Quantcast
Channel: የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views
Viewing all 266 articles
Browse latest View live

ለሊዮ ቶሎይስቶይ የተጻፈ ደብዳቤ (እውነተኛ የሰሙኑ ገጠመኝ)

$
0
0


አንድ ወዳጄ ከሳምንታት በፊት አንድ ቴአትር ይጽፍና በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት ቴአትር ቤቶች ወደ አንዱ ይሄዳል፡፡ ድርሰቱን ለግምገማ እንዲያስገባ ይነገረዋል፡፡ አስገባ፡፡ በቀደም ዕለት የግምገማውን ውጤት ለማየት ወደ ቤተ ተውኔቱ ያመራል፡፡ መዝገብ ቤቶቹም ‹የግምገማው ውጤት ደርሷል፡፡ መታወቂያዎትን አሳይተው ፈርመው መውሰድ ይችላሉ› ይሉታል፡፡ ከደረት ኪሱ መዥለጥ አድርጎ መታወቂያውን ሰጣቸው፡፡ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ መታወቂያውንና ደብዳቤውን አስተያየና ‹እርስዎ መውሰድ አይችሉም፤ መውሰድ የሚችለው ደራሲው ነው› ይሉታል፡፡ እርሱም ደረቱን ነፍቶ ‹የድርሰቱ ባለቤት እኔ ነኝና ልውሰድ› ይላል፡፡ መዝገብ ቤቶቹም ‹እዚህ ላይ የተጻፈው ግን የእርስዎ ስም ሳይሆን የደራሲው ስም ነው› ይሉታል፡፡ ግራ ገባው፡፡ እዚህ ቴአትር ቤት ይህንኑ ድርሰት ይዞ የመጣ ሌላ ደራሲ ይኖር ይሆን? ብሎ አሰበ፡፡ የትርጉም ሥራዎች አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች አንድን ሥራ ያውም በተመሳሳይ ጊዜ ተርጉመው ሊያቀርቡት ይችላሉ፡፡
‹የተጻፈውን ደብዳቤ ማየት እችላለሁ› ይላል ወዳጄ የተጻፈለትን ሰው ስም ለማየት ጓጉቶ፡፡
‹መውሰድ አይችሉም እንጂ ማየትስ ይችላሉ› አለው የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ፡፡
ወዳጄ ወደ ማኅደሩ አንገቱን ልኮ ሲመለከተው ግን ክው ብሎ ነበር የቀረው፡፡

የወዳጄ የቴአትር ደርሰት የዝነኛው ሩሲያዊ ደራሲ የሊዮ ቶሎይስቶይ ድርሰት ነው፡፡ ወዳጄ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ነው ያቀረበው፡፡ በድርሰቱ ጽሑፍ ላይ ‹ደራሲ ሊዮ ቶሎይስቶይ፣ ተርጓሚ እገሌ› ይላል፡፡ አስደናቂው የቴአትር ቤቱ ደብዳቤ  ‹ለአቶ ሊዮ ቶሎይስቶይ› ተብሎ ነው የተጻፈው፡፡ ለዚህ ነበር መዝገብ ቤቱ መስጠት የቸገረው፡፡ ወዳጄ መጀመሪያ ነደደው፣ ቀጥሎ ገረመው፣ በመጨረሻም ዞረበት፡፡ ለማረጋገጥም ፊርማና ማኅተሙን አየው፡፡
‹ሊዮ ቶሎይስቶይኮ የለም› አለ ወዳጄ የሚናገረው ነገር ግራ ገብቶት፡፡
‹ታድያ አቶ ሊዮ ሲመጡ ይውሰዱ፣ ወይም እርስዎ ሕጋዊ ውክልና ይዘው ይምጡና ይውሰዱላቸው› አለ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ ነገሩን ያቀለለ መስሎት፡፡
‹ከማን ነው ውክልና የማመጣው› አለ ወዳጄ የማሽላ ሳቅ ስቆ፡፡
የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ መነጽሩን አፍንጫው ላይ አስደግፎ መዝገቡን እያየ ‹ከአቶ ሊዮ ቶሎይስቶይ ነዋ፡፡ ዛሬኮ ውክልና ቀላል ሆኗል፡፡ በ30 ደቂቃ ይጨርሱታል፡፡ ውጭ ሀገር ከሆኑም መላክ ይችላሉ› አለው፡፡
‹ሊዮ ቶሎይስቶይን ታውቀዋለህ?› አለው፡፡
‹እዚህ ቴአትር ቤት ድርሰት ይዞ የሚመጣው ብዙ ነው፡፡ ስንቱን ዐውቀዋለሁ ብለው ነው፡፡ በተለይ ጀማሪ ደራሲዎችን አናውቃቸውም፡፡ ይሄ ሊዮ የተባለው ጀማሪ ጸሐፊ ይሆን?› አለና በግማሽ መነጽሩ እያየ መለሰለት፡፡ እንዴት አድርጎ ሊያስረዳው ይችላል፡፡ ሊቃውንት ተብለው የተቀመጡት ገምጋሚ ኮሚቴዎች ያላወቁትን ይህንን የመዝገብ ቤት ሹም ዕወቅ ማለት ግፍ ነው፡፡ ‹ድኃው ምን አረገ ሊቆቹን ነው መርገም› አለ ገሞራው፡፡
‹ሊዮ ቶሎይስቶይኮ ሞቷል፡፡ እንዴት ነው ለሞተ ሰው ደብዳቤ የምትጽፉት?›
ውይ፣ ውይ፣ ውይ ብሎ የመዝገብ ቤቱ ሹም አዘነ፡፡ ባያውቀውም በባህሉ መሠረት ለሞተ ሰው ማዘን ያለ ነው፡፡
‹መቼ ነው የሞቱት፡፡ አይ ሰው መሆን፤ ቴአትራቸው ሳይታይላቸው፤ ትንሽም ቢሆን ገንዘብ ሳያገኙ፤ አይ ሰው፤ ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው› አለ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ አንገቱን እየነቀነቀ፡፡
‹የሞተውማ በ1903 ዓም የዛሬ 106 ዓመት በኅዳር ወር ነው› አለው ወዳጄ፡፡ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ ግራ ገባው፡፡ እስከዛሬ የተገመገመ ድራማ ሲያስረክብ ኖረ እንጂ ራሱ ድራማ ሠርቶ አያውቅም፡፡ አሁን ግን ራሱ ድራማ እየሠራ መሰለው፡፡    
‹አሁን የሚሉኝ ነገር እዚህ አንዳንዶች ጽፈው ከሚያመጡት የተሻለ ድራማ ይወጣዋል› አለና መዝገብ ቤቱ ሳቀ፡፡  
‹እንዴት የሚገመግሙት ሰዎች ሊዮ ቶሎይስቶይን አያውቁትም? ለመሆኑ ምን ተምረው ነው ገምጋሚ የሆኑት፡፡ የድርሰት አብነቶችን ሳያውቁ ምኑን ነው የሚገመግሙት? በ1821 ዓም ራሽያ ተወልዶ በ1903 ዓም የሞተውን ታላቁን የድርሰት ሰው ቶሎይስቶይን የማያውቅ የድርሰት ገምጋሚ ቴአትሮቻችንን ቢጥል ምን ይገርማል፡፡ ቴአትር የማያውቁ ሰዎች ቴአትር ከገመገሙ ቴአትር ሞቷል በለኛ፡፡›
የመዝገብ ቤት ባልደረባው አንገቱን እየነቀነቀ ‹ጌታው እኛ የታዘዝነው አቶ ሊዮ ቶሎይስቶይ ለሚባሉ ሰው አስፈርማችሁ ስጡ ተብለን ነው፡፡ እርስዎ ደግሞ አቶ ሊዮ ሞተዋል እያሉኝ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ከዐቅማችን በላይ ነው፡፡ አለቆቻችንን ያነጋግሩ፡፡ እነርሱ ወስነው ይሄዱና እዳው ለኛ ነው የሚተርፈው› አለው፡፡
ወዳጄ እያዘነም፣ እየተበሳጨም፣ እየተገረመም መጣና ተረከልን፡፡
አንድ መምህሬ ‹ጥበብ በነጋድያን እጅ ስትወድቅ ሸቀጥ፣ በሹመኞች እጅ ስትወድቅ ቀልድ፣ በሆዳሞች እጅ ስትወድቅ ዳቦ፣ በምንደኞች እጅ ስትወድቅ የሥራ ልብስ፣ በዐዋቂዎች እጅ ስትወድቅ ዘውድ ትሆናለች ይሉ ነበር፡፡ ጥበብን የማያፈቅራት ሰው እንጓን ሊገመግማት ሊያደንቃት አይችልም፡፡ ታዋቂው ባለቅኔ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ቅኔ ተቀኝቶ ሲወርድ እንኳን ቅኔ ሊያውቅ ቋንቋው ያልቀናለት ሹም ያገኘውና ‹ይበል ነው› ይለዋል፡፡ መጋቤ ምሥጢርም ‹አንተ ከሰማኸውማ ምኑን ቅኔ ተቀኘሁት› አለ አሉ፡፡ ጥበብ መጀመሪያ ፍላጎት፣ ከዚያም ዕውቀት፣ ቀጥሎም ተመስጦ በመጨረሻም አንክሮ ትሻለች፡፡ ጥበብን የተማረ ሁሉ አይደርስባትም፡፡ ‹አይቴ ብሔራ ለጥበብ - የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው› እያለ የሚፈልጋት እንጂ፡፡ ጥበብን የተሾመባት ሁሉ አያውቃትም፡፡ ‹ወበአይቴ ተረክበ አሠረ ፍኖታ - የጎዳናዋ ፍለጋ በወዴት ተገኘ› ብሎ የሚመረምራት እንጂ፡፡ ጥበብን ባለ ገንዘብ አይገዛትም፤ ‹መኑ ዐደወ ባሕረ ወተሣየጣ በወርቅ ቀይሕ - ባሕሩን ተሻግሮ በቀይ ወርቅ የገዛት ማነው?› እያለ በአንክሮ የሚከተላት እንጂ፡፡ ጥበብን ምንደኛ ቅጥረኛ አይደርስባትም፣ ‹ወመኑ ዐርገ መልዕልተ ደመናት ወአውረዳ - ከደመናት በላይ ወጥቶ ያወረዳት ማነው?› እያለ የሚመሰጥ እንጂ፡፡
የንጉሡ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ አማች ደጃዝማች ካሣ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ይሾማሉ፡፡ ዕውቀት በሹመት ይገኝ ይመስል ደጃዝማቹ በዩኒቨርሲቲ በር እንኳን ሳያልፉ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ሕዝቡን አስደነቀው፡፡ በዚህ ጊዜ፡-
ላም እሳት ወለደች
ወንፊት ውኃ ቀዳ
ሺ ግመል አለፈ በመርፌ ቀዳዳ
በሰንበሌጥ ቁጣ ወደቀ አሉ ዋርካ
ተከካ አልተከካ
ተቦካ አልተቦካ
ተሳካ አልተሳካ
የምንቸገረኝ ቤት ሁል ጊዜ ፋሲካ
በትእዛዝ ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ፡፡
 ተብሎ ተገጠመ ይባላል፡፡
አንዱ ጓደኛችንም ተርጓሚውን እንዲህ አለው ‹ለምን ‹ለቶልስቶይ፣ ባለበት› ብለህ ደብዳቤ አትጽፍለትም፡፡
ይድረስ ለሊዮ ቶሎይስቶይ፡፡ ይኼው ከስምንተኛው ሺ መድረሳችን ታወቀ፡፡ ለዕውቀት ያልደረሱ፣ ለመብል ያላነሡ፣ በትእዛዝ ሊቅ፣ በድጋፍ ምሩቅ የሆኑ፣ አበል የሚሰበስባቸው፣ ጥበብ የማይገዳቸው የሀገሬ ሹማምንት መፈጠርህንም፣ መሞትህንም ሳያውቁ፤ በሞትክ በመቶ ስድስት ዓመትህ ከመዝገብ ቤት መጥተህ ደብዳቤ እንድትወስድ ጽፈውልሃል፡፡ ከቻልክ የገነትን ጠባቂ መልአክ አስፈቅደህ ናና ደብዳቤህን ፈርመህ ውሰድ፡፡ ምናልባት የቀበሌ መታወቂያ ይቸግርህ ከሆነ ምርጫ ሲደርስ ከመጣህ ማውጣቱ ይቀሃል፡፡ የቤት ምዝገባ ሰሞን ግን እንዳትመጣ፡፡ አሳዛኙ ነገር ከ70 ዓመት በፊት ጽፈኸው ዓለምን ጉድ ያሰኘህበት ድርሰትህ በቴአትር ቤታችን ገምጋሚ ኮሚቴ ከልማታዊነትና ከሕዝባዊ ከብሔር ብሔረሰቦች መብት አንጻር ማረሚያ ስለተሰጠው እርሱን አስተካክለህ እንደገና ለማሳተም መሬት ላይ መቆየት የግድ ሊሆንብህ ነው፡፡ ያውም ድርሰትህ የኋላ ዘመን መሆኑ ከታወቀ የነፍጠኛና የጉልተኛ ድርሰት ነው ከመባል ከተረፈልህ ነው፡፡ ስትመጣ ስሙን እንጂ ድርሰቱን ብዙም ለማናውቀው የሀገርህ ሰው ለፑሽኪን ያሠራንለትን አደባባይ ትጎበኛለህ፡፡   


እዝራ በእዝራ መንፈስ

$
0
0

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ገጥመውን ከነበሩት ፈተናዎች አንዱ የሚያውቁት አለመጻፋቸውና የሚጽፉት አለማወቃቸው ነው፡፡ ባሕረ ጥበባት የተባሉት ሊቃውንት ትምህርታቸውን በቃል ከማስተማር ባለፈ በጽሑፍ አስቀምጠው ለማለፍ ብዙም አልተጉበትም፡፡ በዚህ የተነሣም በድርሰቱ ዓለም የምንጠቅሳቸውን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን አንድ ሁለት ብለን በጣቶቻችን ለመቁጠር እንችላለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሥነ ጽሐፈቱን የተማሩት ፊደላውያን ወደ ሊቅነቱ ባሕር አልገቡም፡፡ በዚህ የተነሣ ገልባጮች ወይም ቃል ጸሐፊዎች ፊደል እያደባለቁ፣ እየጎረዱና እየለወጡ አልፈዋል፡፡ አንድን ድርሳን ለማወቅም ልዩ ልዩ ቅጅዎችን እንድናመሳክር ግዴታ ጥለውብናል፡፡ ለዚህ ነው ‹የሚያውቁት ሳይጽፉ፣ የሚጽፉት ሳያውቁ አለፉ› እየተባለ የሚነገረው፡፡

ይህንን ቀንበር እየሰበሩ እንደነ ቅዱስ ያሬድ፣ እንደነ አባ ጊዮርጊስ፣ እንደነ ርቱዐ ሃይማኖት፣ እንደነ አርከ ሥሉስ፣ እንደነ አባ ባሕርይ፣ እንደነ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ እንደነ አባ ስብሐት ለአብ፣ እንደነ እጨጌ ዕንባቆም ያሉት የድርሰት ትሩፋት አቆይተውናል፡፡ በዘመናችንም ቢሆን እነ አቡነ ጎርጎርዮስን፣ እነ አቡነ መቃርዮስን፣ እነ አቡነ ጴጥሮስን፣ እነ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን፣ እነ አለቃ አያሌው ታምሩን፣ እነ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራን፣ እነ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን፣ ወዘተ. እንጠቅስ እንደሆነ እንጂ ዝርዝሩ ሆድ አይሞላም፡፡ በድርሰቱ የምናስታውሰው ጳጳስ ከፈለግንማ ከጎርጎርዮስ አንዘልም፡፡ ወደ ሊቃውንቱ ስንገባም ከላይ ካነሣናቸው በቀር ሊቅነታቸው የሚመጥን ሥራ የሠሩትን ለማስታወስ ዳገት ይሆንብናል፡፡
የሊቀ ሊቃውንት እዝራ መንገድ በዚህ ረገድ ቀና እንድንል ከሚያደርጉን ወገን ነው፡፡ በጎንደር መድኃኔዓለም ደብር የሚያስተምሩትና የሚያስተዳድሩት የአራቱ ጉባኤያት ሊቅ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ በቃል ከማስተማር ጎን ለጎን የሚያስተምሩትን ጽፈው እያሳተሙልን ነው፡፡ የርሳቸው መንገድ ከዘመነኞቻቸው ለየት የሚለው ሥራዬ ብለው ኅትመትን መሥራታቸውና ማከታተላቸው ነው፡፡ እርሳቸው ራሳቸው በሚያስተምሩት የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ላይ እንደሚለው ወንጌላቱና መልእክታቱ የተጻፉት ደቀ መዛሙርት ‹በቃል ያለ ይረሳል፣ በጽሑፍ ያለ ይታወሳልና ጽፈሕ ስጠን› ብለው መምህራቸውን በመጠየቃቸው ነው፡፡ እርሳቸውም የሚያስተምሩትን ተከትለው ታላላቆቹን አብነት የሚሆኑ ድርሳናት በትርጓሜያቸው እያሳተሙ ይገኛሉ፡፡
·         ትርጓሜትንቢተ ኢሳይያስ  
·         ሃይማኖተ አበው ትርጓሜ
·         ድርሳነ ቄርሎስ
·         ጰላድዮስ
·         ተረፈ ቄርሎስ
·         መልክአ ሠለስቱ ምእት
የሚባሉትን መጻሕፍት በሊቅ ትርጓሜ ጽፈው አሳትመዋል፡፡
‹ሁሉም ሰው ትምህርት ቤት አይገባም፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤት ቢገባም ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቤት አይገባም፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቤት ቢገባም ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት አይማርም፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ትምህርት ቢማር እንኳን ሁሉም እኩል አይረዳውም› ይባላል፡፡ መጻሕፍት የሚያስፈልጉት ለዚህ ነው፡፡ከየሊቁ ዕውቀት ለመሰብሰብ፡፡ ከቅርስነታቸው ባሻገር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከ200 ሺ በላይ የብራና መጻሕፍት ያሏት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለብዙዎቹ ደግሞ በቋንቋም፣ በቦታ ርቀትም ምክንያት ባዕድ ነን፡፡ እንዲህ እንደ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ዓይነት ሊቃውንት ሲገኙ ግን ክፍተቱን በዕውቀትና በኅትመት ይሞሉልናል፡፡ ጎንደር ሳንሄድ ጉባኤ እንውላለን፡፡
ሊቀ ሊቃውን እዝራ ከሃይማኖተ አበው ትርጓሜ መጽሐፍ በኋላ ‹ድርሳነ ቄርሎስ ወጰላድዮስ ምስለ ተረፈ ቄርሎስ› የተሰኘ ባለ 833 ገጽ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በአብነቱ መንገድ ለዕውቀት ፈላጊው ማኅበረሰብ ያበረከቱት ይህ አበርክቶ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ደቀ መዝሙር የተማረውን ያጠናበታል፤ ዕውቀት ፈላጊ ይመሰጥበታል፤ አጥኝ የሊቃውንቱን ትምህርት ይፈትሽበታል፡፡
እንደነዚህ ዓይነት ሊቃውንት ሲገኙ ማኅበረሰቡ ማበርታት አለበት፡፡ በሐሳባቸው ብንስማማም ባንስማማም ነባሩ ዕውቀት እንዳይጠፋ፣ ቅሩብ እንዲሆንና እንዲዳረስ የሚደረገውን ሥራ መደገፍ አለብን፡፡ እንዲጽፉ ማትጋት፣ ሲጽፉ ኅትመቱን መደገፍ፣ ሲያሳትሙ መግዛት፡፡ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአብያተ መጻሕፍት፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶችና ለዕውቀት ማዕከላት ጭምር፡፡ ዕውቀት ማለት የምፈልገውና የምንስማማበት ብቻ አይደለምና፡፡ ሊቁ ሲሞት ‹ድጓ ተሸክሞ መጣልህ መምህር› እያልን ማልቀሱ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ የሚያውቀውን ጽፎ፣ ለትውልድም አትርፎ እንዲሄድ ማበርታትና መርዳትም ይገባል እንጂ፡፡
ሊቀ ሊቃውንት እዝራ፣ በእዝራ ሱቱኤል መንፈስ ይቀጥሉ፤ እንዳይቆሙ፡፡      

ነፍሰ ጡሮች በኮርያ

$
0
0
 
በኮርያ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ስትጓዙ ፒንክ ቀለም ያላቸውና በእንግሊዝኛ ‹ፒ› የሚል ፊደል የተጻፈባቸውን መቀመጫዎች ታገኛላችሁ፡፡ የነዚህ መቀመጫዎች ዓላማ ነፍሰ ጡር ሴቶች ያለ ችግር ወንበር እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን የተጀመረ ፕሮጀክትም አላቸው፡፡ ነፍሰ ጡር ሴቶች ከብሉ ቱዝ ጋር የሚሠራ ነገር ይሰጣቸውና ወደ አውቶቡሱ ወይም ባቡሩ ሲገቡ በመቀመጫው አካባቢ ያለው ደወል ይጮኻል፡፡ ያን ጊዜ በነፍሰ ጡሮች ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረው ሰው ይነሣል፡፡
ይህንን ስመለከት የሀገሬ እናቶች ናቸው የታወሱኝ፡፡ በባቡሩ ውስጥ መጨናነቅ፣ በአውቶቡሱ ውስጥ መቆም፣ በታክሲው ወረፋና ግፊያ መከራ የሚያዩት ነፍሰ ጡሮች፡፡ ቀላል ባቡሩ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ጨው እንደጫነ መኪና ይሞላል፡፡ በዚያ ነፋስ በማያሳልፍ ጭንቅንቅ ውስጥ እንኳን ነፍሰ ጡር ሴት የባቡሩም ሾፌር በመከራ ነው የሚደርሰው፡፡ አውቶቡሶቻችንም ቢሆኑ መስኮታቸውን ለመክፈት ሕዝቡ ብርድ የሚፈራባቸውና ሳንዱች በሚሠራ ሙቀት የተሞሉ ናቸው፡፡ የታክሲዎቻችን ሰልፍ እንኳን አይነሣ፡፡ ምንም እንኳን ለነፍሰ ጡር እናቶች ያለን ክብር ተንጠፍጥፎ ባያልቅም የሰልፉ ርዝመት ግን ለሌላ ቅድሚያ የሚያሰጥ አልሆነም፡፡ 

በዚህ ሁሉ መካከል የሚሰቃዩት ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎቶቻችን እንደኮርያውያን አላስታወሷቸውም፡፡ ቅብጠት ነው ብለው ትተዋቸውም ይሆናል፡፡ ‹ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ› ይላልና የሀገሬ ሰው ምንም እንኳ የተብቃቃና የዘመነ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ባይኖረንም ባለን ዐቅም ላይ ሕግና ደግነት መጨመር ግን አያቅተንም፡፡ እነዚህ ነገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጀመሩ አስቸጋሪ፣ ውስብስብና ለአፈጻጸም የማይመቹ ይመስላሉ፡፡ አጥብቀን ሥርዓቱንና ሕጉን ካስፈጸምነው ግን እየቆየ ባሕል ይሆናል፡፡
በታክሲዎቻችን ቢያንስ አንድ፣ በባቡሮቻችን ቢያንስ አራት፣ በአውቶቡሶቻችን ደግሞ ቢያንስ ሦስት ወንበሮችን ለነፍሰ ጡር እናቶች ለይተን ብናዘጋጃቸው፡፡ ልዩ የቀለም ምልክት ተሰጥቶ በላያቸው ላይ ብንጽፍባቸው፡፡ የእነዚህ ወንበሮች ዓላማ ነፍሰ ጡሮችን ብቻ መጠበቅ ሳይሆን ቅድሚያ ለነፍሰ ጡር እናቶች መስጠት ነው፡፡ እነርሱ በማይኖሩበት ጊዜ ሌሎች ተሳፋሪዎች ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ፡፡ የሚዘጋጀው ወንበር አየር በመስኮት ለማስገባት ምቹ በሆነበት አቅጣጫና ለመውረድና ለመውጣት በማያስቸግራቸው አካባቢ ቢሆን ደግሞ ይመረጣል፡፡
ከታክሲ ባለቤቶች፣ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ጋር ብንመክርበት ደግሞ ሐሳቡ ከውጤት በላይ ይሄዳል፡፡ መቼም እናቱን የማይወድ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ በርግጥ በእናቱ የሚሳደብ ባይጠፋም፡፡ በፍቅር ላይ ዕውቀት ሲጨመርበት ደግሞ ነገሩን የሠመረ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በታክሲ ፌርማታዎች ላይ ተራ የሚያስከብሩ ወገኖቻችን ሐሳቡን ‹ለእናቴ የማደርገው ነው› ብለው እንዲቀበሉት ከተደረገ እናቶቻችን ሰልፍ ይቀንስላቸዋል፤ ግፊያም ይቀርላቸዋል፡፡ ወንበር መስጠት ቢያቅተን ቆመው ከሚንቃቁ ድንጋይ ላይም ቢሆን ተቀምጠው ይጠብቃሉ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች የፖሊስ አካላት ነገሩን ማስፈጸም አንዲችሉ ሐሳቡን ሕግ ሊደግፈው ይገባል፡፡ ያን ጊዜ እምቢ የሚለውን ጋጠ ወጥ ከእርግማን ባለፈ ሕግ ፊት ለማቅረብም ይቻላል፡፡
ወደ ክፍለ ሀገር በሚያመሩ አውቶቡሶች ላይ ይህን ብናደርግ ከአዲስ አበባ ይልቅ በክፍለ ሀገር የሚኖሩ እናቶችን እንጠቅማቸዋለን፡፡ በይበልጥም የአውቶቡስ መነሻ ባልሆኑ ትናንሽ ከተሞች ጎዳና ላይ ወጥተው አውቶቡስ እንዲጭናቸው እጃቸውን እያርገበገቡ የሚለምኑ ነፍሰ ጡር እናቶች የተሻለ ዕድል ያገኛሉ፡፡ እኛም ተሳፍረን የምንጓዘው ወዳጆቻቸው መብታቸውን ለማስከበር የሚያስችል የሕግ ዐቅም እናገኛለን፡፡
በተለመደው አሠራራችን ለሽማግሌዎች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለእናቶች ቅድሚያ የመስጠት ባህል ያለን ይመስለናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን በሕግ ካልተደገፉና ያልተከበረላቸው ለማስከበር፣ ያላከበሩ ለመቀጣት ካልቻሉ በሂደት መጥፋታቸው የማይቀር ነው፡፡አሁንም የምናየው ይህንን ነው፡፡ በብዙ ሀገሮች የሕግ አንቀጽ ተጠቅሶ ለእነዚህ አካላት ቅድሚያ እንዲሰጥ በግልጽ በአደባባይ ይጻፋል፡፡ አስፈላጊ ሲሆንም ልዩ መታወቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ በመኪናቸው ላይ የሚለጠፍ ስቲከርም አላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የእነዚህ አካላት መብት እንዲከበር የሚሹ አጋሮች አብረዋቸው መብታቸውን ለማስከበር ይችላሉ፡፡ ሕግ የሚያስከብሩ አካላትም ሕግ ነውና በግድ እንዲከበር ለማድረግ ዐቅም ይሰጣቸዋል፡፡
እንደ ኮርያውያን ለሕጉ የማስፈጸሚያ አሠራር ስናበጅለት ደግሞ ሸጋ ይሆናል፡፡ እነርሱ ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጠውን ቦታ ቀለሙን ለይተው ብቻ ሳይሆን ነፍሰ ጡር ሴት እየመጣች መሆኑን የሚናገር የቴክኖሎጂ ሥርዓትም ዘርግተውለታል፡፡ እዚያ እስክንደርስ ድረስ እጃችን ባለው ነገር መጀመር እንችላለን፡፡
በተለይ ግን የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች እናንተው ራሳችሁ ተነጋግራችሁ በመወሰንና ተግባራዊ በማድረግ ለእናቶቻችሁ ያላችሁን ክብርና ፍቅር ማሳያ ብታደርጉት ሞገስ ይጨምርላችኋል፡፡

