሪክ ይንገሩን›› አሉ ወ/ሮ አያህሉሽ ሽንኩርት መላጡን ትተው፡፡ እማማም በዚያው ዘፈኑ እንዲረሳላቸው ፈለጉና ‹እይውልሽ መምሩ የቆሮንቶስ ሰዎች አመንዝሮች ናቸው፡፡ አመንዝራነት ጥሩ አይደለም፡፡ እያሉ ሕዝቡን ይወቅጡት ጀመር፡፡ ታድያ እትዬ ስንዱ መረራቸውና ‹አሁን እኛ አመንዝራ አይደለን ለምን ይወቅሱናል?› ብለው መምሩን መጠየቅ፡፡ መምሩም ደነገጡና ‹አይ እኔኮ የቆሮንቶስ ሰዎችን እንጂ እናንተን አላልኩም› ይሏቸዋል፡፡ እትዬ ስንዱም ‹ድሮም ከቆሮንቶስ ተጀምሮ ነው እኛ ዘንድ የሚደርሰው እንጂ ለኢትዮጵያ ብሎ ድሮስ ማን ጻፈ› አሉ አሉ፡፡››
ልጆቹም ወ/ሮ አያህሉሽም ሳቁ፡፡
‹‹ምናለ ታድያ ሴቶቹን ትተው እነዚህን ፀጉራቸውን እንደ ገመድ የሚያስረዝሙትን ወንዶች እያጨዱ አይሸጡልኝም ነበር›› አሉ ወ/ሮ አያህሉሽ፡፡
‹‹እርስዎ ደግሞ፤ የሴቶቹ እንጂ የወንዶቹ በዶላር ተሸጠ ማን አለ፡፡ የተባለውን ነው መስማት፡፡ መጀመሪያ የተባለውን በትክክል መስማት ነው፡፡ ቀጥሎ አስተካክሎ መተርጎም ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ አስተካክሎ መጠንቀቅ ነው፡፡ ዛሬ ቻይና ላይ ተደረገ ከተባለ ነገ እዚህ እኛ ቀበሌ አጀንዳ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከውስጥ የተገኘ ዕውቀት እንጂ ከውጭ የተገኘ ልምድ መች ይናቃል፡፡ ይኼ ሁሉ ባለ ሥልጣን ቻይና ጎብኝቶ ጎብኝቶ መዐት ሊያመጣብን ነው መሰል፡፡ ‹መላጣ፣ የሥላሴ ጦጣ፣ አይበላም ሰላጣ› እንዳልተባለ ሁሉ መላጣ የሚመሰገንበት ዘመን ሊመጣ እንዳይሆን፡፡››
‹‹አይ እማማ›› አሉ ወ/ሮ አያህሉሽ ሽንኩርቱን እየላጡ ‹‹መላጣማ ችግር ላይኮ ነው››
‹‹ምንድነው ደግሞ ችግሩ››
‹‹ዘንድሮኮ በከተማው ባዶ ቦታ እንዳይኖር ተብሏል፡፡ ወደፊትኮ ባዶ ቦታ ለማየት ገጠር መሄድ ይኖርብናል፡፡ በዚህ አያያዝ በከተማ ባዶ ቦታ ሲጠፋ ልጆቻችንን ስለ ባዶ ቦታ ማስተማር የምንችለው መላጣ ሰው እያሳየን ብቻ ነው፡፡›› ወይዘሮ አያህሉሽ ብቻቸውን ሳቁ፡፡ ልጃገረዶቹም አብረው ሳቁና ‹‹እና መላጣ የትምህርት መሣሪያ ሊሆን ነው›› ብለው ጨመሩበት፡፡
‹‹አያችሁ ልጆች፣ ለዚህ ነው ‹ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ› ብላችሁ መዝፈኑን ተውት ያልኳችሁ›› አሉ እማማ
‹‹ታድያ ምን ብለን እንዝፈን› ልጃገረዶቹ በቅሬታ ድምፀት ጠየቁ
‹‹እስከ መቼ ድረስ ፀጉር ተበጥሮ
መቀስ የት ይገኛል ቁርጥ ነው ዘንድሮ›› በሉታ፡፡
 

Viewing all articles
Browse latest Browse all 266

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>