ፓንክረስት ሞተ ይላሉ

$
0
0

ፓንክረስት ሞተ ይላሉ
አያፍሩም ደግሞ ይዋሻሉ፤
ታሪክን እንደነዳጅ ቆፍሮ
ለቅርስ እንደ ውርስ ተከራክሮ
ላልተወለደባት ምድር ከተወላጅ በላይ ለፍቶ
በደም ከወረሷት በላይ በፍቅር ልቧ ውስጥ ገብቶ
ከእናቱ እስከ ልጁ - ለጦቢያ ልቡን ሠውቶ
በትውልድ ማማ ላይ ቆሞ የጸናውን ጌታ
ሞቷል እያለ ይዋሻል ታሪክ የጠላ ቱማታ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው
ብርቱ እንደ ፓንክረስት የሚነጥቀው
ሞኝ እንደ ከመዳፉ የሚቀማው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ጸጋ ነው
ልባም እንደ ዐሉላ የሚቀባው
ሞኝ እንደ ባንዳ የሚነሣው፤
ስንቱ ከማዕዘናተ ዓለም
እንደ ኦሎምፒክ ከትሞባት
ባተወለደባት ምድር
እትብቱን አምጥቶ ሲቀብርባት
ከደጁ ሞፈር ሲቆረጥ
ጅላጅል ቆሞ አንጎላጀ
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ
ሐበሻ ሳይሆን አረጀ፡፡
እንዲህ ያለው ልብ አልባ
ልባሙን ሞተ ይለዋል
በትውልድ ማማ ላይ ያለ
መቼ ልብ ሰጥቶ ይሰማዋል፡፡
ፓንክረስትማ አልሞተም
በኢትዮጵያ ልብ ይኖራል
በዐጸደ ነፍስ ሆኖ
ጠላቷ ፍግም ሲል ያያል፡፡
የካቲት 10 ቀን 2009 ዓም

የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ፡- ከእቴጌ ጣይቱ እስከ ዶክተር ክንደያ

$
0
0

click here for pdf
የመቀሌው ምሽግ ጥንታዊ ፎቶ
የአድዋ ጦርነትና ድል ሲነሣ ምንጊዜም አብሮ የሚነሣ የኢትዮጵያውያን የጀግንነትና የብልሃት ዐውደ ውጊያ አለ፡፡ የመቀሌው ምሽግ ውጊያ፡፡
ጣልያኖች የመረብን ወንዝ ተሻግረው ወደ ትግራይ ሲገቡ ጠንካራ ምሽግ ከሠሩባቸው ቦታዎች አንዱ መቀሌ እንዳ ኢየሱስ ነበር፡፡ ምሽጉን ማጆር ቶዞሊ አስጀምሮት እርሱ በአላጌው ውጊያ ሲሞት ማጆር ጋልያኖ አጠናቅቆታል፡፡ ለመቀሌው ምሽግ መጠናከር ዋናው ምክንያት ጣልያኖች አላጀ ላይ በራስ መኮንን በሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የገጠማቸው ሽንፈት ነው፡፡ ጄኔራል አርሞንዲ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓም የደረሰበትን የአላጌን ግንባር ሽንፈት ተከትሎ ወደ ኋላ በሸሸው የጣልያን ወታደር አማካኝነት ከባሕር ወለል በላይ በ2240 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውን የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ የበለጠ እንዲጠናከር አደረገ፡፡ በቦታው የሚገኘውን የኢየሱስን ታቦት አስወጥቶ ቦታውን ሙሉ በሙሉ ምሽግ አደረገው፡፡
እነ ፊታውራሪ ገበየሁ ታሪክ የሠሩበትና የኢትዮጵያውያንን ጥምር ክንድ ጣልያን በሚገባ በቀመሰበት በአላጌ ግንባር ማዦር ቶዜሊ በራስ ዐሉላ ብርጌድ ደረቱን ተመትቶ የወደቀበት ነው፡፡
አላጌ በሩ ላይ ሲወርድ ማዦር
እንደ ግራኝ ሁሉ በሰባት አረር - ተብሎለታል፡፡ 

 
በዚህ ጦርነት አምስት ካፒቴኖች፣ ዐሥር የመቶ አለቆችና ሁለት ምክትል መቶ አለቆች በጦርነቱ ተገደሉ፡፡ ሁለት ሺ የሚደርሱ የኢጣልያ ወታደሮችም አለቁ፡፡ ራስ መኮንንም የጣልያኖቹን ሬሳ ከየቦታው አስለቅመው በቤተ ማርያም አስቀበሩት፡፡ ይህም ጣልያኖች መቀሌ ላይ ጠንካራ ምሽግ  እንዲሠሩ አደረጋቸው፡፡ ጄነራል አርሞንዲ የመቀሌው ምሽ በተመለከተ የሚዋዥቅ ሐሳብ ነበረው፡፡ ትቶ ለመሄድም አስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ማድረግ የጣልያንን ክብር መንካት ነው ብሎ ያመነው፣ ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያን ጦር የሚንቀው ጋልያኖ የመቀሌው ምሽግ ላለማስደፈርና ተዋግቶ ለመሞት ቆረጠ፡፡ 
በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጊዜ መልሶ የተሠራው የመቀሌው ምሽግ
ጳውሎስ ኞኞ እንደሚለው ‹የመቀሌ ምሽግ በደቡብ በኩል 3 ሜትር ስፋት ያለው ግንብ እየሆነ ተገነባ፡፡ ምሽጉ ዙሪያ ክቡን ካለው አጥር ሌላ ከግንቡ 30 ሜትር ያህል ራቅ ብሎ በጣም የሾሉ እንጨቶች በምሽጉ ዙሪያ በብዛት ተተከሉ፡፡ ካንዱ ሹል እንጨት እስከ አንዱ ሹል እንጨት ያለው ርቀትም 20 ሳንቲ ሜትር ያህል ነበር፡፡ እነኚህ ሹል እንጨቶች ከመሬት በላይ ያላቸው ከፍታ 30 ሳንቲ ሜትር ነው፡፡ ከሹል እንጨቶቹ አልፎ ደግሞ እሾካማ ሽቦ እየተድቦለቦለ በምሽጉ ዙሪያ እየተተከለ ተከምሯል፡፡ ከሽቦው ውጭ ደግሞ ጠርሙስ እየተሰበረ እንዲነሰነስ ተደረገ› ይላል፡፡
ጣልያኖች ይህንን ያደረጉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ባዶ እግራቸውን ናቸውና ይህን አደገኛ እሾሃማ አጥር ተሻግረው ለመግባት ይከብዳቸዋል ብለው በማሰባቸው ነበር፡፡ እንዳሉትም ምሽጉን ለመስበር በተደጋጋሚ የተደረጉ ሙከራዎች ሊሳኩ አልቻሉም፡፡
ጣልያኖች ከምሽጉ ሥራና አጥር በተጨማሪ በምሽጉ ውስጥ ጠንካራ ጦር መሽጎ ነበር፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደሚሉት  በጋልያኖ የሚመራው አንድ ባታልዮን ጦር 21 የጦር መኮንኖችን፣ 176 ነጭ ለባሾችን፣ 1150 የሀገር ተወላጅ ወታደሮችን እና አንድ መድፈኛ ጦር የያዘ ነበር፡፡ ጳውሎስ ኞኞም የመቀሌ ምሽግ 20 ከፍተኛ መኮንኖች 13 ዝቅተኛ መኮንኖች፣ 150 ባለ ሌላ ማዕረግ ወታደሮችና አንድ ሺ ጥቁር ወታደሮች ነበሩበት ይላል፡፡
በራስ መኮንን የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የአላጀን ድል ተከትሎ ወደ መቀሌ ገሰገሠ፡፡ ኦገስት ዋይልድ የራስ መኮንን ጦር ኅዳር 30 ቀን 1888 ዓም የመቀሌውን ምሽግ ከብቦ መቀመጡን ጦርነቱንም ታኅሣሥ 18 ቀን መጀመሩን የሚገልጡ አሉ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ግን ጦርነቱ የተጀመረው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ መቀሌ ከገቡ በኋላ ታኅሣሥ 30 ቀን መሆኑን ይናገራል፡፡
ዐፄ ምኒሊክ መቀሌ ሲገቡ የመቀሌው የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ ዙሪያውን ተከበበ፡፡ ጦሩ ከጣልያን መድፍ ርቀት ውጭ ሆኖ በጨለቆት በኩል የንጉሠ ነገሥቱ ጦር፣ የራስ መኮንንና የፊታውራሪ ገበየሁ ጦር፤ በደብሪ በኩል የሸዋ ጦር፤ በምሥራቅ በኩል የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትና የራስ መንገሻ ጦር፤  በገምበላ በኩል የራስ መንገሻ አቲከም እና የራስ ወሌ ጦር እንዲሠፍር ተደረገ፡፡ ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለውና በጅሮንድ ባልቻ ደግሞ መድፎቻቸውን ይዘው በስተ ምሥራቅ በኩል አመቺ ሥፍራ ያዙ፡፡ 

ብዙዎቻችን እንደሚመስለን የኢትዮጵያ ጦር ወደ አድዋ ሲዘምት ኋላ ቀር መሣሪያ ብቻ አልያዘም፡፡ የኢትዮጵያን ጦር ለውጤት ያበቁት ጠንካራ የሀገር ፍቅር፣ ተገቢ የሆነ ዝግጅትና አደረጃጀት፣ የሁሉም ሕዝብ ሁለገብ ተሳትፎ፣ የዐፄ ምኒልክና የጦር ጄኔራሎቻቸው የአመራር ጥበብ፣ ከዚያ በፊት ከውጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ውጊያዎች የተቀሰሙ ልምዶች እና ትክክለኛ የጦርነት ምክንያት ናቸው፡፡
ዐፄ ምኒልክ ለማይቀረው ጦርነት ቅድመ ዝግጅት አድርገውበታል፡፡ ሀገሪቱ ጠብቃ ባቆየቻቸው መሣሪያዎች ላይ ከፈረንሳይ ተገዝተው በጅቡቲ በኩል የገቡትና በየዐውደ ውጊያው የተማረኩት ዘመናዊ መሣሪያዎችም ለጦርነቱ ውለዋል፡፡ ኦገስት ዋይልድ ይህንን ሁኔታ ሲገልጠው ‹the Hotchkiss quick firing guns with a longer range …were of a caliber of about two inches, firing both solid and percussion shell, and their range and accuracy were much superior to the muzzle-loading mountain guns of the Italians.> ይላል፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያም ‹ከፈረንሳይ ሀገር ተገዝቶ የመጣውና በኢትዮጵያውያን እጅ ያለው የመድፍ ጥይት እስከ 4500 ሜትር ድረስ ሄዶ የሚመታ ሲሆን የኢጣልያኖች ግን 3800 ሜትር የሚሄድ ነበር› ይላሉ፡፡ በዚህ መሣሪያ ላይ እነ ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለውና በጅሮንድ ባልቻ አባ ነፍሶ ያሳደጉት ፈረስ ያህል ተክነውበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን በመድፎቻቸው እየተረዱ ምሽጉን ሰብረው ለመግባት በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ መሰላል አምጥተው ወደ ምሽጉ ከታች ወደ ላይ በድፍረት ለመውጣትም ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ምሽጉ ከነበረበት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ አንጻር ሊሳካ አልቻለም፡፡
በመጨረሻ ግን የእቴጌ ጣይቱ መላ በአጭር ጊዜ ምሽጉ እንዲለቀቅ አደረገ፡፡ 
ማይ አንሽቲ ምንጭ
 እቴጌ ጣይቱ ሊቀ መኳስ አባተ ቧ ያለው ጋር መክረው ‹ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣለሁ፣ ለሞቱትም ተዝካራቸውን አወጣላቸዋለሁ› ብለው ብለው የላኳቸው በዝቅተኛ መኮንኖች የተመሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከምሽቱ በ11 ሰዓት ገብረ ጊዮርጊስ ድል ነሤ እና ሸዋዬ የሚባሉ አሽከሮች ሶስት ሦስት መቶ ወታደሮች ይዘው ወደ ማይ አንሽቲ ምንጭ ወረዱ፡፡ ምሽጋቸውንም ሠሩ፡፡ እቴጌይቱ ሌሊቱን ሙሉ ‹አምላኬ ሆይ አታሳፍረኝ እርዳኝ› እያሉ ሲጸልዩ ማደራቸውን ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ዐፄ ምሊክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጽሐፍ ላይ ይገልጣሉ፡፡ 

ማይ አንሽቲ ከእንዳ ኢየሱስ ምሽግ 150 ክንድ ርቀት ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ወታደሮቹ በሌሊት ገሥግሠው ምንጩን ከበቡት፡፡ ምንጩ የሚገኘው ከእንዳ ኢየሱስ ምሽግ ወረድ ብሎ ገደል ሥር ነበር፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ወታደሮች ከምንጩ በ15 ክንድ ርቀት ላይ አድፍጠው ተቀመጡ፡፡ ጣልያኖች ምንጩ ለምሽጉ ቅርብ ስለነበር ይያዛል ብለው አልገመቱም፡፡ ውኃው በኢትዮጵያውያን መያዙን ሲያውቁ ምንጩን ለመቆጣጠር መድፎቻቸው ጎትተው አውጥተው በተደጋጋሚ ጥረት አደረጉ፡፡ ቦታው ከምሽጉ በኩል ለሚደረግ የመድፍ ምት ምቹ አልነበረም፡፡ ለፊት ለፊት ውጊያም ከጣልያኖች ይልቅ ለኢትዮጵያውያን የተመቸ ነበር፡፡ ምንጩን ለመቆጣጠር ጣልያኖች ያደረጉትን ጥረት የኢትዮጵያ ወታደሮች አደናቀፉት፡፡ ሊቀ መኳሽ አባተና በጅሮንድ ባልቻም የጣልያን መድፎችን በመነጽር አይተው ደበደቧቸው፡፡ ከዚያም አልፈው የጣልያኖችን መድፍ በመድፍ አፉን መትተው ሥራ አስፈቷቸው፡፡ በዚህም ምክንያት
አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው
ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው - ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡
የጦርነቱ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ የጣልያኖቹ ውኃ እያለቀ መጣ፡፡ መጀመሪያ በራሽን ውኃ መታደል ጀመረ፡፡ በመቀጠልም ችግሩ ከጣልያን ወታደሮች ዐቅም በላይ ሆነ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ግን ለምሽጉ ጠባቂዎች በየቀኑ ስንቅ ይልኩ ነበር፡፡   
ጣልያኖቹ ቀሪ ዕጣ ፈንታቸው ሞት መሆኑን ሲያውቁት ከ45 ቀን ከበባ በኋላ በድርድር እጃቸውን ለመስጠትና ምሽጉን ከነ መሣሪያው ለቀው ለመውጣት ወሰኑ፡፡ ጥር 21 ቀን በድርድሩም መሠረት ምሽጉ ተለቀቀ፡፡ ጣልያኖች መሣሪያቸውን አስረክበው ወጡ፡፡ ዐፄ ምኒልክም በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ሸኟቸው፤ ዳግም በውጊያ ካገኟቸው እንደማይምሯቸው አስጠነቀቋቸው፡፡ ይህንን ውጤት ያመጣው እቴጌ ጣይቱ የዘየዱት መላ ነው፡፡ አስቀድመው ለጣልያኑ አምባሳደር ለአንቶኒሊ እስንዳስጠነቀቁት ጦርነቱን አልፈለጉትም ነበር፡፡ በሀገር ላይ ሲመጣ ግን ‹እዚያው የጦሩ ዐውድማ ላይ እንገናኛለን› ነበር አንቶኖሊን ያሉት፡፡ እቴጌ ጣይቱ ያሉት አልቀረም ለአድዋው ድል በር ከፋች የሆነውንና የካቲት 23 ቀን ለሚዋጋው ሠራዊት የሞራል ከፍታ የፈጠረውን ድል አስመዘገቡት፡፡ 
ለጎብኝ እንዲያመች ሆኖ የተጠገነው ምሽግ የግቢው መግቢያ
 እቴጌ ጣይቱ ታሪኩን ለመሥራት ሳይከብዳቸው ለ121ኛው የዐድዋ ድል በዓል አከባበር አድዋ ላይ የተገኙት ‹አርቲስቶች› ስማቸውን ማንሣት ከበዳቸው፡፡ ‹ኢትዮጵያውያን በፈጠሩት ዘዴ› ብለው ያለፉት ይህንን የጣልያን መዛግብት ሳይቀሩ በድንቅ የሚያነሡትን የእቴጌ ጣይቱን ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ ዐድዋን እያከበሩ ምኒሊክንና ጣይቱን አለማንሣት ማለት አሜሪካን ከመከፋፈል ታድጎ ወደ አንድነት ያመጣትን ‹የአሜሪካ የርስበርስ ጦርነት› የሚባለውን ዘመቻ ታሪክ አንሥቶ አብርሃም ሊንከንን መዝለል ማለት ነው፡፡ የዶጋሊን ድል አንሥቶ ዐሉላ አባ ነጋን መዘንጋት፣ የሕወሐትን የመቀሌ እሥር ቤት ሰበራን ታሪክ አንሥቶ ኃየሎም አርአያን መተው ማለት ነው፡፡ በዐድዋው በዓል ላይ የዐፄ ምሊክ ስም ያነሡት ሁለት ተናጋሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪና የጉዞ አድዋ አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ፡፡ ለእናንተ ኮፍያችንን በክብር እናነሣለን፡፡ 
 
የግቢው ንጣፍ በብርጭቆ ስብርባሪ ተነጥፏል
እንደ ንጉሡ አጎንብሱ ብለው ጣልያን ዐድዋ ላይ የሠራውን ስሕተት በደገሙት አርቲስቶቻችንና አርቲስቶቹ ታሪክ ዘለው ታሪክ እንዲያጠለሹ መመሪያ በሰጡት አለቆቻቸው እያዘንን 121ኛውን የዐድዋ ድል ልናከብረው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ሲረዳን ግን የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ እንደገና እንዲያዝ ያደረገውን ታሪክ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓም መቀሌ ላይ አየን፡፡ 
የዛሬ 2 ዓመት የአድዋ ተጓዦ ወጣቶች በእንዳ ኢየሱስ በኩል ሲያልፉ ምሽጉ ፈራርሶ፣ ተንቆና ተረስቶ፣ በዚያ ላይ የተሠዉት ኢትዮጵያውያን መቃብር ክብሩ ተዋርዶ፣ ዐጽማቸው የትም ወዳድቆ ተመለከቱ፡፡ አዘኑ፡፡ ዐፄ ምኒልክ ያልቻልክ በኀዘንህ እርዳኝ እንዳሉት፡፡ አዝነው ግን ዝም አላሉም የመቀሌ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረ ሕይወት ይህንን ነገር እያዩ ለምን ዝም አሉ? ሲሉ ጠየቁ፡፡ ያሬድ ሹመቴ ስሜት የሞላበት ግልጽ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ሌሎችም ያንን ጩኸት አስተጋቡት፡፡ ‹መቼ ተነሡና የወዳደቁት› የሚለው የእጅጋየሁ ሺባባው ቃል እውነት ሆኖ አየነው ብለን ኀዘናችንን ገለጥን፡፡
ምሽጉ እንዳይፈርስ የተገነባው የመጠበቂያ ግንብ
 ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማ ባለ ሥልጣን፣ ሰምቶም የሚፈጽም ባለ ሥልጣን በሥዕለት ከሚገኙ ነገሮች መካከል ናቸው፡፡ ዶክተር ክንደያና አመራራቸው ግን ሰሙ፡፡ ሰምተውም ቅርስን የሚመለከተውን የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ክፍል ጠሩ፡፡ከዩኒቨርሲቲው የግንባታ ክፍል ጋር በመሆን ታሪኩንና ቅርሱን የሚጠብቅ ዲዛይን እንዲዘጋጅ አዘዙ፡፡ የዲዛይኑን ዝግጅትም ራሳቸው ተከታተሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው በጀትና የሰው ኃይል የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ እንዲጠገን፣ አካባቢው እንዲጸዳ፣ ለጎብኚዎች በሚሆን መልኩ እንዲዘጋጅ፣ ዐጽሞቹ በክብር እንዲሰበሰቡና በልዩ ሥነ ሥርዓት እንዲቀበሩ አስደረጉ፡፡
የምሽጉ ጥገና ሥራ ተፈጽሞ ባለፈው እሑድ የካቲት 26 ቀን ተከብሯል፡፡ ጣልያን አድርጎት እንደነበረው ዙሪያውን በሽቦ ታጥሯል፡› መንገዱ ጣልያን ኢትዮጵያውያንን ለመከላከል አድርጎት እንደነበረው የብርጭቆ ስብርባሪ ተነስንሶበታል፡፡ በመቃብሩ ላይ ታሪኩን የሚዘክሩ ማስተዋሻዎችን ለማድረግ ተመቻችቷል፡፡ ከመንገዱ መጨረሻ ያለውን መቃብር በንጹሕ ሣር ለማሣመር ተሰናድቷል፡፡ ከመከራው መንገድ በኋላ ለስላሳ መስክ ይጠብቀናል፡፡ ከዐርበኞቹ ተጋድሎ በኋላ ያገኘነውን ነጻነት ለማስታወስ ነው፡፡ 
 
ምሽጉ ከውጭ ሲታይ
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይነት እቴጌ ጣይቱ በብልሃት ያስያዙትን ታሪካዊውን የማይ አንሽቲ ምንጭ ታሪካዊነቱን ጠብቆ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ለማድረግ መወሰኑን በዕለቱ ገልጧል፡፡
ታሪካዊ ቅርሶች ጠባቂና ተከባካቢ ካላገኙ ወደ ተረትነት መቀየራቸው የማይቀር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ‹ዩኒቨርሳል› ነገሮችን ከማጉላት ይልቅ ‹መንደራዊ› ነገሮችን ወደ ማቀንቀን ከሚወርዱ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ታሪክ ዐውቆ፣ ታሪክንም ጠብቆ፣ ታሪክ የሚሠራ ትውልድ እንዲያፈሩ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ችቦውን ከፍ አድርጎታል፡፡ 

ስሟ የጠፋው አህያ

$
0
0


የፊታችን እሑድ የሆሳዕና በዓል ይከበራል፡፡ ሆሳዕና የአህዮች ክብረ በዓል ነው፡፡ መቼም እንደ ዕለተ ሆሳዕና አህያ በታሪኳ የከበረችበት ቀን ያለ አይመስለኝም፡፡ ዙሪያዋን እየተዘመረ፣ ዘንባባ ተይዞ፣ ምንጣፍ ላይ እግሯ በኩራት እየተራመደ በኢየሩሳሌም ጎዳና ላይ ተጉዛለች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አህያ ስሟ እንዴት ሊጠፋና የድድብና፣ የሸክምና የድንቁርና ምሳሌ እንደሆነች እግዜር ይወቅ፡፤ ምናልባትም ከ50 ዓመት የዘለለው የአህያ ሽማግሌ አይገኝም እንጂ እንጠይቀው ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ታድያ የአንድ አህያ እድሜ ቢበዛ ከሃምሳ አይበልጥም፡፡ ያም ሆኖ በአዳጊ አገር ውስጥ እድሜ ያጥራልና የአህያም እድሜ ከ10 አይበልጥም አሉ፡፡ ሽማግሌ ከሌለ እዚህ ሀገር ታሪክን ማን ያስታውሰዋል፡፡ የሀገሬ ታሪክ ነገርን ከመጽሐፍ በላይ በሚያስታውሱ ሽማግሌዎች ልቡና እንደ ጽላት ተጽፎ እንደሚገኝ የማያውቀው ያ የጀርመን ፈላስፋ ሄግል ‹ያልተጻፈ ታሪክ ታሪክ አይደለም› አለ፡፡ 

አህያ ከሰው ጋር መኖር ጀመረች የምትባለው የዛሬ 5000 ዓመታት ገደማ አፍሪካ ውስጥ ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ሆኖ እየቀረበ ያለው ደግሞ የሜዳ አህያ የሚገኘው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማልያ ውስጥ ብቻ መሆኑ ነው፡፡  ሰውን ማገልገሌ ካልቀረ አገር ላቅና ብላ መጀመሪያ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄዳ በኋላ ደግሞ ወደ አውሮፓ ተሻገረች፡፡ አህያን መጀመሪያ ከአፍሪካ የወሰዷት ሮማውያን ናቸው፡፡ ሮማውያን ወደ ሰሜን አውሮፓ ሲስፋፉ በዚያው ሰሜን አውሮፓ አስገቧት፡፡ እንኳን ዛሬ አልሆነ እንጂ ከአፍሪካ መሄዷ ሲታወቅ ሕገ ወጥ ስደተኛ ነበር የምትባለው፡፡ የግብጽ ሥልጣኔ እያልን የምንጠራው ታላቁ የዓባይ ሥልጣኔ ‹የአህዮች ሥልጣኔ› ነው ይሉታል፡፡ ያ ሁሉ ሀብት ከምድረ አፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተጭኖ ግብጽ የገባው በአህያ ጀርባ ነውና፡፡ አውሮፓና እስያን ያገናኝ በነበረውና ከሰላማዊው ውቅያኖስ እስከ ሜዲትራንያን ባሕር በተዘረጋው ጥንታዊው የሐር መንገድ ላይ ሲወጡ ሲወርዱ የኖሩት አህዮች ናቸው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ43 ዓመት ሮማውያን እንግሊዝን በወረሩ ጊዜ  ብሪታንያ የዘለቁት አህዮች ዛሬ እዚያው ብሪታንያ ውስጥ ለመኖር ከፈለጉ ፓስፖርት እንዲኖራቸው ሕጉ ያዛል፡፡ በ16ኛው መክዘ ደግሞ ስፔኖች አህያን ወደ ላቲን አሜሪካ አደረሷት፡፡ አህያን ያለ ዲቪና አሳይለም በ1598 ዓም ሰሜን አሜሪካ የወሰዳት ዩአን ዲ ኦናቴ የተባለው አሳሽ ነው አሉ፡፡ ቻይና ዓለምን የምትመራው በሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን በአህያ ብዛትም ጭምር ነው፡፡ በምድሪቱ ላይ ካሉት 41 ሚሊዮን አህዮች መካከል 11 ሚሊዮኑ አህዮች የሚገኙት ቻይና ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ5 ሚሊዮን፣ ሜክሲኮ በ3.2 ሚሊዮን ሁለተኛና ሦስተኛ ናቸው፡፡ 

‹አንድ እግረኛ ያወራውን ሃምሳ ፈረሰኛ አይመልሰውም› የተባለው ደርሶባት እንጂ አህያ እንኳን ‹ደደብ› አልነበረችም፡፡ አህያኮ የኖረችበትን አካባቢና ሌሎች ወዳጅ ዘመድ አህዮችን ሳትረሳ ለሃያ አምስት ዓመታት ማስታወስ የምትችል ፍጡር ናት፡፡ ዛሬ ሰው በሳምንትና በወር እየተረሳሳ ‹እገሌኮ ረሳኝ፣ እጄ አመድ አፋሽ ነው፣ አይ ሰው - ከዓይን ከራቁ ከልብ ይርቁ› እያለ በሚተርትበት ዘመን ሃያ አምስት ዓመት የበላችበትን ቤትና አብረዋት የበሉትን አህዮች የማትረሳውን አህያ እንዴት ‹ደደብ› እንላታለን፡፡ እስኪ ወጣ በሉና ገጠሩን ተመልከቱትማ፡፡ ገበሬው ለገበያ ይወጣና አህሉን ሽጦ ሲመለስ፤ መንገድ ዳር ወዳለው ጠጅ ቤትና ጠላ ቤት ጎራ ይላል፡፡ አህያዋ ግን ግራና ቀኝ ያገኘችውን ሣር እየጋጠች ቀጥ ብላ ወደ ሠፈሯ ታቀናለች፡፡ ጅብ ካላገኛት፣ ሌባ ካልሰረቃት በቀር አህያ ቤቷን ስታ አትጠፋም፡፡

አህያን ‹ደደብ› ያስባላት ሰው በፈለገው መንገድ እንደፈለገው ስለማይወስዳት ነው፡፡ ይኼው የፋርሱ ጠቢብ በለዓም እንኳን እስራኤልን ሊረግም ሲጓዝ አህያው አልሄድም ብትለው እስኪበቃት በዱላ ዠልጧት የለ፡፡ ግን ጥፋቱ የማን ሆኖ ተገኘ? የራሱ የበለዓም ነዋ፡፡ አህያዋ ያየችውን ጠቢቡ ለማየት ባለመቻሉ፡፡ አህያዋ ከፊቷ መልአኩን አየች፤ ከዚያ ቆመች፡፡ ጠቢቡ ግን  አላየውም፡፡ ታድያ አህያ ከጠቢቡ በላይ ጠቢብ አልሆነችም፡፡ ይህ የአህያ ጠባይ በሳይንስ ተረጋግጦላችኋል፡፡ አህያ ትሞታለች እንጂ ሰላማዊ ባልሆነና ደኅነቷን በማያረጋግጥ ሁኔታ ውስጥ አትገባም፡፡ አህያ ሊመጣ ያለውን ችግር፣ ሥጋትና መከራ ቀድማ የመጠርጠር ጸጋ ተሰጥቷታል፡፡ ከፊት ለፊቷ አደጋ፣ ችግር፣ መከራ፣ ሕይወቷን የሚያሰጋ ነገር መኖሩን ካረጋገጠች ‹ፍንክች የአባ ቢላ ልጅ› ከቆመችበት አትነቃነቅም፡፡ በለዓም እንዲህ አይደል የሆነው፡፡ እርሷ ሰይፍ የመዘዘ መልአክ ታይቷታል፡፡ እርሱ ግን እኛ እንደምናደርገው ‹አህያና ዱላ› እያለ ነረታት፡፡ እርሱ እጁን ደከመው እንጂ አህያዋ ግን ሐሳቧን አልቀየረችም፡፡ አጥኚዎቹ የደረሱበት የአህያ ጠባይ ይሄ ነው፡፡ ደኅንነቷ እስካልተረጋገጠ ድረስ በዱላ ብዛት አህያ ሐሳቧን አትቀይርም፡፡ እኛም ሐሳቧን ከመረዳት ይልቅ ዱላ ይቀናናል፡፡ 

እንዲያውም ሊቃውንቱ እንደሚሉት አህያ ከፈረስ በላይ ታመዛዝናለች፡፡ መጀመሪያ በተሰጣት የመገምገም ችሎታ የአካባቢውን ደኅነት ትገመግማለች፣ ከዚያ ታረጋገጣለች፣ በመጨረሻም ትወስናለች፡፡ እኛ ግን ጥሎብን ይህንን እንድታደርግ ዕድል አንሰጣትም፡፡ መነረት ብቻ ነው፡፡ ለአህያ ግን ከደኅንነት የሚበልጥ ነገር የለም፡፡ የጥንት ሰዎች ‹በፈረስ የሚመጡ ጦረኞች፣ በአህያ የሚጡ ግን ሰላማውያን ናቸው› ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ምክንያቱም አህያ ከፊቷ የደኅንነት ሥጋት እያለ እሺ ብላ አትንቀሳቀስምና፡፡ ክርስቶስም በዕለተ ሆሳዕና ከፈረስ፣ ከበቅሎና ከግመል ይልቅ በአህያ የሄደው ሰላማዊ መሆኑን ሊያበሥር ነው ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡

አህያ ‹ነገር በቀላሉ የማይገባው› ሰው ምሳሌ ሆና ስሟ ጠፍቷል፡፡ አንዱ ማይም ሊቁን ደደብ ብሎ ተሳድቦ ይከሰሳል አሉ፡፡ ዳኞቹ ተሰብስበው ሁለቱን ሲያካስሱ አንደኛው ዳኛ ይጠራሉ፡፡ ለጠሪውም ሰው ‹ጠብቀኝ ስም ተቀያይሮ እያስመለስን ነው› ብለው ላኩበት አሉ፡፡ አሁንም የአህያን ስም የሚያስመልስ ጠፍቶ እንጂ አህያ እንካን ነገር የማይገባት አልነበረችም፡፡ አህያን ማስተማር ግን ፈረስና በቅሎ፣ ውሻና ድመት እንደማስተማር አይደለም፡፡ አህያ ሁለት ነገር ትፈልጋለች፡፡ አንድ አካባቢው ደኅናና ሰላማዊ መሆኑን፣ ሁለት ደግሞ የሚያስተምራት ሰው ለአደጋ የማያጋልጣት፣ ቢቻልም ከአደጋ የሚከላከልላት መሆኑን ማረጋገጥ፡፡ ይህንን ሳታረጋግጥ አህያ ለትምህርት ዝግጁ አትሆንም፡፡ ትምህርቱ የሚያበላ ነው ቢሏትም - መጀመሪያ ራስ ደኅና፣ ልብ ጤና - ትላችኋለች፡፡ ደግሞ ይግረማችሁ ብላ ይህንን በሂደት ነው የምታረጋግጠው፡፡ ቀደማ ባየችውና በሰማችው ነገር ምስጥ ብላ የምትቀር አይደለችም፡፡ ‹አካሄዱን አይታ ጭብጦውን የምትቀማ› ናት፡፡ እንደጀመርከው መጓዝህን፣ እንደተጓዝከው መጨረስህን ማረጋገጥ ትፈልጋለች፡፡ ይበልጥ ባረጋገጠች ቁጥር ይበልጥ የምታዛትን ትቀበልሃለች፡፡ ምን ዋጋ አለው ታድያ፡፡ ይህንን ማን ያውቅላታል፡፡ አልገባትም ብሎ ያልገባው ይነርታታል እንጂ፡፡ ይልቅ አህያ እንደ ብቸኝነት አድርጋ የምትጠላው ነገር የለም፡፡ ካገኘች ከሌሎች አህዮች ጋር፣ ካልቻለች ከፍየሎችም ጋር ቢሆን መኖርን ትመርጣለች፡፡ እንዲያውም አህያ ብቻዋን ከኖረች እድሜዋ በግማሽ ያጥራል ይባላል፡፡ 

መቼም በሀገራችን እንደ አህያና የዝሆን ጆሮ የተቀለደበት ጆሮ የለም፡፡ አህያ ግን በረሐ ውስጥ እስከ 60 ማይል ድረስ የሌላውን አህያ ጩኸት መስማት የምትችል ፍጡር ናት፡፡ ዛሬ ዛሬ ጉርብትና እየጠፋ ጎረቤት ጎረቤቱን መስማት ባቆመበት ዘመን ወዳጁን ከ60 ማይል መስማት ከሚችል ፍጡር በላይ ምን ወዳጅነት አለ፡፡ የአህያ ጆሮ ይህ ብቻ አይደለም ጥቅሙ፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ተናገሩት የተባለውን ነገር የሚያረጋግጥልን ነገርም አለው፡፡ ንጉሡ ወደ ደብረ ዘይት ሲሄዱ የአየር ንብረት ዘገባ በሬዲዮ ይሰማሉ፡፡ ቀኑ ፀሐይ ነው የሚል ነው ትንበያው፡፡ ንጉሡም ይህንን አምነው ወደ ደብረ ዘይት ያመራሉ፡፡ መንገድ ላይ ግን አንድ ገበሬ አህያውን እያስሮጠ ሲሄድ ያዩታል፡፡ ንጉሡም ‹ምነው አህያዋን ታስሮጣታለህ› ይሉታል፡፡ ገበሬውም ‹ዝናብ ሊመጣ ስለሆነ ነው› ይላቸዋል፡፡ ንጉሡም ‹እንዴት ዐወቅህ› ይሉታል፡፡ ገበሬውም ‹አህያዋ ጆሮዋን ጥላለች› ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ገርሟቸው ይሄዳሉ፡፡ እልፍ እንዳሉም የአየር ትንበያው የተናገረው ፀሐይ ቀርቶ ገበሬው የተናገረው ዝናብ መጣ ይባላል፡፡

የአህያ ጆሮ የአየር ንብረትን በተመለከተ ለአህያዋ ሁለት ነገር ይጠቅማታል፡፡ በአንድ በኩል የውስጧን የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታ ለመጠበቅ ሲያገለግላት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢውን የአየር ሁኔታ ገምግማ ርምጃ ለመውሰድ እንድትችል ያግዛታል፡፡ አህያ እንደነፈረስ ዝናብ የሚችል ቆዳ የላትም፡፡ ያላት ዝንብ መምጣቱን ዐውቆ እንድትጠለል የሚመክር ጆሮ ነው፡፡ ከፈጣሪ ካገኘችው አደጋን ቀድማ የመገመት ችሎታ ጋር ተጨምሮ ጆሮዎቿ የአካባቢውን ቀጣይ የአየር ሁኔታ ዐውቃ ሰውነቷን ለማዘጋጀት እንድትችል ያደርጓታል፡፡ የደብረ ዘይቱ ገበሬም ይህንን ነገር ነው የደረሰበት፡፡

ባይሆን አህያ በሆዳምነት መታማቷ እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ አህያ እስከ 40 የሚደርሱ ጨጓራዎች እንዳሏት ስትሰሙ ኡኡ ማለታችሁ አይቀርም፡፡ የአሁኑ ይባስ እንድትሉ ሁለት ነገሮች እንጨምር፡፡ አህያ በእድሜ በገፋች ቁጥር የጨጓራዋን መጠን እየጨመረችው ትሄዳለች፡፡ እድሜ ለዐርባ ጨጓራዎቿ 18 ኪሎ ካሮት እምሽክ ለማድረግ አንድ ሰዓት አይፈጅባትም፡፡ እስካሁን በአህዮች ታሪክ ከፍተኛውን ጨጓራ ያስመዘገበችው የኡዝቤክስታን አህያ ናት፡፡ 59 ጨጓራ አስመዝግባለች፡፡ አንድ አህያ እግዜርን ካልፈራች 2722 ኪሎ ምግብ በዓመት ትፈጃለች፡፡ እንኳን የሸመተ ያረሰም አይችልሽ ማለት አሁን ነው፡፡

የአህያን መሥዋዕትነት ብነግራችሁ ግን ‹ትብላ፣ ደግ አረገች› ትሏታላችሁ፡፡ የአህያ መንጋ የቡድን መሪ አለው፡፡ ጠራጣራዋ አህያ አደጋ ሊመጣ መሆኑን ከጠረጠረች አካባቢዋን ታስሳለች፡፡ ቀጥላም  የአደጋውን አቅጣጫ ታረጋግጣለች፡፡ ከዚያም አደጋው በመጣበት በኩል ራስዋን ታሠማራለች፡፡ በመጨረሻ አደጋውን ትጋፈጣለች፡፡ የአህያ መሪ አደጋውን ስትጋፈጥ ሌሎቹ በቂ ጊዜ አግኝተው ከአካባቢው ይሸሻሉ፡፡ በመሪዋ መሥዋዕትነት ሌሎቹ ይተርፋሉ፡፡ መሪ ማለት እንዲህም አይደል፡፡ ራሱን ሠውቶ ሕዝቡን የሚታደግ፡፡ የአህያ መሪ ይስጠን፡፡

ለሕዝብ ያልታወቀ - ከሕዝብ የራቀ

$
0
0

መቅደላ ላይ ጀግናው ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን የሠዉበትን ቦታ ለማየት ጎብኚዎች ተራራውን ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ እልፍ ብሎ ደግሞ አንድ የመቅደላ ገበሬ በትሩን ተደግፎ ቆሞ የሚሆነውን በአግራሞት ያያል፡፡ ይህንን የታዘበ ጋዜጠኛ ካሜራውን አነጣጥሮ፣ መቅረጸ ድምጹንም ወድሮ ጠጋ አለውና ‹ዐፄ ቴዎድሮስ የተሠዉበት የመቅደላ አካባቢ ነዋሪ በመሆንዎ ምን ይሰማዎታል› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ገበሬውም በትሩን ተደግፎ ባሻገር መቅደላን እያየ ‹ተወኝ ባክህ፤ ካላጣው ቦታ እዚህ መጥቶ ሞቶ እህሌን ያስጠቀጠቅብኛል› አለና መለሰለት ይባላል፡፡
ይሄ ገበሬ በመቅደላ ዙሪያ የሚኖር ገበሬ ነው፡፡ ለእርሱ ከመቅደላ አምባ በላይ የእርሻ ቦታው የመኖርና ያለመኖር ጉዳዩ ነው፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ መቅደላን ለመጎብኘት በመሄዱ ገበሬው ያገኘው ትሩፋት የለም፡፡ እንዲያውም ተጓዡ መንገድ ፍለጋ በእርሻው ላይ ሲሄድ ሲመጣ የሚያደርሰው ጉዳት ያሳስበዋል፡፡ ለእርሱ ያ ሁሉ ወጭ ወራጅ ‹ዓለምኛ› ነው፡፡ ቤሳ ቤስቲኒ ጠብ አያደርግለትም፡፡ ለምን እንደሚወርዱ፣ ለምንስ እንደሚወጡ የነገረው ያለም፡፡ እርሱ የወረዳ ካቢኔ፣ የፓርቲ ካድሬ፣ የዞን መስተዳድር፣ የክልል ባለ ሥልጣን፣ የ‹ወርክ ሾፕ› ተሳታፊ፣ የመስክ ጎብኚ፣ የኮንፈረንስ ተካፋይ አይደለ፡፡ ማን ይነግረዋል፡፡ እርሱ ‹ሕዝብ› ነው፡፡
መብት ዕድልን ካላስቀደመ ዋጋ የለውም፡፡ የማወቅ መብት የማወቅ ዕድልን ማስቀደም አለበት፡፡ ፍትሕ የማግኘት መብት የፍትሕ አካላትን በቅርበትና በነጻነት የማግኘትን ዕድል ማስቀደም አለበት፡፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጥ መብት ነጻና ገለልተኛ ሐሳብ የመግለጫ መንገዶችን በቅርበት የማግኘት መብትን ማስቀደም አለበት፡፡ ትምህርት ቤቶች በሌሉበት የመማር መብት፣ የማምለኪያ ቦታዎች በሌሉበት የማመን መብት፣ አመቺና ተደራሽ የመጓጓዣ መንገዶችና ዘዴዎች በሌሉበት የመዘዋወር መብት፣ ደመና እንጂ ዝናብ አይሆኑም፡፡

የሀገራችን ሰው ‹ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሣት› የሚለው ብሂል አለ፡፡ በጥንቱ ባህል ግብዣ ላይ ቁርጥ ሥጋ ሲቀርብ የሰላ ቢላዋ ከሌለ፣ ሥጋው ለዓይን እንጂ ለሆድ ምግብ ሊሆን አይችልም፡፡ የአዲስ ዓለም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1898 ዓም ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ፈረስ የሚያስጋልብ ዳስ ተጥሎ፣ ሥጋው ቅጠል በተረበረበ አልጋ ላይ ተጋድሞ፣ ተጋባዡ ዓላማ እንዳየ ወታደር ተሰድሮ ይረበረብ ነበር ይባላል፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ የቀረበው ሥጋና የመጣው ቢላዋ አልጣጣም ብሎ ብዙው ተጋባዥ ሥጋ አግኝቶ ቢለዋ ሳይደርሰው ቀረ፡፡
ይህን ያየ ተጋባዥ ‹ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሣት› ሆነበትና የዳሱ ማገር የተሠራበትን ሸንበቆ እየሳበ፣ እንደ ቢላዋ እየጠረበ ሥጋውን ይቆርጠው ጀመር፡፡ ይህንን የተመለከተ ገጣሚ
ብርንዶው ባንድ አልጋ
ጮማውም ባንድ አልጋ
በማገር ይበላል እንዲህ ያለ ሥጋ፡፡ ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡
አንድ ነገር ለሕዝብ ተብሎ መሠራቱ፣ መቅረቡና መገዛቱ ብቻ ጠቃሚ አያደርገውም፡፡ ሕዝቡ ያንን ነገር የሚያውቅበት፣ ዐውቆ የሚወስንበት፣ ወስኖ የሚያስከብርበት ዐቅም እንዲያዳብር መደረግ አለበት፡፡ የሐኪሙ ፍቱን መድኃኒት ከማዘዝ በላይ የበሽተኛው የመድኃኒቱን ጥቅምና አጠቃቀም ተረድቶ መውሰዱ የበለጠ አስፈላጊ ነው፡፡ ደርግ በወደቀ ጊዜ ገበሬው ለምን የገበሬ ማኅበርን ደን እንደቆረጠ አንድ ባለሞያ የተናገሩት እዚህ ላይ ቢጠቀስ ሸጋ ነው፡፡ ‹የዚያ ዘመን አብዮተኞች ሕዝቡ በታሪኩም በተረቱም ሰምቶት የማያውቀውን ኮሙኒዝም የሚባል ዛር አመጡበት፡፡ የት እንዳለ፣ ምን እንደሚመስል፣  ግብሩ ምን እንደሆነ፣ ማርከሻው በምን እንደሆነ የማይታወቅ ዛር ነው ይዘውበት የመጡት፡፡ በሥዕል አያውቀውም፣ በተረት አልተነገረውም፣ በዘፈን አልሰማውም፣ በድርሳንም በተአምርም አንብቦት አያውቅም፡፡ ጠበል ላይም ሲለፈልፍ አልሰማም፡፡ ለዚህ ለማያውቀው ዛር ሲባል ብዙ መከራ ተቀብሏል፡፡ ውትድርና ዘምቷል፣ ዛፍ ተክሏል፣ እርሻ አርሷል፣ መዋጮ ገፍግፏል፡፡ በመጨረሻ ደርግ ሲወድቅ ኮሙኒዝምን ቢፈልግ ቢፈልግ አላገነውም፡፡ ያገኘው ዛፉን ነው፡፡ ዛፉ ኮሙኒዝም መሰለውና ቆረጠው፡፡ የዛፍ መትከልን አስፈላጊነትና ጥቅም ከማስረዳት፣ ከማሳመንና አምኖ እንዲሠራበት ከማድረግ ይልቅ ‹ባይገባውም ዋናው ዛፉ ነው› ተብሎ በቅጣት የተሠራው ሥራ ዛፉ ኮሙኒዝ እንዲሆን አደረገው› ነበር ያሉት፡፡
ማስገደድና ማዘዝ ሥልጣንንና ጉልበትን እንጂ ዐቅምን አያመለክቱም፡፡ በአእምሮ ዐቅማቸው የማይተማመኑ ሁሉ ሐሳብን፣ ዕውቀትንና ተዋሥኦን ይፈሩታል፡፡ ተናግረው እንደማይሰሙ፣ ተንትነው እንደማያሳምኑ፣ ተከራክረው እንደማይረቱ ልባቸው ያውቀዋል፡፡ ስለዚህም ከሰውነት ተርታ ይወርዳሉ፡፡ እንስሳነት ሜዳ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ እንስሳትም ጉልበትና ሥልጣንን ብቻ ይጠቀማሉ፡፡ መመሪያቸው ‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው› ነው፡፡ የዱቄቱ ጥራት ግን እንደተፈጨበት ቦታ እንደሚወሰን አያውቁም፡፡ በሚሸረክት ወፍጮ የተፈጨ ዱቄት እንዴት ዳቦ ይሆናል? ንጽሕና በሌለው ወፍጮ የተፈጨ ዱቄትስ እንዴት ጤና ይሆናል፡፡ ውጤት ያለ ሂደቱ ብቻውን ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡
እስኪ ሁለት ነገሮች እናንሳና የመቅደላውን ገበሬ የሚያስታውሰንን ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ በየስብሰባውም፣ በየሚዲያውም፣ በየሰሌዳውም ‹ዕድገትና የትራንስፎርሜሽ ዕቅድ› ይባላል፡፡ ለመሆኑ ይህ ዕቅድ የት ነው ያለው? እንደ ግማደ መስቀሉ ተቀብሮ? ወይስ እንደ ታቦተ ጽዮን ተሠውሮ? ለመሆኑ ስንት ገጽ አለው? የተጻፈውስ በምን ቋንቋ ነው? ‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅዱን ለማሳካት እንዲህና እንዲያ እናደርጋለን› የሚሉት ሰዎች ምን ያህል አንብበውታል? ምን ያህልስ ተረድተውታል? ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ልባቸውን ሞልተው ደረታቸውን ነፍተው ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅዱ የሚናገሩት ጋዜጠኞችስ እውነት አንብበውታል? አንድ ቅጅስ በእጃቸው ይገኛል? ወይስ ‹ሳያዩ የሚያም› የሚለው ለዚህም ይሠራል? በየመድረኩ የሚያስፎክሩን ሰዎችስ ‹ዕድገት›ና ‹ትራንስፎርሜሽን› ስለሚሉት ሐሳቦች ተመሳሳይ ግንዛቤ አላቸው?
አዲስ አበባ መሪ ዕቅድስ? የዕቅዱ ባለቤት ሕዝብ ነው፤ በዕቅዱ ላይ ከሁለት መቶ ሺ ሕዝብ በላይ ተሳትፎበታል ተብሏል፡፡ ሕዝቡ ግን በእጁ ቅጅው አለው? መጠየቅ ይችላል? በዕቅዱ መሠረት ተፈጽሟል፣ በዕቅዱ መሠረት አልተፈጸመም ለማለት የሚያስችለው መዝገብ በእጁ አለ? በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የሚማሩ ወጣቶች አንብበው ሊረዱት፣ መምህራንም ከዚያ አውጥተው የቤት ሥራ ሊሰጡበት የሚችሉበት ቅጅ አለ?  
በሌላው ዓለም የሆነ እንደሆነ የማወቅ መብትን ለማረጋገጥ እንዲቻል የሚታወቅበት መንገድ ወሳኝ ነውና ‹የሕዝብ ቅጅ (Popular Version)› የሚባል ኅትመት ይዘጋጃል፡፡ የሕዝብ ቅጅ የሚባለው ሞያዊ በሆኑ ቃላት የተሞላውን፣ ውስብስብ የሆነውንና እልፍ በሆኑ ገጾች የተዘጋጀውን መዝገብ ሦስት ነገሮችን አሟልቶ እንዲዘጋጅ ለማድረግ መቻል ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ፣ ዋና ዋና ሐሳቦችንና ጉዳዮችን ይዞ፣ በተመጠኑ ገጾች የሚዘጋጅ ነው የሕዝብ ቅጅ፡፡ የኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚጎድለው አንዱ ዋነኛ ነገር ይሄ ነው፡፡ ዕቅዱ የሚታሰብ እንጂ የሚነበብ አልሆነም፡፡ ዕቅዱ ስለ እርሱ የምንሰማለት እንጂ እርሱን ራሱን የምንሰማው አልሆነም፡፡ ዕቅዱ መኖሩን በእምነት እንጂ በመንካት ልናረጋግጠው አልቻልንም፡፡ ስለ ዕቅዱ እናውቃለን እንጂ ዕቅዱን አናውቀውም፡፡ ለምን?
የሕዝብን የማወቅ መብት የሚያስከብር የሕዝብ የማወቂያ መንገድ አልተዘጋጀምና፡፡ የመቅደላው ገበሬ ከመቅደላ አምባ ይልቅ የእርሱ እርሻ ነገር ያሳሰበው፣ መቅደላ ላይ ምን እየተደረገ እንዳለ የሚነግረው ስላላገኘ ነው፡፡ ለተራራው ቅርብ ቢሆንም ለጉዳዩ ግን እጅግ እንዲርቅ ተደርጓል፡፡ የሁለቱ ሀገራዊ መዛግብት ዕጣ ፈንታም እንዲሁ ነው፡፡ ስለ ፈጣሪ የሚነግሩን ቅዱሳት መጻሕፍት እንኳን ለሕዝብ በሚገባው ቋንቋ በቀላሉ ሕዝብ እጅ እንዲደርሱ፣ ጳጳሱና ምእመኑ፣ ዑለማውና ሙእሚኑ እኩል እንዲጠቅሱዋቸው በተደረገበት ዘመን፤ ለሀገር የወጣ ዕቅድ ምነው እንደ ሰማይ ራቀ፣ እንደ ነፍስ ረቀቀ?  
  


አራቱ መስተፃርራን

$
0
0

click here for pdf 
ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ ሕዝብ የሚሠሩ፣ በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ የማይመስሉ ለመሥራት ተመሥርተው በማፍረስ የተጠመዱ አራት መስተፃርራን አሉ፡፡ እርስ በርሳቸው የሚቀዋወሙ፡፡ አንዱ የሠራውን ሌላው ካላፈረሰ የሠራ የማይመስለው፡፡ ዋና ተልዕኳቸው የሌላውን ማፍረስ እንጂ የራሳቸውን መሥራት ያልሆነ፡፡ መዝገበ ቃላታቸውን - ናደው፣ ደምስሰው፣ አፍርሰው፣ ቆፍረው፣ ጉረደው፣ ቁረጠው፣ ገልብጠው - በሚሉ ቃላት የተሞሉ፡፡
አንድ ነገር ሲያምር ያየሁት እንደሆን
ያንን ካላጠፋሁ ከቶ ምንም ቢሆን
ዕረፍት አላገኝም እንቅልፍ አይወስደኝም
ቅን ነገር አይቼ እኔ አያስችለኝም፡፡ የሚለው መዝሙር ብሔራዊ መዝሙራቸው የሆነ - አራቱ መስተፃርራን፡፡
እነዚህ አራቱስ እነማን ናቸው ቢሉ - ውኃና ፍሳሽ፣ ቴሌ፣ መንገዶች ባለሥልጣንና መብራት ኃይል ይባላሉ፡፡ አንዱ የሌላውን መኖር ቢያውቅም፣ አንዱ ግን ከሌላው ጋር ለመተባበር አይፈልግም፡፡ ወዳጅ እንዳንላቸው የሀገር ሀብት ሲያፈርሱ ምንም አይመስላቸው፤ ጠላት እንዳንላቸው የምንሠራ ለሀገር ነው ይላሉ፡፡   

መንገዶች ባለ ሥልጣን ይመጣና አካባቢውን ቆፍሮ፣ ንዶ፣ ቤት አፍርሶ፣ ዛፍ ገንድሶ፣ አጥር ጠርምሶ፣ ምሶሶ ነቅሎ፣ መንገድ እሠራለሁ ይላል፡፡ የቴሌን ገመድ ሲበጥሰው፣ የውኃውን መሥመር ሲተረትረው፣ የፍሳሹን ቱቦ ሲዘጋው፣ የመብራቱን እንጨት ሲያግድመው ትንኝ የነካ እንኳን አይመስለውም፡፡ አካባቢው ይታመሳል፣ ይተራመሳል፡፡ ለጥቂት ጊዜ ችግሩን ቻሉት እንባልና የአፈር እንጀራ እንበላለን፣ የአቧራ ውኃ እንጠጣለን፡፡ ልክ ጠጠሩ ተደላድሎ አስፓልቱ ሲነጠፍ፣ አካፋና አዷማ የያዙ ጎልማሶች አካባቢውን ይወሩታል፡፡ ያሠምራሉ፣ ይለካሉ፣ ይቆርጣሉ፡፡ ምንድን ነው? ስንላቸው ‹የቴሌ መሥመር ልንዘረጋ ነው› ይሉናል፡፡ ‹እስካሁን የት ነበራችሁ› ያልናቸው እንደሆን መልሱን የሚሰጡን ጉድጓዱን እየቆፈሩ ነው፡፡ ‹የተሠራ ሳናበላሽ፣ የተገነባ ሳንንድ አታውለን› ብለው ጸልየው የመጡ ናቸውና ያሉትን ሳያደርጉ አይመለሱም፡፡ እኛም
የተመኘሁትን አንድ ቀን ሳላይ
ያልፍልኛል ስለው ሊያልፍብኝ ነወይ 
ያለችውን ሴትዮ እንጉርጉሮ እንዳንጎራጎርን እንከርማለን፡፡ የደኻ ምርኩዙ ተስፋ ነውና ቴሌ ጨርሶ ሲሄድ ሠፈራችን ያልፍለታል ብለን ደግሞ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የተሠራውን አስፓልት ንደው፣ የተደለደለውን ጎድጉደው፣ በሬንጁ ምትክ አፈር፣ በአስፓልቱ ምትክ ጠጠር ሞልተው፣ የአህያ ሻኛ ቁስል የመሰለ የአስፓልት ላይ ቁስል ትተው ቴሌዎች ይሄዳሉ፡፡ እኛም
ለማይሰማው ስልክ ለሚቆራረጠው
እንደ ገላውዴዎስ መንገዴን ቆረጠው
እያልን እያዜምን እንቀራለን፡፡ እንደ ገላውዴዎስ የተባሉት ዐፄ ገላውዴዎስ ናቸው፡፡ መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም. ሐረር አካባቢ ከሐረሩ አሚር ከኑር መሐመድ ጦር ጋር በተደረገ ጦርነት ዐፄ ገላውዴዎስ ተገደሉ፡፡ ራሳቸውንም ቆርጠው ወደ ሐረር ከተማ ወሰዷቸው፡፡ 
ቴሌ በቆፈረው ጉድጓድ እየተንገጫገጭን፣ ጉድጓዱ በያዘው ውኃም እየተንቦራጨቅን ኑሯችንን ስንገፋ፡፡ ሦስተኛው ፀር ይመጣል፡፡ ‹መንገዱ የፍሳሽ ማስወገጃ የለውም፤ አሮጌውም የውኃ መሥመር ይቀየራል› የሚል መፈክር ያሰማል፡፡ ምነው ሲሆን መንገዱ ሳይሠራ፣ ካልሆነም ቴሌ ሲቆፍረው አትመጡም ወይ? ያልናቸው እንደሆን ‹እኛ በወንድነት ከነማን አንሰን ነው ሌላ በቆፈረው ጉድጓድ የምንሠራ፡፡ እኛም የራሳችን ቆፋሪ ክፍል አለን፣ የመቆፈሪያ በጀት አለን፣ የማስቆፈሪያ አበል አለን፡፡ እጃችን ሙቅ ይዟል እንዴ? እንንደዋለን እንጂ፡፡ እንኳን ይኼንን ኮረትና አፈር የለበሰ ጉድጓድ፣ ምን የመሰለውን  አውራ አስፓልትም ዕጢ እንደሚወጣለት ሆድ ስንተረትረው ባያችሁ› ይሉናል፡፡
ገና እናፈርሳለን
ገና እንንዳለን
በጀት እስካስፈቀድን፣ ዕቅድ እስካወጣን
ገና እንቆፍራለን፣ ገና እናፈርሳለን፡፡
የሚለውን መዝሙር እያቀነቀኑ ያን የፈረደበት አስፓልት ይተረትሩታል፡፡ አማርኛ የሚናገሩ ደርቡሾች፡፡ ስትፈርስ ስትሠራ የምትኖር አገር ናት፣ መቼም ፈርዶባታል ብለን እኛም ዝም አልን፡፡ ዝምታችንም እንደፍርሃት ስለተቆጠረ ሦስቱ ጨረሱና አራተኛው መጣ፡፡ ‹ለአዲሱ መንገድ የኤሌክትሪክ ምሶሶ እንተክላለን› የሚሉ አፍራሾች መቆፈሪያቸውን እንደሳንጃ ወድረው፣ አካፋቸውን እንደ ጦር አሹለው አሰፈሰፉ፡፡ የተስተካከለውን የእግረኛ መንገድ እንደተጣመመ ጥርስ እየነቀሉ፣ የተደላደለውን ጎዳና እንደ ወርቅ ፈላጊ እየፈነቀሉ የበልግ እርሻ አስመሰሉት፡፡ ይባስ ብለው ወደ ምሶሶ የሚገባው የኤሌክትሪክ ገመድ እንደ ፈልፈል በምድር ውስጥ ነውና የሚሄደው እኛም በተራችን መንገድ እንቆርጣለን - አሉና ተነሡ፡፡ እኛም
በመንደሩ መሐል አንድ ዋርካ ቢኖር
ያም መጥቶ ያም መጥቶ ይፈልጠው ጀመር
የሚለውን ነጠላ ዜማ ለቀቅን፡፡ ሠፈራችንን ከመልቀቅ ነጠላ ዜማ መልቀቅ ይሻላል ብለን፡፡ ይኼው ከተማችንም አራቱ መስተፃርራን እንደ አራቱ ወቅቶች እየተፈራረቁ ሲያፈርሷት፣ እርሷም ሳያልፍላት እኛም ሳያልፍልን እንኖራለን፡፡ በዚህ የጠላትነት አዙሪት ውስጥ መግባታችን የሚታወቀው ደግሞ ውኃና ፍሳሽ የዘረጋውን፣ መብራት ኃይል የቀበረውን፣ ቴሌ የደለደለውን መንገዶች ባለ ሥልጣን እንደገና አፈርሰዋለሁ ብሎ መነሣቱን ስናይ ነው፡፡ መንገዱ ይሰፋል፣ ደረጃው ይሻሻላል ብሎ ባልተወለደ አንጀቱ ያ ሁሉ ብር የፈሰሰበትን አስፋልት ጅብ እንዳገኘው የአህያ ሆድ ዘረገፈው፡፡   
የአቦላን ተራራ ያክላል ጡትሽ
ወይ ባል አላገባሽ ወይ አልመነኮስሽ
እንዴው ልጃገረድ ይባላል ስምሽ
እንዳለው ክራር ገራፊ፡፡ ከተማችንም ገጠር አይሏት ሕንጻዎቿ እንደ ጡት አጎጥጉጠው፤ ወይ ሁነኛ የመንግሥት ባል አላገባች፣ ወይ እንደ ፈረሰች ከተማ ጨርሶ አልመነኮሰች - እንደ መንደር ምግብ ቤት ድስት አሥር ጊዜ ስትወጠወጥ ትኖራለች፡፡ የሀገሬ ህዳሴ የሚጀምረው መቼ ነው ብለው ለሚጠይቁ - መልሱ - እነዚህ አራቱ መስተፃርራን የታረቁ ጊዜ ነው፡፡  
         

ድስትና ሰሐን

$
0
0

 click here for pdf
እሳቱን ግር አድርገው አንድደው ይለበልቡታል፡፡ ዕዳው የጀመረው ‹ትንሽ እሳት ይስማው› ብለው የጣዱት ጊዜ ነው፡፡ እሳቱ ሞቅ ሲያደርገው ሽንኩርቱን አቀመሱት፡፡ ሽንኩርቱ ብቻውን አልመጣም፡፡ ወደል ማማሰያ ይዞ እንጂ፡፡ ባልተወለደ አንጀቱ ሆዱን ያተራምስለት ገባ፡፡ አንዴ እያማሰለ፤ አንዴም ሆዱን እየፋቀ የክብደት አንሽ እግር የሚያህለው ማማሰያ  ድስቱን ይፈቀፍቀዋል፡፡ ሽንኩርቱ አጋም ሲመስል ደግሞ ውኃውን ቸለስ አደረጉበት፡፡ እፎይ አለ ድስቱ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው እፎይታው የዘለቀው እስኪንፈቀፈቅ ድረስ ብቻ ነው፡፡
የድስቱ ዙሪያ መጀመሪያ ጠቆረ፣ ቀጥሎም ጥላሸት ተቀባ፡፡ በመጨረሻም ራሱ ከሰለ፡፡ ሁለቱ ጆሮዎቹ ከሥሩ የሚነደውን ገሞራ እያዩ ‹ማርያም ማርያም› ይላሉ፡፡ ሥጋው ከገባበት በኋላማ ከሥሩ ማገዶውን፣ ከሆዱ ማማሰሉን እያከታተሉ ስቃዩን አበዙት፡፡ ደግሞ የጉልቻው መከራ፡፡ ይቆረቁራል፡፡ ‹‹የእናት ሞትና የድንጋይ መቀመጫ እየቆዩ ይቆረቁራል›› እንዲሉ በአንድ በኩል የድንጋዩ ጉብጠት፣ በሌላ በኩል የድንጋዩ ትኩሳት፣ እንኳን ለመቀመጫነት ለሲኦልነት እንኳን ሲበዛበት ነው፡፡
ለአራት ሰዓታት ያህል በውስጥ በአፍኣ አሳሩን ሲበላ ቆይቶ እዚያው ምድጃው ላይ ተዉት፡፡ እርሱም ተንፈቅፍቆ - ተንፈቅፍቆ፣ በመጨረሻ በክዳኑ በኩል ትንፋሹ እያወጣ ያንኮራፋ ጀመር፡፡ እሳቱም እየደከመውና ዓይኑ እየተስለመለመ ሄዶ አሸለበ፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ቆይተን የዚህን ድስት መጨረሻ እናያለን ያሉ ጉማጆች የዐመድ ሻሽ ለብሰው፣ ዓይናቸውን ከፈት ከደን እያደረጉ ሙቀቱ ጨርሶ እንዳይጠፋ አድርገውታል፡፡ ጉልቻውም ዋናው እሳት የተወውን እኔ ‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ› አልሆንም ብሎ መቀዝቀዝ ጀምሯል፡፡ 

ድስቱ ግን ዕንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም፡፡ ኳ - ኳኳ - ቂው - ቂው ቂው - ቻ - ቻቻ - የሚል ድምጽ ማዕድ ቤቱን ሞላው፡፡ እዚህና እዚያ የሚጣደፉ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ይወጣሉ፤ ይገባሉ፡፡ ይከራከራሉ፤ ይነታረካሉ፡፡ ድስቱን ረበሸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ድካሙ ስለበረታበት ክዳኑን አናቱ ላይ ጣል አድርጎ ሸለብ ማድረግ ሲጀምር - ኳ - የሚል የቅርብ ድምጽ ሰማ፡፡ ይበልጥ ያነቃው ደግሞ - ኳ - የሚለው ድምጽ እዚያው ድስቱ አካባቢ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡
የድስቱ ክዳን ተነሣ፡፡ ‹እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል› እንዲሉ ለአራት ሰዓታት ያህል ያሰቃየው እሳት ደግሞ ሊመለስ ነው ብሎ ሰቀጠጠው፡፡ ግድንግዱ ማማሰያ መጥቶ ሊወቅጠኝ ነው ብሎ ሲጠብቅ አንዲት አንገቷ የሰለለ፣ አናቷ የሞለለ ጭልፋ ቀጫ ቀንቧ እያለች ስትመጣ ታየች፡፡ ‹ይቺ ደግሞ ምንድን ናት?› አለ ድስቱ፡፡ የሚገርመው ነገር ብቻዋን አልነበረችም፡፡ ሁለት ድንቡሽ ያሉ ወጣት ሴቶች አንዲት እንደነርሱ ድንቡሽ ያለች ሰሐን ይዘዋል፡፡ ዙሪያዋን በአበባ ምስል ተጊጣለች፡፡ ሁለመናዋ ነጭ ነው፡፡ አንድም የቆሸሸ ነገር አይታይባትም፡፡ እንዲያውም ከሁለቱ ወጣት ሴቶች ጀርባ ፎጣ ይዛ አንዲት ልጅ ትከተል ነበር፡፡  ያቺ ሰሐን አንዳች ነገር ጠብ ሲልባት ፈጠን ብላ ጠረግ ታደርግላታለች፡፡ 

ጭልፋዋ ወደ ወጡ ጎንበስ ስትል ድንገት አንዲት ፍንጣቂ ዘልላ ሰሐኗ ላይ ዐረፈች፡፡ ያቺ እንደ ደንገጡር ከኋላ የምትከተል ወጣት እንደ ጀት ፈጥና በያዘችው ፎጣ ጥርግ አደረገችላት፡፡ ድስቱ ተገረመ፡፡ አራት ሰዓት ሙሉ ሲንፈቀፈቅ፣ ከታች የሚመጣ እሳት፣ ከውስጥ የሚፈነጥቅ ወጥ እንዲያ ጥቁርና ቀይ ሲያደርገው ዘወር ብሎ ያየው የለም፡፡ ጠቁሮ - ጠልሽቶ -ከስሎ -  እንኳን ሌላ ራሱ ድስቱ ራሱን እስኪረሳው ድረስ - ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነ፡፡ ያን ጊዜ ቀርቶ ወጡ በስሎ ሲያልቅ እንኳን ልጥረግህ፣ ልወልውልህ ያለው የለም - አየ ድስት መሆን፡፡
‹ደግሞ አንቺ ማነሽ?› አላት ድስት በሁለት ቆነጃጅት እጆች የተያዘችውን ሰሐን፡፡
‹የወጥ ማቅረቢያ ሰሐን ነኝ› አለችው ፈገግ እያለች፡፡
‹ምን ልታደርጊ መጣሽ?› አለ ከዚህ በፊት እዚያ አካባቢ አይቷት አያውቅም፡፡
‹ለእንግዶቹ ወጥ ልወስድ ነው› አለች የወጡ ፍንጣቂ እንዳይነካት ፈንጠር እያለች፡፡
‹ማን የሠራውን ማን ያቀርበዋል?› አለ ድስት እንደመፎከር ብሎ፡፡
‹ድስቶች ለፍተው የሠሩትን ሰሐኖች ተዉበው ያቀርቡታል› አለችውና ፍልቅ ብላ ሳቀች፡፡
‹የት ነበርሽ አንቺ ለመሆኑ? እሳት ከሥር፣ ማማሰያ ከላይ ሲኦል እንደገባ ኃጥእ ሲያሰቃዩኝ? ለመሆኑ ሽኩርቱ ሲቁላላ፣ ቅመሙ ሲዋሐድ፣ ሥጋው ሲወጠወጥ፣ ጨው ጣል ሲደረግ፣ ማማሰያው ሆዴን ሲያተራምሰው - ለመሆኑ አንቺ የት ነበርሽ? የመሥዋዕቱ ጊዜ የት ነበርሽ፣ የመከራው ጊዜ የት ነበርሽ፣ የችግሩ ጊዜ የት ነበርሽ፣ ሽንኩርቱ፣ ቅመሙ፣ ቅቤው፣ ሥጋው መልክና ስማቸውን ቀይረው ‹ወጥ› እስኪባሉ ድረስ የት ነበርሽ? አሁን ወጥ ሆኑ ሲባል ነው የምትመጭው› አላት ድስቱ ከጉልቻው ላይ እየተወዛወዘ፡፡
‹ስማ ድስቱ› አለችው ሰሐኗ፡፡ ‹ዋናው መሥዋዕትነቱ አይደለም፡፡ አቀራረቡ ነው፡፡ ሰውኮ ድስቱን ሳይሆን ወጡን ነው የሚፈልገው፡፡ ወጡ ደግሞ በእኛ በኩል ነው የሚቀርበው፡፡ በድስት ይሠራ፣ በበርሜል ይሠራ፣ በገንዳ ይሠራ፣ በጉድጓድ ይሠራ ማን ያይልሃል፡፡ ተጋባዦቹምኮ አዳራሹን እንጂ ማዕድ ቤቱን አያዩትም፡፡ ለመሆኑ ምግብ ቤት ገብቶ ‹አስተናጋጇ በደንብ አላስተናገደችኝም› የሚል እንጂ ‹ወጥ ሠሪዋ በሚገባ ለብሳ፣ ጤናዋን ጠብቃ፣ ከአደጋ የሚከላከል ልብስ አጥልቃ፣ አካባቢዋን አጽድታ አልሠራችውም› ብሎ የሚያማርር ተስተናጋጅ ሰምተህ ታውቃለህ? ወዳጄ ዘመኑ ለድስቶች ሳይሆን ለሰሐኖች ነው ዋጋ የሚሰጠው›› አለችው፡፡
ድስቱ አልተዋጠለትም፡፡ በተለይ ደግሞ አራት ሰዓት ሙሉ ከሥር ከላይ የከፈለውን መሥዋዕትነት ሲያስበው - እንኳን ሊዋጥለት፣ ሊጎረስለት አልቻለም፡፡
የለፋነው እኛ፣ የነደድነው እኛ፣ የተማሰልነው እኛ፤ መከራውን የቀመስነው እኛ - ለመሆኑ ከየት የመጣ ወጥ ነው ብሎ ነው ተጋባዡ የሚያስበው? ለመሆኑ ያለ አኛ እናንተ መኖር ትችሉ ነበር? ያንቺ ውበት የኔ መቃጠል ውጤት አይደለም? አንቺ በሁለት እልፍኝ አስከልካዮችና በአንዲት ደንገጡር እንድትከበቢ ያደረግንሽ እኛ አይደለንም? እኔና የወጥ ማማሰያ የከፈልነው መሥዋዕትነት እንዴት ቢረሳ ነው አንቺና ጭልፋ በመጨረሻ መጥታችሁ የምትሽረቀሩት››
ሁለቱ ሴቶች ወጡን እያወጡ ወደ ሰሐኗ ሲጨምሩ - ‹ስማ› አለቺው ሰሐኗ ‹አንተ የተናገርከው እውነቱን ነው፡፡ እኔ የምነግርህ የሚያዋጣውን ነው፡፡በዚህ ዘመን በሚፈለገውና በሚያስፈልገው መካከል ልዩነት መፈጠሩን አልሰማህም መሰል፡፡ በዚህ ዘመን ማራቶኑን የምትፈልገው ለጤና ከሆነ ዐርባ ሁለቱን ኪሎ ሜትር ሩጥ፤ ማራቶኑን የምትፈልገው ለሽልማቱ ከሆነ ግን ዐርባውን ሌሎች ይሩጡልህ፣ አንተ ግን ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀር ገብተህ ቅደም፡፡ ያን ጊዜ ልፋቱን ሌላው ይለፋል -ሽልማቱን አንተ ትወስዳለህ፡፡ እስኪ ለሀገራቸው ዋጋ የከፈሉትን፣ የተሠዉትን፣ የሞቱትን፣ የደከሙትንና ሀገሪቱን ሀገር ያደረጉትን አስባቸው፡፡ ምን አገኙ? እነርሱ እንዳንተ ማዕድ ቤት ውስጥ ተረስተው  ቀርተዋል፡፡ ስለ እነርሱ የሚደሰኩረውና የሚተርከው ግን ዛሬ የት ነው ያለው? ዘመኑ የዐርበኞች ሳይሆን የድል አጥቢያ ዐርበኞች ነው፡፡››
ይህንን ስትነግረው ወጡ ተጠቃልሎ ወጥቶ ደንገጡሯ የተፈናጠቀውን እየጠረገች ነበር፡፡ በድስቱ ክዳን አናት ላይ ባለችው ቀዳዳ አበባ ተደረገባት፡፡ ሰሐንዋን የያዘችው ወጣት ለሌላዋ ወጣት ስትሰጣት እንደ አራስ ልጅ በባለ አበባ ጨርቅ አደግድጋ ተቀበለቻት፡፡ ጭልፋ የያዘችው ወጣት ከፊት እንደ እልፍኝ አስከልካይ እየመራች፣ ፎጣ የያዘችው ወጣት እንደ ደንገጡር እየተከተለች አጅባት ሄደች፡፡ ድስቱም ‹እዚህ ሀገር እንደ ጠረጲዛ አበባ ፊት  ሆኖ የሚታየውን እንጂ፣ እንደ ጄነሬተር ከኋላ ሆኖ የሚሠራውን የሚያየውና የሚያከብረው የለም ማለት ነው?›› አለ፡፡ ይህን ሲናገር ሁለት ወጠምሻ ጎረምሶች መጥተው ከጉልቻው አውጥተው ድስቱን ዐመድ ላይ ጣሉት፡፡
  

አምስተኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር

$
0
0

የበጎ ሰው  ሽልማት
የዜና መግለጫ
አምስተኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር
የእጩዎች ጥቆማ ግንቦት 16 ይጀመራል
ላለፉት አራት ዓመታት ለሀገርና ለሕዝብ አርአያነት ያለው ታላቅ ተግባር ያከናወኑ ሰዎችን ዕውቅና የሚሰጠው የበጎ ሰው ሽልማት አምስተኛው መርሐ ግብሩን ከነገ ግንቦት 16 ቀን አንስቶ የእጩዎች ጥቆማ በመቀበል በይፋ ይጀምራል፡፡
ለዚህ የሽልማት መርሐ ግብር በአስር ዘርፎች ማለትም
1.መምህርነት
2.ንግድና ሥራ ፈጠራ
3.ማኅበራዊ ጥናት
4.ሳይንስ
5.ቅርስና ባሕል
6.መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት
7.ለኢትዮጵያ የላቀ አስተዋጽዖ ያደረጉ የውጭ ሀገር ዜጎች
8.ኪነ ጥበብ (በቴአትር ጥበባት)
9.ሚዲያና ጋዜጠኛነት
10.በጎ አድራጎት ከህዝብ የእጩዎችን ጥቆማ ለመቀበል ተዘጋጅተናል፡፡

ባለፉት አራት የሽልማት ወቅቶች፤ አገራችን የምትኮራባቸውና የላቀ አርአያነት ያለው ተግባር ያከናወኑ ሰዎችን እውቅና የሰጠነው ከህዝብ በቀረቡ ጥቆማዎች መሰረት ነው፡፡ የበጎ ሰው ሽልማትን ለዚህ ያበቃውም በሽልማቱ ሂደት የህዝብ ተሳትፎ በመኖሩና ይህም ከዓመት ዓመት እያደገ በመሄዱ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን፡፡ ይህ ተሳትፎ አሁንም እንደሚቀጥል ጽኑ እምነት አለን፡፡   
የበጎ ሰው ሽልማት ዓላማ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ መልካም የሚሠሩ፣ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን በብቃትና በልዩ ልዕልና የሚወጡ፣ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ለውጥ አምጪ ተግባር የፈጸሙ፤ በብዙ ሰዎች የማይደፈረውን ተግባር በተነሣሽነት የከወኑ፣ ለድጋፍ ፈላጊ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነት ወስደው የሠሩ፣ የሀገሪቱ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል፣ እንዲጠበቅ፣  የሀገሪቱ  ሥልጣኔ  ከፍ  እንዲል  የሠሩ  ኢትዮጵያውያንን  በማበረታታት፣  ዕውቅና  በመስጠትና በመሸለም ሌሎችን በጎ ሠሪዎች ለሀገራችን ማፍራት ነው፡፡
ስለዚህ ይህን የበጎ ሰው ሽልማትን ዓላማ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከላይ በተገለጹት መስኮች ከግንቦት 16 እስከ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ህዝቡ ለዚህ ሽልማት ብቁ ናቸው የሚላቸውን እጩዎች እንዲጠቁም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ጥቆማ የምንቀበለው በስልክ፣ በኢሜይልና በፖስታ ነው፡፡ አድራሻዎቹም፤
1.ስልክ፡- 0960402990
2.ኢሜይል፡ begosew2009@gmail.com
3.ፖስታ፡ 150035 አዲስ አበባ
4.በአካል ለሚመጡ፡- ለም ሆቴል፣ ማትያስ ሕንጻ፣ ቢሮ ቁጥር 408
ጠቋሚዎች እጩዎችን በሚጠቁሙበት ጊዜ ዕጩው ግለሰብ ለአገርና ለሕዝብ ያከናወኑትን ተግባር በዝርዝር እንዲገልጹልንና የሚገኙበትንም አድራሻ እንዲጠቁሙን እንጠይቃለን፡፡ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ለመጨረሻው ውድድር ተመርጠው ስማቸው ለዳኞች የሚላከውን ዕጩዎች ማንነት ሕዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ፤ ዐውቆም ለሀገርና ለሕዝብ ባበረከቱት አስተዋጽዖ እንዲያከብራቸው ለማድረግ ዝርዝራቸውን በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ይፋ እናደርጋለን፡፡  
የመጨረሻውን የየዘርፎቹን የበጎ ሰው ተሸላሚ ምርጫ የሚያደርጉት ለእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ በዳኝነት የተመረጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ዳኞቹ በዕውቀታቸውና በሙያቸው አንቱ የተባሉ፣ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በታማኝነት ምርጫውን ያከናውናሉ ተብለው የታመነባቸው ናቸው፡፡ ለእያንዳንዱ ዘርፍም ሦስት ዳኞች ተመርጠው ምርጫውን ያከናውናሉ፡፡ 
አምስተኛው የበጎ ሰው ሽልማት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ 
የሕዝቡ የመምረጫ መመዘኛዎች
1. ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝቦች መቀራረብና መደጋገፍ፣ ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣
2. በበጎ አድራጎትና ሰብአዊ ተግባራት ተሠማርተው የሰው ልጅን ሕይወት የለወጡ፣
3. በሥነ ጽሑፍ፣ በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጥበብና በመሳሰሉት መስኮች ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ፣ የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን ሥነ ጥበብ ወደ አንድ የላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ሥራዎች የሠሩ፣
4. በግብርና፣ በቢዝነስ፣ በኢንዱስትሪና በመሳሰሉት መስኮች አዲስ፣ የራሱ ወጥነት ያለውና ያልተደፈረ የሚመስለውን ሥራ ያከናወኑ፣ ለሀገሪቱ ዕድገትና ሥልጣኔም ለውጥ አምጭ አስተዋጽዖ ያደረጉ፣
5. በጋዜጠኛነት መስክ ተሠማርተው ሙያውን የጠበቀ፣ ለሌሎች አርአያ የሚሆን፣ የሕዝቡን ኑሮ የሚለውጥ ሥራ ያከናወኑ፣
6. በዲፕሎማሲው መስክ የሀገሪቱን ክብርና ደረጃ ያስጠበቁ፣ የሀገሪቱንም መብት ያስከበሩ፣
7. በመንግሥትና በሥራ ተቋሞቻቸው የተሰጧቸውን የተለያዩ ሀገራዊ ግዳጆችን በብቃት የተወጡ፣ መሥዋዕትነት የሚጠይቁ ተልዕኮዎችን ያከናወኑ፣ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ ብቁ አመራሮችን የሰጡ፣ በአመራሮቻቸውም ድርጅታቸውንና መሥሪያ ቤቶቻቸውን የለወጡ፣
8. ሀገራዊ ዕውቀቶችን በማስተማር፣ ቅርሶችንና ባህልን በማስጠበቅና በመከባከብ ለውጥ አምጭ ተግባር ያከናወኑ፣
9. በጥናትና ምርምር መስክ ተሠማርተው ችግር ፈች የሆኑ ውጤቶችን ያስመዘገቡ፣
10. በማስታረቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ ሀገራዊ የሽምግልና ሥራ የሠሩ፣
11. በሌሎችም መስኮች የሚጠቀስ፣ ለሀገር የሚጠቅም፣ ለትውልድ አርአያነት ያለው፣ የሀገርን ክብር የሚጨምር፣ ታሪክና ማንነትን የሚያጎላ ተግባር ያከናወኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ይጠቁሙ፤


በጎ ሠሪዎችን በማክበርና በመሸለም ሌሎች በጎ ሠሪዎችን እናፍራ

ለበለጠ መረጃ ይደውሉ፡ ዳንኤል ክብረት - 0911-474503  ወይም ነጻነት ተስፋዬ - 0911485961                                                         

የበጎ ሰው ሽልማት አስተባባሪ ኮሚቴ

 

የመርሕ ጥያቄ

$
0
0





ሰሞኑን ዶክተር አባ ኃይለ ማርያም ኦርቶዶክሳውያን ካልሆኑ አካላት ጋር ያከናወኑትን ‹የጠበልና እምነት› ጉዳይ በተመለከተ አያሌ ጥያቄዎች ሲነሡ ነበር፡፡ ነገሩን ከየምንጮቹ ብሰማቸውም በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን የነበረው የቂሣርያው ገዥ ፊስጦስ ‹ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም፣ ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጥ የሮማውያን ሥርዓት አይደለም› (የሓዋ.25፣16) ብሎ የተናገረውን መሠረት በማድረግ አባ ኃይለ ማርያም ለጉዳዩ የሚሰጡትን መልስና ማብራሪያ ጠብቄ ነበር፡፡ መልስና ማብራሪያውንም ሰጡ፡፡
አባ የድርጊቱን መከናወን አምነው የክንውኑን ዓይነት ከተወራው የተለየ መሆኑን አብራሩልን፡፡
መልሳቸውን ስናጠቃልለው፡-
1.      መርሐ ግብሩ ‹ውኃ ለሁሉም› በሚል መርሕ እንደተዘጋጀ
2.     ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳት እንደተገኙበት
3.     ተበጥብጦ ከመጣው ውኃና እምነት ጠቅሰው በተሳታፊዎቹ ግንባር ላይ ምልክት አንዳደረጉ
4.     ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጂ አንዳልቀባቸው
መርሐ ግብሩ ‹ውኃ ለሁሉም በፍትሐዊነት እንዲዳረስ› ከሆነ እንዴት ነው እምነትና ውኃ በመበጥበጥ ውኃ ለሁሉም ሊዳረስ የሚችለው፡፡ ‹ውኃ ለሁሉም› የሚለው ጉዳይ የዐውደ ጥናት፣ የምክክርና ምናልባትም የጸሎት ርእስ ሊሆን ይችላል እንጂ እምነትን በውኃ በጥብጦ በመቀባት ‹ውኃ ለሁሉም› እንዴት ለማዳረስ  ይቻላል? እምነት በውኃ በጥብጦ መቀባት ለፈውስ ያገለግላል እንጂ እንዴት ከውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ጋር ተገናኘ? ደግሞስ እኛ ከሌሎች እምነቶች ጋር አንድነታችንን ማምጣት ያለብን በክርስቶስ እንጂ እምነት በውኃ በመበጥበጥ ነው እንዴ?  

አባ ኃይለ ማርያም በሰውዬው (የሌላ አምነት መሪ መሆኑ ከፎቶውና ከመረጃው ይታወቃል) ግንባር ላይ ሲቀቡት ምን እንዲያደርግ አስበው ነው? እንዲፈወስ የቀረበ በሽተኛ ነው? ለበረከት የመጣ ደጅ ጠኚ ነው? እንዴትስ ነው የተበጠበጠው እምነት ከ‹ ውኃ ለሁሉም› አስተሳሰብ ጋር የሚሄደው?
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ‹ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጂ አልቀባኝም› ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹ ሁሉ የሚያሳዩት ግን ሲቀባዎት ነው፡፡ ደግሞስ ሰውዬው ለመቀባት ካላሰበ እጁን ለምን ወደ እርስዎ ያስጠጋል? ሊባርክዎ ነው? አስቀድማችሁ የተስማማችሁበት ሥነ ሥርዓት ይህንን የማይፈቅድ ከሆነስ እንዴት እጁን ወደ እርስዎ አስጠጋ? ‹እጁን አስጠግቶ ነበር› ካሉን ደግሞ ከተበጠበጠው እምነት እንደ እርስዎ ጠቅሶ ነበር ማለትዎ ነው? ለመሆኑ ኦርቶዶክሳዊ ክህነት የሌለው ሰው ከእምነት ጠቅሶ ሌላውን ሰው መቀባት፣ ያውም ቆሞሱን ይችላልን?
ሥነ ሥርዓቱ ሲከናወን ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደነበሩ አባም ነግረውናል፣ ፎቶውም አሳይቶናል፡፡ ምን ወስነው? ምን ሊያደርጉ ሄዱ? ውኃ ለሁሉ እንዲዳረስ ሊጸልዩ ወይስ ውኃ ለሁሉ እንዲዳረስ እምነት በውኃ ሊበጠብጡ? ለመሆኑ ይህንን እንዲያደርጉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይፈቅድላቸዋል? ወይስ ሥልጣን ከቀኖና ስለሚበልጥ?

አባን ለዚህ ሁሉ ነገር የዳረጋቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መርሕ እየተጣሰ ስለመጣ ነው፡፡ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን እናንሳ፡-
ቤተ ክርስቲያናችን ኢኩሜኒካል ግንኙነትን የምትመራበት ፖሊሲና ደንብ አላት?
ቤተ ክርስቲያናችን ኢኩሜኒካል ግንኙነቶችን የምታከናውንበት ተቋምስ አላት?
የሁለቱም መልስ የላትም የሚል ነው፡፡ በሌሎች እኅት አብያተ ክርስቲያናት የኢኩሜኒካል ግንኙነትን የተመለከተ ፖሊሲና ደንብ ሲኖዶሱ ያጸድቃል፡፡ ከነማን ጋር ምን ዓይነት ውይይት ይደረጋል፣ ምን ዓይነት ውይይቶች በምን ደረጃ (በሊቃውንት፣ በጳጳሳት) ይደረጋሉ፣ ስምምነቶች እንዴት ይጸድቃሉ፣ የጸደቁት እንዴት ለሕዝብ ይገለጣሉ፣ የጸደቁትን እንዴት መተግበርና መከታተል ይቻላል፣ ስምምነት እስኪደረስ ድረስ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነቶች ይኖሩናል? በምን በምን እንተባበራለን? በየደረጃው ያሉ አካላት (ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምእመናን) ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው፣ የሚሉትን የሚወስን የፖሊሲ መዝገብ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ይህ ፖሊሲ የላትም፡፡ ፖሊሲውንም መሠረት አድርጋ የምትመራበትን ሕግ አላጸደቀችም፡፡ ስብሰባ ስትጠራ መሄድ ብቻ ነው፡፡
በሌላ በኩልም የኢኩሜኒካል ግንኙነትን የሚያካሂድ፣ ባለሞያዎችን የሚሰባስብ፣ መረጃዎችን የሚመዘግብ፣ በዓለም ላይ የሚደረጉ የኢኩሜኒካል ግንኙነቶችን የሚከታተል፣ ግንኙነቶቹን በፖሊሲውና በደንቡ መሠረት የሚመራ፣ ስሕተቶች ሲፈጠሩም የሚያርም ተቋምም የለም፡፡ ያለው የውጭ ግንኙነት መምሪያ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ብዙ ጊዜ እንግሊዝኛ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታሰብ አሜሪካ በኖሩ ሰዎች የሚመራ ነው፡፡ የኢኩሜኒካል ግንኙነት ግን የአሜሪካን እንግሊዝኛ በመቻል ብቻ የሚሠራ አልነበረም፡፡ የውጭ ግንኙነት መምሪያው ወደ ውጭ ለሚሄዱ ሰዎች ሂደቶቻቸውን መከታተል፣ ከውጭ አጥቢያዎች ጋር ‹መገናኘት› የሚላኩ ሰዎችን መላክ እንጂ ራሱ እንኳን የሚመራበት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያለው አይመስልም፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ አባ ኃይለ ማርያም ያንን ነገር ቢያደርጉት የሚገርም አይደለም፡፡  ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በዕለቱ የነበሩት ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን መርሕ እየጣሱ ያዘዟቸውን ነው የተገበሩት፡፡ እርሳቸው ቢሆኑም ግን  ፖሊሲና ሕግ በሌለበት ይህንን ተግባር ከሚያከናውኑ ‹ዱክትርናቸውን› ተጠቅመው ፖሊሲውና ሕጉ እንዲዘጋጅ ቢያደርጉ ኖሮ ይመሰገኑ ነበር፡፡ ነገ ጳጳስ የሚሆኑትን አባት ማንም እየተነሣ እጁን ወደ ግንባራቸው አይልክም ነበር፡፡ በሃይማት መሥመር የበላይ ያመጣውን ሁሉ በእምነት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የበላይ አዞኝ ነው ብሎ ቀኖና መጣስና እምነት ማፋለስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በጉባኤ ኬልቄዶን የክህደቱን ውሳኔ አልቀበልም ያለው ዲዮስቆሮስ በሮም ቤተ መንግሥት ተጠርቶ ‹ለምን አትቀበልም? ልዮንኮ አለቃህ ነው› ሲባል ‹ልክ ነው ልዮን አለቃዬ ነው፡፡ ነገር ግን ከእምነቱ ሲወጣ አልቀበለውም፡፡ ሳጥናኤልም ለቅዱስ ሚካኤል አለቃው ነበር፤ ከእምነቱ ሲወጣ ግን አልተቀበለውም› ያለውን እዚህ ላይ ማስታወሱ መልካም ነው፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያናችን ኢኩሜኒዝምን የተመለከተ ፖሊሲና መመሪያ ካላወጣች፣ ጠንካራ ተቋምም ካልመሠረተች ነገ ከዚህ የባሰ ነገር ማየታችን አይቀርም፡፡ ከዚህ ተግባር የተማርነው ግን የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ በነቃ ኅሊና መከታተል እንዳለብን ነው፡፡ ያሳወቁንን እያመሰገንን፣ ያላወቅነው እንዲገልጥልን እንለምናለን፡፡    

መማርና መማር (ሲጠብቅና ሲላላ)

$
0
0


ትዳርን የተቃናና የተሳካ ለማድረግ በሁለት ባላዎች ላይ መትከል ያሻል ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡ በመማርና በመማር፡፡
  ሰው ሌላውን ሥራ ሁሉ የሚሠራው አንድም ተምሮ አንድም ለምዶ ነው፡፡ ትዳር ሲመሠርት ግን ትምህርትም ልምድም የለም፡፡ ትዳርን እንደ ትምህርት ዓይነት መርጦ፣ ከፊደል እስከ ዳዊት ደግሞ፤ አድርሶ አስመስክሮ የተመረቀ የለም፡፡ እዚህም እዚያም ትዳርን የተመለከተ ንባብና ሐሳብ ይገኝ ካልሆነ የትዳር ዲፕሎማና ዲግሪ፣ ማስተርስና ዱክትርና የለም፡፡ ሌላውን ሞያ ለተግባሩ ተመሳሳይ በሆነ አምሳያ ተግባር(ዎርክ ሾፕ/ሲሙሌተር) ልምምድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ትዳርን ግን በአምሳያው ላይ ልምምድ ማድረግ አይቻልም፡፡ ‹እገሌ ይህን ያህል ዓመት ትዳርን በተመለከተ ልምድ አለው› ብሎ መጻፍ የሚችል መሥሪያ ቤትም የለም፡፡ ለዚህ ነው በትዳር ጉዞ ውስጥ ‹ እየኖሩ መማር› ወሳኝ የሚሆነው፡፡
ትዳር ማለት ጥቂት ዕውቀትና ጥቂት ሐሳብ ይዘው ገብተው፣ እየኖሩ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለ ዋና በሚገባ ማወቅ የሚቻለው እየዋኙ እንደሆነው ሁሉ፣ ስለ ትዳር በበቂ ሁኔታ መማር የሚቻለው እየኖሩ ነው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ቤተሰቦች ባሕልና መርሕ ያደጉ፣ አንዱ ለሌላው ተብሎ በዕውቅ ያልተሠሩ፣ በነጠላ ተወልደው በድርብ የሚኖሩ ናቸውና፡፡ በትዳር መርከብ ውስጥ ከሌላው ጋር ሲኖሩ ሊከሰቱ የሚችሉትን የአስተሳሰብ፣ የፍላጎት፣ የጠባይና የአካሄድ ለውጦች አስቀድሞና አስረግጦ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንኳን አንዱ ስለሌላው ስለራሱም ለውጥ ቀድሞ መተንበይ ይከብደዋል፡፡ ይባስ ብሎም ከዚያ በፊት ያልነበሩ ሦስት ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ በየራሳቸው ሲወስኑና ሲያደርጉ የኖሩት ወንድና ሴት በጋብቻ ምክንያት ሥልጣናቸው የጋራ፣ ኃላፊነታቸው የጋራ፣ ውሳኔያቸውም የጋራ ይሆናል፡፡ መመካከር፣ መግባባትና መጋራት የግድ ይሆናል፡፡ በአንድ ዙፋን ላይ ሁለት ነገሥታት ይነግሣሉ፡፡ 

በእዝ ሠንሠለት ሁለት ሰዎች ለአንድ ሰው ተጠሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንድ ሰው ግን ለሁለት ሰው ተጠሪ አይሆንም፡፡ በትዳር ውስጥ ግን ይከሰታል፡፡ አንድ ልጅ፣አንድ የቤት ሠራተኛ፣ አንድ በቤት ውስጥ የሚኖር ሰው ለሁለት ሰዎች ተጠሪ ይሆናል፡፡ በሁለቱ ጋብቻ ምክንያት ሌላ ማኅበረሰብ ይፈጠራል፡፡ ሲለጥቅ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሚተቃቀፉ፣ አንዳንድ ጊዜም የሚገፋፉ ሁለት ቤተሰቦች ከሁለቱ ጀርባ ይመጣሉ፡፡ መጥተውም ወይ ጸጥ ያለ፣ አለያም ማዕበል የበዛበት ውቅያኖስ ይፈጥራሉ፡፡ ይህን የቤተሰብ ውቅያኖስ ማስተዳደር ለተጋቢዎቹ አዲስ ነገር ነው፡፡ ሲሠልስ ደግሞ ከሁለቱ ኑሮ ልጆች ይወለዳሉ፡፡ ይህን አዲስ የተፈጥሮ ስጦታ መቀበል፣ ተቀብሎም ማስተዳደር ዕውቀት፣ ብስለትና ጥበብ ይጠይቃል፡፡
በዚህ ሁሉ ጉዞ ውስጥ ብልህ ይማራል፣ ሞኝ ያማርራል፡፡ ብልህ ከምን ይማራል? ቢሉ ከሦስት ነገሮች ይማራል፡፡ ከራሱ ጉዞ ይማራል፤ ከትዳር አጋሩ ጉዞ ይማራል፤ ከሁለቱም ጉዞ ይማራል፡፡ ቀድሞ የሚያውቃቸውን፣ ይሆናሉ ብሎ ሲገምታቸው የኖሩትን፣ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸውንና እንዲያደርጋቸው የተመከረውን በትዳር ውስጥ ይሞክራቸዋል፡፡ የተሳካ ውጤት ካመጣለት፣ እሰየው ብሎ መመሪያው ያደርጋቸዋል፡፡ ችግር ከተፈጠረበት፣ ይቅርታ ብሎ ያርማቸዋል፡፡ እየተሞረደና እየተሳለ፣ እያወቀና እየበሰለ፣ እየታረመና እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡ ለዚህም ነው የተሟላ ባል ማግኘት አይቻልም፤ የሚሟላ ባል እንጂ፣ የተሟላች ሚስትም ማግኘት ከባድ ነው፣ የምትሟላ ሚስት እንጂ የሚባለው፡፡
ብልህ ከትዳር አጋሩም ይማራል፡፡ የትዳር አጋርን በእጮኝነት ጊዜ ማየት ፀሐይን በሩቁ እንደማየት፣ በትዳር ጊዜ ማየት ደግሞ ፀሐይን ቀርቦ እንደማየት ነው ይባላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከምናስበው የተለየ ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ መሆኑን ቀድሜ ባውቅ ኖሮ አላገባትም/ አላገባውም ነበር ያሰኛል፡፡ ሊቃውንቱ ‹እንዳውቅህ ተገለጥ› ይላሉ፡፡ የአንድን ሰው ጠባይ፣ ሐሳብና አቋም መገለጡን አንጥላው፡፡ ባወቅነው መጠን እንዴት መያዝ፣ እንዴትስ ማሸነፍ እንደምንችል እናውቃለንና፡፡ ከማያውቁት ነገር ጋር መኖር እንጂ ካወቁት ነገር ጋር መኖር አያስፈራም፡፡ ከትዳር አጋርህ ጋር ይበልጥ አብረሃት በኖርክ ቁጥር ይበልጥ ታውቃታለህ፤ ይበልጥ ባወቅካት ቁጥርም ይበልጥ አብረሃት ትኖራለህ፡፡ ብልህ ባል ከብርታቷም ሆነ ከድካሟ፣ ከትዕግሥቷም ሆነ ከንዴቷ፣ የሚወስደው ትምህርት አለ፡፡ ብልህ ሚስትም እንዲሁ፡፡ ትዳር ማለት ምርቃት የሌለበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ እንደጎበዝ የአብነት ተማሪ ሲቀጽሉ መኖር፡፡ አብረው መዝለቅ የቻሉ ባለትዳሮች በሚገባ እየተማሩ፣ የሰለጡ ባለትዳሮች ይሆናሉ፡፡
በትዳር መማር ብቻ ሳይሆን መማማርም አለ፡፡ ከየራሳቸውና ከአጋራቸው ብቻ ሳይሆን ከጋራ ኑሯቸውም ይማራሉ፡፡ ጋብቻ ማለት በትዳር ላይ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚረከቡበት ቀን ነው፡፡ ጋብቻ በሰጣቸው ሥልጣን ብቻ የሚጠቀሙ ባለትዳሮች ፍቻቸው ቅርብ ነው፡፡ ጋብቻ በሰጣቸው ኃላፊነት ብቻ የሚጠቀሙ ባለትዳሮችም ምሬታቸው ቅርብ ነው፡፡ ጋብቻ ሥልጣንና ኃላፊነት ነው፡፡ ትዳር የሠመረ የሚሆነው እነዚህ ሁለቱ ሚዛን ሲሠሩ ነው፡፡ ትዳር ማለት የሥልጣንና የኃላፊነት አማካዩ ነው፡፡ ኃላፊነት በተሞላበት ስሜት ሥልጣንን ለመጠቀምና ሥልጣን ባለው መንገድ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚችሉበትን ዘዴ የሚያገኙት አብሮ በመኖር፣ አብሮም በመማማር ነው፡፡ እየተማማሩ በሄዱ ቁጥር ሥልጣናቸውን የጋራ፣ ኃላፊነታቸውንም የጋራ ያደርጉታል፡፡
ትዳርን የሚያቆመው ሌላው ባላ ደግሞ ‹መማር› ነው፡፡ ይቅር ማለት፡፡ ይቅር ማለት ‹ለይቅርታ የተዘጋጀ ልብ› ይፈልጋል፡፡ ይቅር ማለት ሽማግሌ ገብቶ፣ ዕርቅ ወርዶ ይቅርታ ሲጠየቅ ‹እሺ ይቅር ብያለሁ› ማለት አይደለም፡፡ ነገሮችን ለማለፍና ለማሳለፍ፣ ራስ ምክንያት ሰጥቶ ይቅር ብሎ ለማለፍ ዝግጁ መሆን ነው፡፡ ነገሮችን በክፋትና በተንኮል ከማየት ይልቅ ከልምድ እጥረት፣ ከጊዜያዊ ስሜት፣ከማይታወቁ መነሻዎችና ከድካም ሊመጡ እንደሚችሉ በመረዳት ቀድሞ ይቅር ማለት፡፡ ቀድሞ ይቅር የሚል ሰው መፍትሔው ላይ እንጂ ችግሩ ላይ አይቆዝምም፤ነገሩን ከመፍተል ይልቅ መፍትሔውን ይሸምናል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው› ብሎ ስለ ሰቃዮቹ ለምኗል፡፡ ሰቃዮቹ ‹የምናደርገውን ስለማናውቅ ይቅር በለን› አላሉትም፡፡ እርሱ ራሱ የቅድሚያ ምክንያት ሰጥቶ ‹የሚያደርጉትን አያውቁም› አለላቸው እንጂ፡፡ የይቅርታ ልብ ማለት ይህ ነው፡፡ በማናቸውም ጊዜና በማናቸውም ሁኔታ እያስተሠረዩ መጓዝ፡፡
ትዳር ነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም፡፡ ልምድ ማስቆጠሪያ እንጂ፡፡ ትዳር በሁሉም ነገር መግባባትን፣ መተማመንንና መስማማትን አይጠይቅም፤ ከተለያዩ በታዎች በመጡ፣ በጾታም በማይገናኙ ሁለት ሰዎች የሚመሠረት ነውና፡፡ ትዳር የተለያዩ ሰዎች ያዘጋጁዋቸው ሁለት ፈትሎች እየተገመዱ የሚሄዱበት ሽመና ነው፡፡ ሲጀመር ጫፍና ጫፉ ይያያዛል፣  በሂደት ግን ካልተገመደው የተገመደው እየበለጠ ይሄዳል፡፡ ግመዳው ግን እንዲህ በቀላሉ የሚከወን አይደለም፡፡ ውስጡ ሕመም አለው፡፡ ያንን ሕመም መጀመሪያ ማከም፣ በኋላም ማዳን የሚቻለው በይቅርታ ነው፤ በመማር፡፡ ውይይቱና ክርክሩ እንኳን ውጤት የሚያመጣው በሁለቱም ልብ ውስጥ የይቅርታ ልብ ካለ ብቻ ነው፡፡ ውጤቱ መሸናነፍ ሳይሆን መተራረም ከሆነ፡፡ መማር ‹ይቅር ብያለሁ› ማለት አይደለም፡፡ መተውና መርሳት ጭምር እንጂ፡፡ ፋይል እየሰበሰቡና በትናንቱ እርሾ የዛሬውን ሊጥ እያቦኩ መሄድ አይደለም፡፡ በትዳር መጋገር ያለበት አፍለኛ እንጀራ ነው፡፡
ከትናንቱ ተምሮና ምሮ መሄድ እንጂ፣ አምርሮና አማርሮ መሄድ ትዳርን ይበክለዋል፡፡
መማርና መማር - ለተቃና ትዳር፡፡

ጥበበኛው ግንበኛ

$
0
0
ግንበኛው ድንጋዩን ይጠርብና በድርድሩ ላይ ሰክቶ አንዴ ፈገግ፣ አንዴ ተከዝ፣ አንዴ ቆም አንዴም ጎንበስ ይላል፡፡ ላት አይቶ በግ እንደሚገዛ ሰው በግራ በቀኝ ያገላብጠዋል፡፡ እንደ ገዳም ጸሎት ሲመሰጥ፣ እንደ ጉብታ ዛፍ ሲናወጥ ይታያል፡፡ እንደ ኮከብ ቆጣሪ ሲያፈጥ፣ እንደ ጥሩ ወጥ ቀማሽ ምራቁን ሲወጥ ይታያል፡፡ ድንጋዩን በግራ ቀኝ ሲፈልጠው ልጇን እንደምታጥብ እናት ሲሳሳ፣ ቅባት እንደምትቀባ ፀጉር ሠሪ ሲዳስስ ይታያል፡፡
ይህንን ሁሉ ያየ መንገደኛ ‹ጌታው፣ ሲያዩህ እንደ ግንበኛ ድንጋይ ትጠርባለህ፣ ግንብ ትሰድራለህ፤ ሁኔታህን ላስተዋለው ግን እንደ ሙዚቀኛም፣ እንደ ቲያትረኛም፣ እንደ ቀማሚም እንደ ዘማሚም ትመስላለህ፡፡ ለመሆኑ ምን እያደረግኩ ነው ትላለህ?› ሲል ጠየቀው፡፡ ግንበኛው መዶሻውን ድንጋዩ ላይ አንተራሰና
እኔ! እኔማ እየፈለጥኩም ግንብ እየሠራሁም አይደለም፡፡
እኔ! እኔማ እንደ ያሬድ አዜማለሁ
እንደ ተዋነይ እቀኛለሁ
እንደ ላሊበላ ድንጋዩን አናግረዋለሁ
እንደ ጊዮርጊስ አመሠጥራለሁ
እንደ አፈወርቅ እስላለሁ
እንደ ሐዲስ እደርሳለሁ
እንደ ጸጋዬ እገጥማለሁ
እንደ ወጋየሁ እተርካለሁ
እንደ ሺመልስ እተውናለሁ
እንደ ኤልያስ አቀናብራለሁ
እስኪ ተመልከታቸውማ፤ የበቃ ባለቅኔ የሰባ ቃል እንዲሻ፣ እነዚህ ጥርብ ድንጋዮች ለእኔ ቃላት ናቸው፡፡ እመርጣለሁ፣ እቀርጻለሁ፡፡ የሰላ ባለ ቅኔ ያማረ ቃል እንዲሻ፣ እኔም እኒህን የድንጋይ ቃላት አሣምራቸዋለሁ፡፡ እኔ ድንጋይ አልፈልጥም፡፡ ሕይወትም በድንጋይ አትኖርም፤ ሕይወትም በድንጋይ አትረካም፡፡ ድንጋይማ የጉልበት ሥራ ነው፡፡ እኔ ቃላትን በፈለገው ቅርጽ ከመዝገቡ እንደሚያወጣ እንደ ርቱዕ ደራሲ ነኝ፡፡ አንዳንዱ ድንጋይ ፈሊጥ ነው፤ አንዳንዱ ድንጋይ ምሳሌ፤ አንዳንዱ ድንጋይ ተረት ነው አንዳንዱ ድንጋይ ዘይቤ፡፡ 

እነዚህን የድንጋይ ቃላት በግንቡ ላይ ስደረድር ዜማ ነው የማቀናብር፡፡ እስኪ ተመልከታቸው፣ ድንጋዮቹኮ ምት አላቸው፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር ተስማምቶና ተዋሕዶ፣ ላይኛው ከታችኛው ጋር ተናቦና ተገናዝቦ፤ ሥሉጥ አቀናባሪ እንዳገኘው ውብ ዜማ፣ ረቂቅ ነው ሙዚቃው ከግንቡ ላይ የሚሰማ፡፡ እስኪ ቀና በልና ድርደራቸውን እያቸው፤ ድንጋዮችኮ ቃላት ናቸው፡፡ ውብ ባለ ቅኔ ካገኛቸው፣ ምሥጢር ዐዋቂ ካሰናኛቸው፡፡ ይኼ ከላይ የማታየው ከግንቡ ጫፍ እስከ ጫፍ ሠልቶ የተደረደረው፡፡ እርሱ የወል ቤት ግጥም ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በወዲህ ዳር፣ ከግንቡ ጫፍ እስከ መስኮቱ አጥሮ የተገጠገጠው፤ እርሱ ቡሄ በሉ ቤት ነው፡፡
ቡሄ በሉ
ልጆች ሁሉ
ቡሄ መጣ
ያ መላጣ፡፡ እያለ ወደታች ይወርዳል፡፡ እንዲህ አጭር ቤት የሚመታ የቡሄ ቤት ባለ ቅኔ፣ ቃላቱን ሲሰይፍና ሲፎንን እንደሚውለው፡፡ እኔም ድንጋዮቹን ስቀርጽና ስቆራርጥ እውላለሁ፡፡ እይውልህ ወዳጄ፡፡ ቅኔ በቁጥር ይመጠናል፣ ዜማው በቁጥር ይለካል፣ መድፊያው ደግሞ ቤት ይመታል፡፡ እኔም ድንጋይ እቆጥራለሁ፡፡ ባለቅኔው ከላይ ወደ ታች፣ እኔ ግን ከታች ወደ ላይ እገጥማለሁ፡፡ የላይኛው ቤት ሲሠራ ከታችኛው ካልገጠመ፣አንድም ሕንጻው ይፈርሳል፣ አንድም ውበቱ ይጠፋል፡፡ ቆጥሮ ያልተቀኘ ባለ ቅኔ ዜማውን ሲሰብር እንዲገኝ፣ ቆጥሮ ያልሠራ ግንበኛም የግንቡን ዜማ ይሠብራል፣ ያኛው ጆሮን ሲያሳቅቅ ይህኛው ዓይን ያሳቅቃል፡፡
እስኪ ተመልከተው ወዳጄ! አንዳች ሥዕል ይታይሃል? ድንጋዮችኮ ቀለም ናቸው፡፡ መርጠህ የምታፈሳቸው፡፡ ይታዩሃል እነዚያ በድንጋዮቹ መካከል የተሰነቀሩት ቁራጮቹ? እነርሱ ምን ይመስሉሃል? በሥዕሉ መካከል የገቡ ሰረዞች ናቸው፡፡ የቀለም ድርደራህ መልክና ልክ እንዲኖረው፣ በእነርሱ ነው የምትለየው፡፡ የድንጋዮቹ መጠን፣ የአቀማመጣቸው ሁኔታ፣ ቅርጻቸውና መልካቸው ሁሉም አመክንዮ አላቸው፡፡
ደግሞም እፈላሰፋለሁ፡፡ ከላይ ያለው በታቹ ላይ ሲቀመጥበት እያየሁ፡፡ ታቹ ሕዝብ ነው እላለሁ፡፡ ስንቱን ችሎ እንደተሸከመ አሻቅቤ አየዋለሁ፡፡ ደግሞም የዓለምን ነገር አይቼ እገረማለሁ፡፡ ሁሉም ከአንድ ቦታ መጥቶ፣ በአንድ ግንበኛ ተሠርቶ፣ ግን ዕጣ ፈንታው ሆነና አንዱ በሌላው ላይ ተቀመጠ፣ አንዱ ከሌላው በለጠ፡፡  አንዱ መጸዳጃ ሆነ፣ አንደኛው ለሳሎን ተጌጠ፤ አንዱ እልፍኝ ውስጥ ገብቶ የሰው ምሥጢር ላይ አፈጠጠ፣ አንዱ ማዕድ ቤት ተሽጦ ከጢስ ከእሳት ጋር ተጋፈጠ፡፡ አንደኛው ወደ ውጭ ወጥቶ ለዝናብ ለፀሐይ ተጋለጠ፤ አንዱ ወደ ውስጥ ሰምጦ የጥላን ዕንቅልፍ ለጠለጠ፡፡
ታችኞቹ እጅግ ያሳዝኑኛል፡፡ በአንድ በኩል ሌላውን ሁሉ ተሸክመዋል፡፡ይህ አልበቃቸው ብሎ መከራው በእነርሱ ይብሳል፡፡   ቆሻሻ የሚሸከሙት እነርሱ ናቸው፡፡ ዝናብ የሚያገኛቸው እነርሱ ናቸው፤ ሥዕልና ፎቶ እሰቅላለሁ ያለ ሁሉ በሚስማር የሚመታቸው እነርሱ ናቸው፡፡ ወንበር የሚገጫቸው፣ የጠረጲዛ ጠርዝ የሚሠረስራቸው እነርሱ ናቸው፡፡
እይውልህ፤ እኔ እንዲህ ሳደርግ ነው የምውለው፡፡ አንተስ ምንድን ነው የምትሠራው?
‹እኔ የቢሮ ሠራተኛ ነኝ› አለ መንገደኛው፡፡
የቢሮ ሠራተኛ ነኝ ብለህ ካሰብክ ሥራህንም ሕይወትክንም ትጠላዋለህ፡፡ አንድ ዓይነት ይሆንብሃል፤ እየቆየ ይሰለችሃል፤ ሲሰለችህ ጠባይህ ይቀየራል፣ ጠባይህ ሲቀየር አነዋወርህ ይበላሻል፡፡ ይልቅ አዚም፣ ተቀኝ፣ ግጠም፣ ድረስ፣ ሳል፣ አመሥጥር፣ ተፈላሰፍ፣ ተመሰጥ፡፡ በደብዳቤው ተቀኝበት፣ በፋይሉ ተሰላሰፍ፣ ወንበርህን ቡርሽ አድርገው ጠረጲዛህን ሰሌዳ፣ ስክርቢቶህ ብዕር ይሁን፣ ደብዳቤህ ደግሞ ብራና፡፡ ባለ ጉዳይ ስታነጋግር ንግግርህ ዜማ ይሁን፣ የሰውን ችግር ስትሰማ ከባድ ቅኔ ዝረፍ እንደተባለ ደቀ መዝሙር ራስህን ቁጠር፣ ሥራህን በዕለት ካልጨረስክ ቤት የማይመታ ግጥም እንደገጠምክ ቁጠረው፣ ሥራህን ስታበላሸው ዜማ እንደሰበርክ ተረዳው፡፡ ደግሞም ተፈላሰፍበት የኑሮን መንገድ መርምረው፡፡ ዛሬ አንተ ጋር የመጣው ደንበኛ ነገ እርሱ በተራው ሹም ነው፡፡ አንተም ሌሎችን እንዳስተናገድክ፣ ሌላ ቦታ አንተም ተስተናጋጅ ነህ፡፡ ሕይወት ይኼውልህ እንዲህ ናት፡፡ አንተ እዚህ ፋይል ስትከምር ያንተም ፋይል ሌላ ቦታ ይከመራል፤ አንተ እዚህ ነገር ስትቋጭ ያንተም ነገር ሌላ ቦታ ይቋጫል፡፡ ሕይወት ዜማ ከሌላት፣ ሕይወት ምቷን ካልጠበቀች፣ ሕይወት ቅኔ ካልቆጠረች፣ ሰምና ወርቁን ካልሠራች፣ ሕይወት ሥዕል ካልሳለች በቀለማት ካልተዋበች፤ኧረ ትሰለቻለች!
ደስታ ወደ ውስጥ አይገባም፤ ደስታ ከውስጥ ይወጣል እንጂ፡፡ ለዚህች ለአጭር ዘመን እድሜ በድንገት ለምትቀጨው፤ ይህ ሁሉ ጭንቀት ለምን ነው? ባለ ጉዳዮችህን እንደ ችግር አትያቸው፤ እንደ ቅኔ ቁጠራቸው፤ ነገራቸው ሲረዝምብህ መወድስ ቅኔ አድርጋቸው፣ ነገራቸው ሲያጥርልህ ጉባኤ ቃና በላቸው፡፡ እነርሱን ዜማህ አድርጋቸው፡፡ ሮሯቸውን ሲያወሩህ እንጉርጉሮ ነው በላቸው፤ ደስታቸውንም ሲነግሩህ ጉሮ ወሸባዬ ነው በላቸው፡፡ ስብሰባህን ማኅሌት፣ ኮሚቴህን ወረብ አድርገው፡፡ ለምሬት ቦታን አትስጠው፡፡ ሥራህን ሥራ አታድርገው፣ ሥራህን ጥበብ አድርገው፡፡ 

‹፣›

$
0
0


‹እኔኮ እዚህ ሀገር መኖር አልቻልኩም፡፡ በቃ ዝም ብለው ደስ ያላቸውን ሁሉ ነው እንዴ የሚያወሩት፡፡ አሁን ከነ እንትና ይኼ ይጠበቃል፡፡› እያለ በአራቱም አቅጣጫ መኪና እንደበዛበት የትራፊክ ፖሊስ እጁን በላይና በታች፣ በግራና በቀኝ እያወናጨፈ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ 

‹እኔኮ ምን ይሻለኛል?እነዚህ ሰዎች ጋር መኖር የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ በቀደም እንደዚያ ሲሉ ቆዩ፣ አሁን ደግሞ እንደዚህ ይላሉ?ቆይ ግን እንዴት ሆኖ ነው ከሰው ጋር መኖር የሚቻለው?› ሶፋው ላይ ዘፍ አለበትና በመዳፉ እንደ ቡና ወቀጠው፡፡ ይህን ሲሰሙ አጎቱ ጋቢያቸውን እያጣፉ ከመኝታ ቤት ወጡ፡፡ በሰያፍ ተመለከቱት፡፡ ፊቱ የማረቆ በርበሬ መስሏል፡፡ ጉንጩ ታርዶ እንደወረደ ትኩስ ሥጋ ይንቀጠቀጣል፡፡ እጁ ገበያ እንደ ደራለት ሸማኔ ያለ ዕረፍት ይወራጫል፡፡ እግሩ ምት እንደሚያስጠብቅ ከበሮ መቺ መሬቱን ይጠቀጥቃል፡፡ የሚያወጣው ትንፋሽ ግለቱ ኖርዌይ ላይ ቢገኝ በጥር የማሞቂያ ዋጋ ያተርፋል፡፡


‹ምን ሆንክ› አሉት አጎቱ እንደ ፊልም ሲያዩት ቆይተው፡፡
‹ቆይ ግን ከሰው ጋር እንዴት ነው መኖር የሚቻለው› አላቸው፡፡ ዓይኖቹ ትከሻቸው ጋ ደርሰው ተመለሱ፡፡
ከሰው ጋር ሲኖሩ ሞኝ ሆኖ

አህያ ሲጭኑ ሦስት ሆኖ - ይባላል፡፡ አጎቱ እየሳቁ ጎኑ ተቀመጡ፡፡
‹ሞኝኮ ሦስት ጊዜ ይሸወዳል፡፡ መጀመሪያ ሞኝ ሲሆን፣ ቀጥሎ ሰዎች ሞኝ መሆኑን ሲያውቁ፣ በመጨረሻም ሞኝ ነው ብለው ሲያሞኙት፡፡ አየህ ሞኝ ስትሆን ሁሉንም ታምናለህ፡፡ ያን ጊዜ ትሸወዳለህ፡፡ የምታምነው እንጂ የሚታመንልህ አይኖርማ፡፡
አያሌው ሞኙ
ሰው አማኙ

የተባለውኮ ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ሞኝ መሆንህን ሲደርሱበት ደግሞ ዋጋህን ከግማሽ በላይ ያወርዱታል፡፡ ‹አሞኘ› የሚባል እንጂ ‹ተሞኘ› የሚባል ስም ሰምተህ ታውቃለህ፡፡ ሞኝ መሆንህን ሲያውቁ በጣም የምትቀርባቸው ሰዎች ሳይቀሩ አንተን በማሞኘት ደስታን ይፈጥራሉ፡፡ ‹ሞኝ አይሙት እንዲያጫውት የተባለው ለዚህ ነው› ሞኝነትህን ለሌላ ሰው ብቻ ሳይሆን ላንተ ለራስህ ‹አይ ሞኙ› እያሉ ይነግሩሃል፡፡ እና እንዴት ነው ሞኝ ሁን የምትለኝ፡፡ ብልጥ ሆኜም አልቻልኩት›

‹አይ፣ ይኼን እንኳን ትንሽ ዘና እንድትል ብዬ ነው፡፡ እሳት ላይ እሳት ላለመጨመር፡፡ ያንን የንብረት ክፍፍል ወረቀት አምጣውማ› አሉት ከቴሌቭዥኑ አጠገብ የሚገኝ ወረቀት እያመለከቱ፡፡ አንድ እግሩን ከነበረበት ሳይለቅ አንድ እግሩን አሻግሮ ይዞላቸው መጣ፡፡
‹ይቺን የመጀመሪያዋን ዐርፍተ ነገር አንብብልኝ› አሉት

ተቀበለና ወረቀቱን ከላይ ወደታች በዓይኑ ዋኘበት፡፡
‹የመጀመሪያውን ዐርፍተ ነገር ብቻ› አሉት፡፡

‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው፣ የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ፣ ወፍጮ ቤቱ፣ የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡› አለና ቀና ብሎ አያቸው፡፡

‹የተጻፈውን ሁሉ አንብበህዋል› አሉት፡፡
‹አዎ፤ የመጀመሪያውን ዐረፍተ ነገር ነው አይደል ያልከኝ› አላቸው፡፡
‹አዎ›
ወረቀቱን ለመቀበል እጃቸውን ዘረጉለት፡፡

‹ተሳስተሃል፤ ያላነበብከው ነገር አለ› አሉና መልሰው ሰጡት፡፡ ወረቀቱን ጠጋ አድርጎ መነጠረው፡፡ ምንም ነገር የሳተው የለም፡፡ ፊደሉን ቆጠረው፡፡ ያው ነው፡፡ ‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው፣ የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ፣ ወፍጮ ቤቱ፣ የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡ አይደለም እንዴ የሚለው›

ወረቀቱን ተቀበሉትና በጣታቸው መጠቆም ጀመሩ፡፡ ‹እስኪ መኪናው በሚለውና የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ በሚለው መካከል ምን ይታይሃል?በሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑና በወፍጮ ቤቱ መካከል ምንም ነገር የለም?በወፍጮ ቤቱና በትራክተሩ መካከልስ ቦታው ባዶ ነው?› ቅድም አጎቱ እንዳሉት ሞኝ የሆነ መሰለው፡፡

‹የሚታየኝ ነጠላ ሠረዝ ብቻ ነው›
‹አ - ዎ፤ ታድያ ለምን አላነበብከውም?‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው (ነጠላ ሰረዝ) የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ (ነጠላ ሠረዝ) ወፍጮ ቤቱ (ነጠላ ሠረዝ) የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡ ብለህ ለምን አላነበብክም?ለምን ዘለልከው?

‹እንዴ አጎቴ፤ ነጠላ ሠረዝ ይነበባል እንዴ?
‹ካልተነበበ ታድያ ለምን ገባ?
‹ለአነባበቡ ይመስለኛል›
‹እንዴት›

‹በቃ፣ በየመሐሉ ፋታ እየሰጡ ለማንበብ›
‹ስታነብ ግን ነጠላ ሠረዙን ታየዋለህ አታየውም›
‹አየዋለሁ እንጂ›
‹ግን አታነበውም› ነገር ዓለሙን ረስቶ ሳቀ፡፡

‹በየሕይወትም ውስጥ እንደዚህ ነው፡፡ ብዙ ነጠላ ሠረዞች አሉ፡፡ የሚታዩ እንጂ የማይነበቡ፡፡ የሚሰሙ እንጂ የማይደመጡ፣ የአንተ ችግር ነጠላ ሠረዙን ሁሉ ስለምታነብ ነው፡፡ ነጠላ ሠረዝ - ሰዎች፣ ነጠላ ሠረዝ ሐሳቦች፣ ነጠላ ሠረዝ - ድርጊቶች፣ ነጠላ ሠረዝ - ክስተቶች፣ ነጠላ ሠረዝ - ችግሮች ሞልተዋል፡፡ ሁሉም ግን ይታያሉ እንጂ አይነበቡም፡፡ ትዘላቸዋለህ፡፡ ቢበዛ - ገታ - ያደርጉህና ፋታ ትወስድባቸዋለህ፡፡ ከዚያ በላይ ግን ቦታ አትሰጣቸውም፡፡ ትሻገራቸዋለህ፡፡ ነጠላ ሠረዞቹ ግን ለአነባበብህ ያስፈልጉሃል፤ በሕይወትህ ውስጥ ያሉ ነጠላ ሠረዞችም የአኗኗርህን መንገድ ለማስተካከል ያስፈልጉሃል፡፡ ግን አይነበቡም፡፡ በሕይወትህ ውስጥ ነጠላ ሠረዙን ሁሉ እያስገባህ የምታነብ ከሆን ምን እንደምትሆን ታውቃለህ?› ዝም ብሎ አያቸው፡፡

‹እንካ የቅድሙን ጽሑፍ ነጠላ ሠረዙን እያስገባህ አንብበው›

‹ከንብረቱ መካከል የቤት መኪናው (ነጠላ ሰረዝ) የሲሚንቶ ማቡኪያ ማሽኑ (ነጠላ ሠረዝ) ወፍጮ ቤቱ (ነጠላ ሠረዝ) የእርሻው ትራክተርና የጭነት መኪናው ለእርሱ ይደርሰዋል፡፡›

‹ዐረፍተ ነገሩ - አንድም ትርጉም አጣ፣ አንድም ቸከ፡፡ ሕይወትህም አንድም ትርጉም ያጣል፣ አንድም ይቸካል፡፡ አንተ አሁን እንዲህ አሉኝ፣ እንዲህ አደረጉኝ፣ እንዲህ ሆኑ፣ እንዲህ ሠሩ የምትላቸው ሁሉ ነጠላ ሠረዞች ናቸው፡፡ አታንባቸው፡፡ ዝለላቸው፡፡ ትርጉም ወደሚሰጠው ነገር ሂድ፣ ይዘሃቸው አትጓዝ፡፡ ነጠላ ሠረዞቹን እዚያው ወረቀቱ ላይ ተዋቸው፡፡
‹ነጠላ ሠረዞች› አለ ሰማ ሰማና

‹መልሰህ አነበብካቸውኮ› አሉት እየሳቁ፡፡

ዋሽንግተን ዲሲ 


በዓለ ወልድ የማነው?

$
0
0

አራት ኪሎ ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አጠገብ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ‹ልማት ላለማ ነው› ብሎ በዚያ ያረፉ ክርስቲያኖችን ዐጽም አንሡልኝ እያለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስን፣ ቀጥሎ የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን አሁን ደግሞ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም አንሡ ብሏል፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድ የማን ነው?
 
ለፕሮፌሰር ዐሥራት የማይሆን በዓለ ወልድ የማን ነው?ከልጅነታቸው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ያደጉ፣ ቤተ መቅደሱን ያገለገሉ፣ በሕክምና ሞያቸው ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እስከ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያከሙ፣ አያሌ ጳጳሳትንና መነኮሳትን በየጊዜው እቤታቸው ድረስ እየመጡ ሲረዱ የነበሩትን የሕክምና ሰው እንደ ባዕድ ቆጥሮ ‹አንሥቼ ወደዚያ አደርጋቸዋለሁ› አለ፡፡ ገና ለገና ከዘመኑ ጋር አይስማሙም፣ በእርሳቸው ጉዳይ መንግሥት አይቆጣንም ብለው ካልሆነ በቀር የፕሮፌሰሩ ውለታ ጠፍቷቸው አልነበረም፡፡ ቀድሞውንም አቡነ ጳውሎስ ፖለቲካው ተጭኗቸው እንጂ ለጥላሁን ገሠሠ የሰጡትን የሥላሴ ቦታ ለፕሮፌሰር ዐሥራት መንፈግ አልነበረባቸውም፡፡ በርግጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዋሉባት እንጂ ለዋሉላት መሆን ካቆመች ቆየች፡፡


የፕሮፌሰር ዐሥራትን ጉዳይ ፓርቲዎቹ ጉዳየ ብለው በክብር አስፈጸሙት፡፡ ይመሰገናሉ፡፡ ፓርቲ አልባውን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬንና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ግን እንደ ተራ ነገር አንሡልኝ አለ አስተዳደሩ፡፡ ቤተ ክህነቱም አያገባኝም ብሎ ዝም አላቸው፡፡ ለመሆኑ በዓለ ወልድን የሊቀ ሥልጣናቱ ብቻ ያደረገው ማነው?እነዚህ ዛሬ ተነሡ የሚሏቸው ሰዎች እኮ ናቸው በዓለ ወልድን የሠሩት?ምእመኑን በእምነቱ አጽንተው እናንተ የሚከፈላችሁን ደመወዝ እንዳይቋረጥባችሁ ያደረጉት?ለመሆኑ አድማሱ ጀንበሬ የቤተሰቦቻቸው ናቸው?የደብሩ ካህናትና የሊቀ ሥልጣናቱ አይደሉም?ሲያስተምሩና ሲያገለግሉ የኖሩት፣ ሲጽፉና ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ጋር ሲታገሉ የኖሩት ለቤተሰቦቻቸው ርስት ጉልት ለማሰጠት ነው?ኮኩሐ ሃይማኖት የተጻፈው ለቤተሰብ ነው?አድማሱ ጀንበሬ የቤተሰቦቻቸው ከሆኑ ነገ ያሬድም፣ አባ ጊዮርጊስም የቤተሰቦቻቸው ናቸው ልትሉን ነው?  

እኒህ ሰውኮ የቤተክርስቲያን ከዚያም ሲያልፍ የሀገር ሀብት ናቸው፡፡ መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬኮ ሙት ያስነሡ ‹ቅዱስ› ናቸው፡፡ በሙት ዘመን ተፈጥረው ቅድስናቸውን የሚያውቅላቸውና የሚያውጅላቸው ጠፋ እንጂ፡፡ ታዋቂነት እንጂ ዐዋቂነት ክብር የማይሰጥበት ጊዜ ሆነ እንጂ ከአትናቴዎስና ከቄርሎስ የሚስተካከሉ ሊቅ ናቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሚነሡ አልነበሩም፤ ቤተ ክርስቲያን የሚሠራላቸው ነበሩ እንጂ፡፡ በምን ሂሳብ ነው ‹ቤተሰቦቻቸው መጥተው አጽሙን ያንሡልን› የሚባለው፡፡ ለመሆኑ ለመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ ክብርና ፍቅር የሌለው ሰበካ ጉባኤ ሃይማኖቱ ምንድን ነው?ደብሩስ የማነው?

የእኒህ አባት ዐጽም የግድ ይፍለስ ከተባለኮ በቤተ ክርስቲያን የፍልሰተ ዐጽም ሥርዓት አለ፡፡ የነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የነ አቡነ ፊልጶስ፣ የነ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፤ ከውጮቹም የነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐጽም እንዴት እንደ ፈለሰ ከካቴድራሉ ዕቃ ቤት ያሉት መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዱናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ የት ሄዶ ነው የአንድ ደብር አስተዳዳሪ የኒህን ቅዱስ ሰው ዐጽም ‹አንሡ፣ ውሰዱ› የሚለው?ወይስ ዮሴፍን የማያውቅ አዲስ ፈርዖን መጣ?

ቤተ ክህነቱ መጽሐፋቸውን አሳትሞ ከመሸጥ ውጭ አያገባውምን?ዛሬ በመልአከ ብርሃናት አድማሱ ላይ እንዲህ ከተደረገ ነገ የየአንዳንዱ ጳጳስና ካህን ፋንታ ዕጣ ከዚህ የከፋ መሆኑን ረሳው?ዛሬ በበዓለ ወልድ የተጀመረው ነገር ሃይ የሚለው ካጣ ወደ ካቴድራሉ ተዛምቶ የማን ዐጽም እንደሚነሣ መንግሥትስ ጠፋው?

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተማሩት በዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ የደከሙት ለዚህች ቤተ ክርስቲያን፣ ያገለገሉት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን - እንዴት ባለ ሂሳብ ነው አዲስ አበባ ለቴአትሩ ንጉሥ ቦታ የላትም ተብሎ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ዐጽሙ ይሂድ የሚባለው?ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ መቀበርም የሚቻለው በክልላችሁ ነው ልትሉን ነው?ዮፍታሔ ንጉሤ የደብረ ኤልያስ ብቻ ናቸው?ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያበረከትሺውን ሰው ጥቀሽ ስትባል ከምትጠቅሳቸው ተርታ አይደሉምን?ይህ ለትውልዱ እየሰጠነው ያለው ትምህርት የት የሚያደርስ ነው?

መሐል ሠፋሪ ጦር ጃንሜዳ እየተሰበሰበ አንዴ እቴጌ ጣይቱ ከቤተ መንግሥት ይውጡ፣ አንዴ ሚኒስትሮቹ ይነሡ ሲል፣ መኳንንቱም እየተቀበሉ ሲያስፈጽሙ፣ እቴጌ ጣይቱ ‹ለዚህ ጦር ክፉ ትምህርት አታስተምሩት፣ ካልሆነ ሁላችሁንም ያወርዳችኋል› ብለው ነበር፡፤ ሰሚ አልተገኘም፡፡ ያው ጦር ግን በ66 ዓም ንጉሡንም መኳንንቱንም አወረደ፡፡ ያውም እንደ እቴጌ ጣይቱ ወደ እንጦጦ አልላካቸውም ፣ ወደ እንጦሮጦስ እንጂ፡፡ ዛሬም ለዚህ ትውልድ ክፉ ትምህርት ባታስተምሩት መልካም ነው፡፡ ዐጽም እያሽቀነጠሩ ሱቅና አዳራሽ መሥራት ነገ በዐጽመ ቅዱሳን መወጋትን ያመጣል፡፡ ሲሠራና ሲታደስ ገንዘብ ካላመጣችሁ የምትሉን ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲህ ደስ ሲላችሁ ዐጽማችንን የምትወረውሩበት ከሆነ በዓለ ወልድ የማነው?ብለን እንጠይቃለን፡፡

በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጽር ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሕንጻ እየሠራ ነው፡፡ ከሕንጻው አጠገብ አንድ አምስት መቃብሮች አሉ፡፡ አንዱ የጣልያን ወታደር፣ ሌሎቹ የኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት እነዚህን ዐጽሞች እግር ከሚጠቀጥቃቸው በክብርና በሥርዓት አንሥተን በተገቢው ቦታ እናድርጋቸው፣ ብለው ጠየቁ፡፡ ቤተ ክህነቱ የሰጠው መልስ ግን አስገራሚ ነበር፡፡ ‹ከመቃብሮቹ መካከል የኢትዮጵያውያንን እንደፈለጋችሁ ማንሣት ትችላላችሁ፤ የጣልያኑን መቃብር ግን እኔ መፍቀድ አልችልም› አላቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለጣልያን ወታደር የምትሰጠውን ቦታ ያህል ለአድማሱ ጀንበሬና ለዮፍታሔ ንጉሤ የላትም?

ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ
ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ
ይሉ ነበር፡፡  



የዮፍታሔና የአድማሱ ነገር

$
0
0

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬንና የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤን ዐጽም በተመለከተ የሰጠውን ማብራሪያ ተመለከትኩት፡፡ ካቴድራሉ ሐሳቡን ለማስረዳት መትጋቱን አደንቃለሁ፡፡ የካቴድራሉ ሐሳብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት የራቀ በመሆኑ ግን ተገርሜያለሁ፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤና መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬን በተመለከተ ካቴድራሉ ያየበት መነጽር ነው ስሕተቱን ያመጣው፡፡ ካቴድራሉ አገልጋዮቹን የሚያያቸው በቤተሰብና በጎጥ ደረጃ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን አገልጋዮቿን የምታያቸው በሀገርና ከዚያም ሲያልፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ የወሎ ቦረና፣ ቅዱስ ያሬድ የትግራይ አኩስም፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሸዋ ጽላልሽ፣ አቡነ አረጋዊ የሮም ተወላጆች እንጂ ሀብቶች አይደሉም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ካቴድራላችን ግን የቤተሰቦቻቸውና የተወላጆቻቸው አድርጎ ያያቸዋል፡፡ ስሕተቱ የመጣው ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ዐጽም በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት ከማፍለስ ይልቅ ‹ቤተሰቦቻቸው ተገኝተው ያፍልሱ› ብሎ ዐዋጅ ከመንገሩ ላይ ነው፡፡ የካቴድራሉ ካህናትና ዲያቆናት ለመልአከ ብርሃን አድማሱና ለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ቤተሰቦቻቸው አይደሉምን? በዚህ ዓይነት እጨጌ ዕንባቆም ወደ የመን፣ አቡነ አረጋዊ ወደ ሮም፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ወደ ግብጽ የሥጋ ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ይሂዱን? ይህ የካቴድራላችን እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አይደለም፡፡
‹ቅንጣቱ ከምሉዑ ውጭ አይሆንም› የሚል ፍልስፍና አለ፡፡ አንድ ነገር የነገሩ ማኅበረሰብ ከሆነው ውጭ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ የቤተ ዘመድና የተወላጅነት አሠራር የቤተ ክህነት ሰዎችን እየተዋሐደን ስለመጣ ሊቃውንትንና ቅዱሳንንም ከጎጥና ከቤተሰብ ውጭ ልናያቸው አልቻልንም፡፡ 

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ያረፉት ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም. ነው፡፡ የዛሬ 70 ዓመት፡፡ ሊቀ ሥላጣናቱ በመግለጫቸው እንደነገሩን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዐጽም ተነሥቶ ሌላ ቦታ የተቀመጠው ‹የቀኝጌታዮፍታሔንጉሤቤተሰቦችበወቅቱባለመምጣታቸው› ነው፡፡ ከሰባ ዓመት በኋላ ትውልድ እንጂ ቤተሰብ እንዴት ይገኛል?በምን ሂሳብ ነው ቤተ ክርስቲያኒቱን አምነው የዛሬ 70 ዓመት የተቀበሩትን ክርስቲያኖች ዐጽም በክብር የማፍለስ ኃላፊነት የልጅ ልጆቻቸው የሚሆነው? አሠራሩ ችግር እንዳለበት የሚያሳየው ካቴድራሉ ባስነገረው ዐዋጅ መሠረት የሚመጣ ጠፍቶ ‹ስምንት ዓመት ዐጽሙ ተነሥቶ ሌላ ቦታ መቆየቱ› ነው፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ካቴድራሉ የሊቁን ዐጽም ሲያነሣ ምን በዓል አዘጋጅቶ ነበር? ለመሆኑ የእኒህን በቤተ ክርስቲያን በምርግትና ያገለገሉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም በዓለም ዐቀፍ መድረክ ያስጠሩ፣ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ልጄ ሆንክ ብላ የምትኮራባቸውን ሊቅ ዐጽም እያነሣ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር? ለመሆኑ የሀገሪቱ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሳይቀር መጋበዝ እንደነበረባቸው ካቴድራሉ ያውቃል? አድባር እኮ ነው እየነቀላችሁ ያላችሁት? ታድያ  እናንተ እኒህን የመሰሉ ሊቅ ዐጽም አንሥታችሁ በማይገባ ቦታ ስታስቀምጡ የሀገሩ ሰዎችማ ምን ያድርጓችሁ? ኃላፊነቱን መውሰድ የነበረባቸው ሀገርና ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ ልኳንዳ ቤት ሥጋ ቆጥረው ኃላፊነቱን ለልጅ ልጆቹ ሲሰጡ ምን ያድርጓችሁ? ‹ተወላጆቹ› በ19/10/2009 በጻፉላችሁ ደብዳቤ ዐጽሙን ወደ ደብረ ኤልያስ(ጎጃም) የወሰዱት ሌላ አማራጭ በማጣታቸው መሆኑን ገልጠውታል፡፡ ምን ያድርጉ?
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ጉዳይ የእኛው የራሳችን የካቴድራሉ አባቶች፣ ከዚያም አልፎ የጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን፣ ተሻግሮም ሀገራችን የኢትዮጵያ ጉዳይ እንጂ የአጥንትና ጉልጥምት ጉዳይ አይደለም ብላችሁ አትመልሱም ነበር? የዮፍታሔ ታሪክ የዚህች ሀገር ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ታሪክ በሚሰጥበት ትምህርት ቤት ሁሉ ይሰጣል፡፡ የነገው ታሪክ ላይ ግን እንዲህ የሚል ትምህርት ጨምራችሁበታል ‹ካቴድራሉ ዐጽሙን አንሥቶ ለክብሩ በማይመጥን ቦታ ስላስቀመጠው፣ በተቀበሩ በ70 ዓመት እንደገና ዐጽሙ ፈልሶ፣ ዓባይን ተሻገረ›፡፡
ለመሆኑ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የማን ናቸው? የቤተሰቦቻቸው ናቸው? ያስተማሩትና የጻፉት ለቤተሰቦቻቸው ነው? የተጋደሉት ለቤተ ክርስቲያን አይደለም? ካቴድራሉ ምን ቢደፍር ነው ለቤተሰቦቻቸው ኃላፊነቱን ሰጥቶ ማስታወቂያ የሚያወጣው? ለመሆኑ በካቴድራሉ ቤተ መጻሕፍት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት ይህንን ነው የሚናገሩት?
በገድለ ተክለ ሃይማኖት መጨረሻ ላይ ‹መጽሐፈ ፍልሰቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት› የሚል መጽሐፍ አለ፡፡ የተጻፈው በ1418 ዓ.ም. በሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት በእጨጌ ዮሐንስ ከማ ነው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዐጽም ካረፉ ከ57 ዓመት በኋላ ከደብረ አስቦ ወደ ዔላም ሲፈልስ የነበረውን ሥርዓት ይናገራል፡፡ አራተኛው እጨጌ አቡነ ሕዝቅያስ ለፍልሰተ ዐጽሙ ደቀ መዝሙሮቻቸውን ጠሩ እንጂ በጽላልሽ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን አልጠሩም፡፡ ካቴድራሉ ግን የእኒህን ሊቅና ጻድቅ ዐጽም ለማንሣት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊት ውጭ ‹ወንድማቸው መጡ፣ ልጃቸው መጣ› በሚል ጠባብ ምልከታ ጉዳዩን ወደ ዘመድ አዝማድ አወረደው?
የሦስተኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት የአቡነ ፊልጶስ ዐጽም ከደቡብ ጎንደር ደብረ ሐቃሊት ገዳም በ1481 ዓም ፈልሷል፡፡ ይህንን ታሪክም በወቅቱ የዓይን ምስክር የነበረውና ‹መጽሐፈ ፍልሰቱ ለአቡነ ፊልጶስ› የተሰኘውን መጽሐፍ በእጨጌ ጴጥሮስ ዘመን(1489-1516) የጻፈው ፍሬ ቅዱስ በሚገባ ይተርከዋል፡፡ ፍሬ ቅዱስ እንደሚነግረን ዐጽሙን ያፈለሱት ደቀ መዝሙሮቻቸውና መላው ክርስቲያኖች እንጂ ዘመዶቻቸው አይደሉም፡፡ የፈለሰውም ወደ ትውልድ ቦታቸው አይደለም፤ ወደ ገዳማቸው እንጂ፡፡ እንዲያውም በሚያስደንቅ ሁኔታ በንጉሥ ሰይፈ አርእድ ተሰደው በሄዱበት ሀገር ያረፉትን የአቡነ ፊልጶስን ዐጽም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1411 ዓ.ም. ለማፍለስ የሞከረው በርናባስ የተባለ ከአገው አውራጃዎች በአንዷ ፍርቃ በምትባለው የሚኖር ክርስቲያን ነው፡፡ ‹ቤተሰባቸው› አይደለም፡፡ ለአባ ፊልጶስ የሥጋ ዘመዱ አይደለም፤ የመንፈስ ልጁ እንጂ፡፡ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጉዳይ የእኛ የመንፈስ ልጆቻቸው፣ የቀለም ልጆቻቸው፣ የሃይማኖት ልጆቻቸው ጉዳይ እንጂ የሥጋ ዘመዶቻቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስንና ካቴድራሉን ነው፡፡
መጋቢት 27 ቀን 1551 ዓ.ም. ከአዳሎች መሪ ከመሐመድ ኑር ጋር ገጥሞ ንጉሥ ገላውዴዎስ ተሸንፎ ተሠዋ፡፡ አብሮት የነበረው የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስም ተሠዋ፡፡ አንድ ምእመንም የእርሱንና የአባ መቃርዮስን ሥጋ ወስዶ በትንሽ መቃብር ቀበራቸው፡፡ በኋላም ሀገር ሲረጋጋ የመንፈስ ልጁ አባ ቴዎሎጎስ ወደሚያስተዳድረው ደብር አመጣው፡፡ የአባ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የሚሆን አባ መብዐ ድንግልም ከዚያ አፍልሶ ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር አመጣው፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ቤተ ዘመድ የለበትም፡፡ ለሊቃውንትና ለቅዱሳን ቤተዘመዶቻቸው የመንፈስ ልጆቻቸው፣ ቤታቸውም ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡
ሩቅ ሳንሄድ ሁለት የቅርብ ዘመን ታሪክ ልጥቀስ፡፡
የአሁኑ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሠሩትን ተጠቃሽ ሥራ መጥቀሱ ይገባል፡፡ በብጹዕነታቸው መሪነትና በአባ ማርቆስ ተፈራ አስተባባሪነት ትልቁ የዝዋይ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲታነጽ የነፍስ ኄር ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ (ካልዕ) ዐጽም ከትንሿ ቤተ ክርስቲያን ፈልሶ ወደ ትልቁ ደብር ገብቷል፡፡ ያን ጊዜ ግን ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ(የአሁኑ) የነፍስ ኄር አቡነ ጎርጎርዮስን ዘመዶች ከወሎ አልጠሩም፡፡ ጉዳዩ የዘመድ ጉዳይ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ነውና፡፡ የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ትምህርት፣ መጻሕፍትና አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ነውና፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ልክ እንደ እጨጌ ሕዝቅያስ የጠሩት በመላው ዓለም የሚገኙ የቀለምና የመንፈስ ልጆቻቸውን ነው፡፡ የሰበሰቡት ጳጳሳትንና ካህናትን ነው፡፡ እንደ ካቴድራሉ ‹ዐጽም አንሡልን› ብለው ዐዋጅ አልነገሩም፡፡ በጸሎትና በቅዳሴ፣ በዝማሬና በማዕጠንት፣ እንደ ጥንቱ ሥርዓት በክብር እንዲፈልስና እንዲያርፍ አደረጉ እንጂ፡፡ ጎርጎርዮስ ጎርጎርዮስን እንዳከበሩ፣ አክባሪ ይላክላቸው፡፡
በደርግ ዘመን በሰማዕትነት አልፎ ዐጽማቸው የትም ተጥሎ የነበሩትን የታላቁን አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዐጽም ማፍለስ ቤተ ክርስቲያናችን ‹ቤተሰቦቻቸውን› በዐዋጅ አልጠራችም፡፡ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መሪነት ራስ ቅዱስ ሲኖዶሱ በክብር አፍልሶ ወደ ጎፋ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አፈለሰው እንጂ፡፡ ይህ የሆነው ግን አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመድ ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፡፡
ካቴድራላችን ይህንን ትውፊት እንዴት ዘንግቶት ነው ጉዳዩን አውርዶ የቤተሰብና የተወላጅ ያደረገው? እንዴው ስንቱን ነገር አውርደንና ወርደን እንችለዋለን? ይህንን በዘመድ መሥራት መቼ ነው የምንተወው?  
<ሆኖምበአሁኑወቅት፣የልጃቸውባለቤትየሆኑግለሰብቀርበውበማመልከታቸው፣ካቴድራሉ፥የመልአከብርሃንአድማሱንዐፅምሌላቦታሰጥቶለማፍለስናለማሳረፍእየተዘጋጀእንዳለአስተዳዳሪውአስታውቀዋል፡፡> ይላል ጋዜጣው፡፡ ባያመለክቱስ ኖሮ ምን ልታደርጓቸው ነበር? እንደ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አንድ ቦታ ከትታችሁ የተናደደ ወገን ሲመጣ ወንዝ ልታሻግሩ? ለመሆኑስ ከልጃቸው ባለቤት ይልቅ ለመልአከ ብርሃን አድማሱ እናንተ አትቀርቧቸውም? ለመሆኑስ ይህን ከማን ነው የተማራችሁት?
አሁንም ሦስት አካላት እንዲያስቡበት አደራ እላለሁ፡፡ ሲኖዶሱ፣ ካቴድራሉና ምእመናኑ፡፡ ሲኖዶሱ ቢያንስ ቢያንስ ነግ በኔ ብሎ ጉዳዩን በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ መመልከት አለበት፡፡ ሊቅ አይውጣላችሁ ተብለን ተረግመን ካልሆነ በቀር፡፡ ካቴድራሉም አሁን እንዳደረገውና እንደሚያደርገው ‹የልጅ ሚስት፣ የልጅ ባል› የሚባለውን ጨዋታ ትቶ ጉዳዩን የቤተ ክርስቲያኒቱ ያድርገው፡፡ ያ ካልሆነ ደግሞ እኛ ምእመናን መንግሥትንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን ጠይቀን ለክብራቸው የሚመጥን ሥራ እንሥራ፡፡ ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነትና ከርግማን እንድናለን፡፡

//kibret1.rssing.com/chan-29905284/article197-live.html

$
0
0

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ወደ ጵጵስናው የመጡት ብዙ ጫና ተደርጎባቸው ነበር፡፡ ከጵጵስናው ይልቅ በሶርያውያን ገዳም መኖርን ይመርጡ ነበር፡፡ ሺኖዳ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ምኞታቸው እንደ አባ ገብረ ክርስቶስ በበረሓ መኖር ነበር፡፡ የወቅቱ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ግን ገዳሙን እንዲረዱ ወደ ሶርያውያን ገዳም ላኳቸው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የገዳሙ አበው ሺኖዳ ለገዳሙ መሻሻል የሚሠሩትን ሥራ አልወደዱትም፡፡ የኢትዮጵያዊው የገብረ ክርስቶስ (አብዱል መሲሕ) ደቀ መዝሙር የነበሩት ሺኖዳ (በጥንቱ ስማቸው አባ እንጦንስ) ግን መከራውን ሁሉ ተቋቋሙት፡፡ በመጨረሻም አቡነ ቄርሎስ ገዳሙን እንዲያስተዳድሩ በጫና ሾሟቸው፡፡ በኃላፊነታቸው ላይ እያሉ ግን እርሳቸው ለገዳሙ መሻሻል የሚሠሩትን ሥራ ያልወደዱ መነኮሳት ተነሡባቸው፡፡ ለፓትርያርኩም ከሰሷቸው፡፡ ፓትርያርኩም አባ እንጦንስን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ጠሯቸው፡፡ ሺኖዳም ከሳሾቻቸው ትክክል እርሳቸው ግን ስሕተት መሆናቸውን ገልጡ፡፡ ይህ ፈተና የመጣውም በእርሳቸው ድክመት እንጂ በከሰሷቸው አባቶች ምክንያት እንዳልሆነ ተናገሩ፡፡ ስለዚህም ከኃላፊነት እንዲነሡና ወደ በረሓ ገብተው በምናኔ እንዲኖሩ የፓትርያርኩን ፈቃድ ጠየቁ፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ ግን ውሳኔያቸውን በማግሥቱ እንደሚያሳውቋቸው ነግረው በመንበረ ፓትርያርኩ እንዲቆዩ አደረጉ፡፡
በማግሥቱ ሴፕቴምበር 30 ቀን 1962 ዓም አቡነ ቄርሎስ አቡነ እንጦንስን ለውሳኔው ጠሯቸው፡፡ አባ እንጦንስም ወደ በረሓው የሚመለሱበትን ቀን እየናፈቁ ጠበቁ፡፡ አቡነ ቄርሎስም እጃቸውን በአቡነ ሺኖዳ ላይ ጭነው ‹የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮትና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳስ› አድርገው ሳያስቡት ሾሟቸው፡፡
ይህ በተፈጸመ ሰሞን የትምህርት ቤት ጓደኛቸውና የብዙ ጊዜ ወዳጃቸው ጀርመናዊው ፕሮቴስታንትና በካይሮ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የኮፕቲክ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ዶክተር ሜናድረስ (Dr. Otto Meinardus) ‹እንኳን ደስ ያለዎት› የሚል የደስታ መግለጫ ደብዳቤ ላከላቸው፡፡ ብጹዕ አቡነ ሺኖዳም ደብዳቤውን በደስታ ከተቀበሉ በኋላ የሚከተለውን መልስ ላኩለት፡፡ 

‹ሰላምና ጸጋ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይሁንልህ፡፡ ስለ ላክህልኝ የደስታ መግለጫ መልእክት ምስጋናዬን አቀርብልሃለሁ፡፡ ወዳጅነትህንና ፍቅርህን መቼም አልዘነጋውም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ላለው (ለጵጵስናው ሹመት) ጊዜ የኀዘን መግለጫ እንጂ የደስታ መግለጫ አይስማማውም፡፡ አንድ መነኩሴ ጸጥታ የነገሠበትን በረሓ ትቶ ውጥንቅጡ ወደ በዛ ከተማ ሲገባ እንዴት እንኳን ደስ ያለህ ይባላል? በክርስቶስ እግር ሥር መቀመጧን ትታ እኅቷ ማርታ ወደምትደክምበት የማድቤት ሥራ ስትመለስ ማርያምን ማነው እንኳን ደስ አለሽ የሚላት? ለእኔ ይህ አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ እኔ ጵጵስና የተሾምኩበትን ቀን የማስታውሰው በኀዘንና በልቅሶ ነው፡፡ እውነት ለመናገር የምናኔና የጸሎት ሕይወት ከማንኛውም መለኪያ በላይ ነው፡፡ ከኤጲስቆጶስነትም ሆነ ከጵጵስና ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ወዳጄ ሆይ እውነተኛው መቀባት (ለጵጵስና መቀባት ሳይሆን) ልብን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ አድርጎ መቀባት ነው፡፡ እርሱ በመጨረሻው ቀን የሚጠይቀን ማዕረጋችንን ሳይሆን ንጹሕ ልባችንን ነውና፡፡ ይህንን የምጽፍልህ በዋዲ - ኤል - ናትሩን፣ ባሕር - ኤል - ፋሬግ ከሚገኘው ከምወደው ዋሻዬ ውስጥ ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ በዚህ ቦታ እስከ ጥምቀት በዓል ድረስ ለመቆየት አስባለሁ፡፡ ከዚያም ወዲያ ወደ ካይሮ እመለሳለሁ፡፡

ለተሾሙት ጳጳሳት በየአካባቢው የሚደረገውን ድግስ ስመለከት ይህ ትዝ አለኝ፡፡ 

Otto Friedrich August Meinardus, Two Thousand Years of Coptic Christianity,1999, p. 5

የደብረ ሊባኖስን ታሪክ ማጥፋት፣ ለምን?

$
0
0



‹በአባታችን በዮሐንስ ከማ ዘመን ሃይማኖቱ የቀና ንጉሥ ይስሐቅ(1406-1421) ታላቅ ቤተ ክርስቲያን በእንጨትና በድንጋይ ያንጹ ዘንድ አዘዘ፡፡ ያቺም ቤተ ክርስቲያን ተሠርታ ስትፈጸም ፈረሰች፡፡ ንጉሡም ይህንን ሰምቶ እጅግ አዘነ፡፡ እንዲህ ሲልም ወደ አባ ዮሐንስ ከማ መልእክት ላከ፤‹‹የዚህን ነገር ምክንያት ታውቅ ዘንድ ጸሎት አድርግ፤ስታውቀውም ወደ እኔ ላክብኝ፡፡›› ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ከማ ቅዱሳን ልጆቹን ሰበሰበ፡፡ ንጉሡ እንዳለው ጸሎትን አጽንተው እንደዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡ እነዚህ ንጹሐን በጸሎት ተግተው በጸኑ ጊዜ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእነዚያ ቅዱሳን ለአንዱ ተገለጠችለት፡፡ እንዲህ ስትልም ተናገረቺው፤ ‹‹ይህንን መሥፈሪያ እንካ፤ ቤተ መቅደሴንም በዚህ መለኪያ ለክተህ ሥራ ብለህ ለአባትህ ለዮሐንስ ከማ ንገረው፡፡ ስትሠሩም ከልጆችህ በቀር ሌሎች አይሥሯት፤ ባስልኤልና ኤልያብ ጥበብን እንደተመሉ(ዘጸ. 31፣1-11)ሁሉ እኔም እነርሱን በጥበብ እመላቸዋለሁ፡፡››
አባታችንም የአምላክ እናት የእመቤታችን የማርያምን የቃል መልእክት በሰማ ጊዜ የሆነውን ሁሉ ለንጉሡ ላከበት፡፡ ንጉሡም የታመነውን የምሥራች ቃል ባገኘ ጊዜ ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥቶ[1]መነኮሳቱን፤ ‹‹የአባታችሁ መቃብር ናትና እናንተ ሥሯት፤ ሌሎች ከሠሯት ግን መልካም አይሆንም ብለው ሐሰት የማይገኝባቸው ሰዎች ነገሩኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ሊሠሩ አልወደዱም ነበር፡፡ ነገር ግን የንጉሡን ቃል እንዳያስተሐቅሩ ሲሉ ጀመሩ፡፡ እርሱ አስቀድሞ ‹‹በንጉሥ ዜና መዋዕል፣ ንጉሥ ሲለምን፤ ለምኖም እምቢ ሲሉት አልሰማሁም›› አላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ሊሠሩ ጀመሩ፡፡ ሕንጻውም በሰባት ዓመት ተፈጸመ፡፡ እዚህ ላይ ከታሪኩ ጋር የሚሄድ መልካምን ዜና እንንገራችሁ፡፡ በገድል የተጠመደ አንድ መነኮስ ነበረ፡፡ ኅሊና መንፈሳዊ በመጣበትም ጊዜ ቁመትን ከጸሎት ጋር አስተባብሮ ያለ ድካም ዘወትር ይተጋ ዘንድ ገድልን ጀመረ፡፡ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንዋን ሕንጻ ፍጻሜ ያሳየው ዘንድ፡፡ በዚህ ሁኔታም ለሰባት ዓመታት ኖረ፡፡ ከዚህም በኋላ የሥራውን ፍጻሜ ሲመለከት የሥጋን ድካም ድል ያደርግ ዘንድ ኃይልን ሰጥቶታልና እግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ የዚህ ጻድቅ ረድኤት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡
ይለናል በ1587 ዓም የተጻፈው ‹ዜና ደብረ ሊባኖስ› የተሰኘው መጽሐፍ፡፡ 

ደብረ ሊባኖስ በ1926/27
የደብረ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ዝም ብሎ እጨጌና መነኮሳት፣ ነገሥታትና መኳንንት፣ መሐንዲሶችና ዶክተሮች ስለፈለጉ ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ኢየሩሳሌም ለሐዋርያዊ አገልግሎት የደከሙት፣ ኢትዮጵያን በዮዲት ዘመን ከገባችበት የትምህርት ጨለማ በስብከት ያበሩላት፣ ደቀ መዝሙሮቻቸውን በአራቱ መዓዝን ያሠማሩት፣ ሐዲስ ሐዋርያ ተክለ ሃይማኖት የጸለዩበት፣ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትና ያረፉበት የተቀደሰ ሥፍራ ነውና፡፡ አሁን ያለውን ሕንፃ ጨምሮ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ታሪክ ውስጥ 10 አብያተ ክርስቲያናት በተከታታይ ተሠርተዋል፡፡ የመጀመሪያው የገዳሙ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው ዔላም በተባለውና ከደብረ አስቦ ወረድ ብሎ በሚገኘው ሜዳማ ሥፍራ ላይ ሲሆን ዘመኑም በ1362 ዓም ነው፡፡ ያሳነጹትም አራተኛው እጨጌ ሕዝቅያስ ናቸው፡፡ አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያን ያሠሩት ደግሞ በ1955 ዓ.ም. በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት ነው፡፡ ዐሥሩም የደብረ ሊባኖስ አብያተ ክርስቲያናት ከገዳሙ የደስታና የመከራ ታሪክ ጋር የተያያዘ ምክንያት አላቸው፡፡ አንዳቸውም ቢሆኑ ገንዘብ አለን፣ ሞያ አለን፣ ቦታ ጠበበን፣ ተብለው የተሠሩ አይደሉም፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን የተሠራው አባታችን ቀድመው በተናገሩት መሠረት ዐጽማቸው ከደብረ አስቦ የሚፈልስበት የትንቢት ጊዜው በመድረሱ ነው፡፡ አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያን የተሠራው ደግሞ ግንቦት 12 ቀን 1929 ዓም. የአባታችንን የፍልሰተ ዐጽም በዓል ለማክበር የተሰበሰቡትን ካህናትና ምእመናንን የግራዝያኒ ጦር ጨፍጭፎ፣ ቤተ ክርስቲያኑን አቃጥሎ፣ ቅርሱን ዘርፎ በመሄዱ የተነሣ ገዳሙ በመዳከሙ ምክንያት እንደገና እንዲሠራ ጻድቁ የላኳቸው መናንያን ለንጉሡ በመናገራቸው ነው፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም ክልል ከ30 በላይ እጨጌዎች የተቀበሩበት፣ የብዙ ቅዱሳን ዐጽም ያረፈበት፣ ታላላቅ ጉባኤያት የተደረጉበት፣ ከዕብራይስጥና በዐረብኛ ሳይቀር ትርጓሜ መጻሕፍት ሲሰጡ የኖሩበት(ዛሬ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጣቸው አጥተው ትምህርት ቤቶቹ ቢዳከሙም)፣ አያሌ ቅዱሳት መጻሕፍት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎሙበት ቅዱስና ታሪካዊ መካን ነው፡፡ በዚህ ቦታ የሚሠሩ ግባታዎች የጥንቱን ታሪክ እንዳያጠፉ፣ ወደፊት የሚደረገውን የአርኬዎሎጂ ጥናት እንዳያደናቅፉ፣ የገዳሙን ታሪካዊ ክብር እንዳያጎድፉ ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የገዳሙ አስተዳደር ገድል ቤቱ ጠበበ ብሎ በማሰብ ተጨማሪ ሕንጻ (የገድል ማንበቢያ) ለመሥራት በዕቅድ ላይ ነው፡፡ በገዳሙ ቅጽር የለጠፈው የሥራ ማሳወቂያ ሰሌዳም ይህንኑ ያውጃል፡፡ የሥራው ዓላማ መልካም ቢሆንም ሊሠራ የታሰበው ነገርና ሊሠራ የታሰበበት ቦታ ግን ሁላችንም ‹ኡኡ፣ የተክልየ ያለህ› እንድንል የሚያደርገን ነው፡፡
ገዳሙ ሊሠራ የለጠፈው ሰሌደ
ገዳሙ የለጠፈው ሰሌዳ እንደሚገልጠው ሊሠራ የታሰበው ሕንጻ በ1955 ዓም በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የተሠራውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ራሱን የሚደግም ነው፡፡ለምን? ሁለት ተመሳሳይ ሕንጻዎችን በአንድ ግቢ ውስጥ ማቆም ለምን አስፈለገ? በአኩስም ጽዮን ሁለት ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ዐፄ ፋሲል ያሠሩትና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያሠሩት፡፡ ዐፄ ፋሲል የጥንቱን ደብረ ብርሃን ሥላሴና ዳጋ እስጢፋኖስ የተሠሩበትን መንገድ ተከትለው ሲያንጹ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ በቁስጥንጥንያ የነበረችውን፣ በ381 ዓም ጉባኤ ቁስጥንጥንያ የተደረገባትን፣ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ያስተማሩባትን፣ በኋላ ቱርክ መስጊድ ያደረጋትን ሐጊያ ሶፍያን የምትመስል ክብ ቤተ ክርስቲያን አሠሩ፡፡ መንታ ቤተ ክርስቲያን ግን አላቆሙም፡፡
ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ በሮሐ፣ በአንድ አካባቢ ላይ 11 አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጽ መንታ አድርጎ የሠራው ሕንጻ የለም፡፡ እንዲያውም በመጽሐፈ አኩስም የተጻፈላትን የጥንቷን የአኩስም ጽዮን የሕንጻ ዲዛይን አስመጥቶ ቤተ ማርያም ላይ እንዲተገበር በማድረጉ ሲደነቅ ይኖራል፡፡ ደብረ ሊባኖሶች ምንድን ነው የነካብን? እንዲህ ያለውንስ ሥርዓት ከየትኛው ታሪክ ነው የተማሩት? ቤቱ የታሪክ፣ የተውፊትና የሥርዓት ቤት ነበርኮ!
እጅግ የሚደንቀው ደግሞ ይኼው በመልክና በቅርጽ ተመሳሳይ የሆነ ሕንጻ የሚሠራው በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ሃምሳ ሜትር በማይርቅ ቦታ ላይ የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ለዚያውም አሳንሶ መድገም ታሪክ ማጥፋት እንጂ ታሪክ መሥራት ሊሆን አይችልም፡፡ የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን የሠሩት ዐቃጆች(አርክቴክቶች) ከሩቅ ከሚታየው ፏፏቴ ጋር ተነጻጽሮ እንዲሠራ ያደረጉበት ምክንያት ነበራቸው፡፡ አላቫሬዝ በመጽሐፉ እንደተረክልን ይኼ ወንዝ የደብረ ሊባኖስ መታወቂያውና መገለጫው ነበር፡፡ እንደነ እጨጌ ዕንባቆም ያሉት ተሻግረውት የመጡት ወንዝ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያታቸው ደግሞ ለ300 ዓመታት ደብረ ሊባኖስ ጠፍ ሆና ስትኖር የአባታችንን መቃብር የሚጠብቁ መናንያን ዐጽሙ ያረፈበትን ቦታ ለመለየት የተጠቀሙበት የመለያ ምልክት ስለነበረ ነው፡፡(ስለዚህ ጉዳይ በቅርቡ በሚታተመው የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የደብረ ሊባኖስ ታሪክ መጽሐፍ ላይ በሰፊው እመለስበታለሁ)
አሁን ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራበትን ቦታ በተመለከት ታሪካዊ መዛግብት እንዲህ ይሉናል ‹በዐፄ ምኒልክ ዘመን በ1895 ዓ.ም. የደብረ ሊባኖስን ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ ሕንጻው ሲጀመር እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስና ክቡር ራስ አባተ (ቧ ያለው) ለሥራው ተመድበው ነበር፡፡ ሥራው ተጀምሮ አካባቢው ሲቆፈር በዛሬው ቤተ ክርስቲያን መሠረት ላይ በስተ ደቡብ በኩል ‹‹ተ›› የሚል ጽሕፈት ያለበት መቃብር ተገኘ፡፡ እጨጌው ይህ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት መቃብር ሊሆን ስለሚችል ከፍተን እናውጣውና ተአምራት ያድርግ ቢሏቸው ራስ አባተ ቧ ያለው ግን ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም በላዩ ላይ ተሠራ[2]፡፡ በ1955 ዓ.ም. የአሁኑ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራም በዚያው መሠረት ላይ ነው የታነጸው፡፡›
በመሆኑም አሁን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በሠራበት አካባቢ የሚደረግ ቁፋሮ ሁሉ ታሪካዊ ምክንያት ሊኖረውና ሊገኙ የሚችሉ ጥንታዊ ቅርሶችን አደጋ ላይ የማይጥል መሆን አለበት፡፡ ቦታው በግሬደር የምንንደው ተራ ቦታ አይደለምና፡፡
ሌላም ጉዳይ አለው? ሁለተኛው ተመሳሳይ ሕንጻ የጥንቱን ሕንጻ ኪነ ጥበባዊ፣ ታሪካዊና መካናዊ(Placement) የሚቀንስና የሚያሳጣ ነው፡፡ ያንን በፎቶ ግራፍ ስናየው፣ በፖስተር ስናትመው ግርማ ሞገስ የሚኖረውን፣ በደን የተከበበውን፣ ከኋላው በበጋ ተራራው፣ በክረምት ፏፏቴው የሚያጅበውን ደብረ ሊባኖስ የሚያጠፋ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ በኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተመደቡ ከተወሰኑ ወራት በኋላ በኢየሩሳሌም አግኝቻቸው ነበር፡፡ ብጹዕነታቸው አጥብቀው ያዘዙኝ ነገር ቢኖር ከኋላው ጋራውና ፏፏቴው የሚታይበትን የደብረ ሊባኖስን ቤተ ክርስቲያን ፎቶ እንድልክላቸው ነበር፡፡ ዘወትር በዓይነ ኅሊናቸው የሚታያቸው ያ መሆኑን ገልጠውልኛል፡፡ ታድያ ምነው ብጹዕ አባታችን ታሪኩ ሲጠፋ በዝምታ ተመለከቱት? እባክዎን ነገሩን ደግሞው ያስቡበት፡፡
ደግሞስ የቀደሙት አበው በዘመናቸው ሠሩ፡፡ ያ ታሪካችንም ሀብታችንም ነው፡፡ እኛ ደግሞ በዘመናችን የዘመናችንን ለምን አንሠራም? የእነርሱን ታሪክ፣ የገዳሙን ዝናና ታላቅነት፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ቦታ (ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት እስከ እጨጌ ወልደ ኪዳን ድረስ ከ52 በላይ እጨጌዎች ነበሩት)፣ ከሌሎች ገዳማት በተለየ ለ300 ዓመታት ያህል ጎንደር ላይ የነበረ ገዳም መሆኑን የሚያሳይ ዲዛይን አሠርተን፣ ያንንም በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በመልክዐ ምድር፣ በአርክቴክቸር፣ ባለሞያዎች አስገምግመን፤ ለቀጣዮቹ 50 ዓመታት የሚያገለግል ሕንጻ መሥራት ነበረብን እንጂ ሌሎች የሠሩትን ማጥፋት ይገባን ነበር?
በደብረ ሊባኖስ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ ቦታ ያላት፣ ጻድቁም ሲጸልዩባት የኖረችው፣ ራሷን በተመለከተ ‹ዜና ምጽአታ ለታቦተ ማርያም› የሚል መጽሐፍ የተጻፈላት ‹ታቦተ ማርያም› አለች፡፡ የመጀመሪያው የደብረ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያንም የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ሦስተኛዋና በእጨጌ ዮሐንስ ከማ ዘመን(1406-1420) የተሠራችው ቤተ ክርስቲያንም  ቅዳሴ ቤቷ የተከበረው ሰኔ 21 ቀን ከጥንቱ ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያን ጋር በማስተሣሠር ነበር፡፡ ታድያ ምነው ሌላ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ካስፈለገ እንኳን ታሪካዊነቱን ሳይለቅ፣ የአባታችንንም ሥራ በሚያስታውስ መልኩ ለእመቤታችን ታቦት ቤተ ክርስቲያን ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ሊገናኙ በማይችሉበት ቦታ ላይ በገዳሙ ክልል ለምን አይሠራም?
ይህንን ጥያቄ ስናነሣ ሁለት መልሶች ከገዳሙ ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያው ‹የምንሠራው ገድል ቤት ነው› የሚል ነው፡፡ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተን የምንሠራውን ሕንጻ ገድል ቤት ብቻ እናደርገዋለን ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡ ነገ ታቦት እናስገባበታለን፡፡ ያ መሆኑ ካልቀረ ደግሞ ጎን ለጎን ከማድረግ ራቅ አድርጎ በንግሥ ጊዜ የሚመጣውን ሕዝብ ሊያካትት የሚችል ሰፊ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ነው፡፡ ሁለተኛው መልስ ደግሞ ‹በገዳሙ ክልል ገደል እንጂ ምቹ ቦታ የለም› የሚል ነው፡፡ ዘመኑ 21ኛው መክዘ መሆኑን የዘነጋ መልስ፡፡ እንኳን በደብረ ሊባኖስ በዜጋመል መሥራት ይቻላል፡፡ መመካከሩና ተረጋግቶ ማቀዱ ካለ፡፡
ደብረ ሊባኖስ የሚታወቀው በምንኩስናና በትምህርት ማዕከልነቱ ነው፡፡ ታላላቆቹ ነገሥታትም በዘመኑ ትልቅ ያሉትን ቤተ ክርስቲያን የሚሠሩት ስብሐት እንዲወርድበት ትምህርት እንዲሰጥበት ነው፡፡ ዐፄ ምኒልክ የደብረ ሊባኖስን ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለንግሡ በወረዱ ጊዜ የሆነውንና ‹ከገድለ ተክለ ሃይማኖት ጋር የተገኘ መዝገብ› የመዘገበልንን ልጥቀሰው ‹ዐፄ ምኒልክ በ1885 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሠራዊት በዐዋጅ ሰብስበው ደብረ ሊባኖስ ወረዱ፡፡ ከሠራዊቱም ብዛት የተነሣ ደጋውም ቆላውም ለሰፈር ጠቦት ነበር፡፡ በግንቦት 12 ቀን የተክለ ሃይማኖት በዓለ ፍልሰተ ዐጽም በሚከበርበት ቀን ምሳሌ በሌለው አከባበር ታቦቱን አንግሠው ካዲሱ ቤተ ክርስቲያን አግብተው ታላቅ ሥነ በዓል ተደረገ፡፡ መኳንንቱም መሳፍንቱም ባላገሩም አንክሮ ባለው ደስታ እየተደሰቱ ሰነበቱ፡፡ በሁለተኛው ቀን ንጉሡ ቤተ ክርስቲያኑ በጣም ትልቅ ነበርና፤ ‹‹መምህራን ይሰብሰቡ መወድስ ማኅሌት ስብሐተ ነግህ ጾመ ድጓ ይቆምበት፤ የባላገር  ልጅ እየተማረ ደጅ ይጥና፤ እኔ ማደሪያ ቀለብ እሰጣለሁ›› ብለው ዐዋጅ አናገሩ፡፡ መነኮሳቱ ተሰብስበው፤ ‹‹ይኸማ ከሆነ ገዳምነቱ ይቀር የለምን?›› ብለው ቢያመለክቱ፤ ‹‹ይኸን ያህል ቤተ ክርስቲያን ሠርቼ እናንተ ምን ታደርጉበታላችሁ? ለናንተስ ምርፋቅ መስቀል ቤት ሠርቼላችኋለሁ ከዚያው ሳታት ቁሙ፡፡ ዳዊት ድገሙ አሏቸው፡፡›
የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን በመንትያው ከማበላሸት ገዳሙን በሚገባ ዐቅድ ሰጥቶ መናንያንና ዓለማውያን እንዳይገናኙ ክልል መከለል፣ ለገዳማውያኑ የሚሆን አነስተኛ ቤተ መቅደስ በመናንያኑ ክልል ውስጥ መሥራት፣ ለሕዝቡ የሚሆን ደግሞ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሰፊ ቦታ ፈልጎ መሥራት ይገባል፡፡ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ (አንዳንዶች እንደሚገምቱት 75 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል) ሕንጻ ሠርቶ ገድል ቤት ብቻ ነው የሚለውን ንጉሥ ምኒልክ አለመስማታቸው መልካም ነው፡፡
ስንጠቀልለውም የገዳሙን ክልል በባለሞያ ዕቅድ እንሥራለት፣ የገዳማውያኑን፣ የጠበልተኛውን፣ የመቃብሩን፣ የሱባኤተኛውን፣ የትምህርት ቤቶቹን፣ የቢሮዎቹን ቦታ በአጥር እንለየው፣ አንደኛው ወደ ሌላው አይለፍ፡፡ በተለይ ወደ መናንያኑ፡፡ ለሕዝቡ በመደብነው ቦታ ላይ የዘመኑን አርክቴክቸርና የግንባታ ጥበብ ተጠቅመን አሁን ያለውን ምእመን ቁጥር የሚመጥን ሰፊ ቤተ ክርስቲያን እንሥራ፤ ካስፈለገም ቤተ ክርስቲያኑን ፎቅና ምድር ቤት አድርገን ታቹን ለገድል ቤት እንጠቀምበት፤ እግረ መንገዳችንንም በሚገባቸው ባለሞያዎች አስጠንተን የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን የማንበርያ ሥራ (maintenance) እንሥራ፡፡ አዲስ የተመደቡት ጸባቴ እና ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ ጉዳዩን እንዲያዩት አደራ እላለሁ፡፡
በምንም መልኩ ግን የጥንቱን ታሪክ የሚያደበዝዝ፣ ከደብረ ሊባኖስ ታሪክና ክብር ጋር የማይመጥን፣ ቅርሶቻችንን የሚጎዳ ግንባታ መሥራት የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ከሚያጠፉ ጋር መተባበር ነው፡፡ ይህን ጥፋት በዕውቀታችሁና በገንዘባችሁ እየፈጸማችሁ ያላችሁ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን የተክልየ ዐጽም ይፋረዳችኋል፡፡



‹ድኻ ወርቅ አይግዛ›

$
0
0
‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› ይላሉ የምንዳዬ እናት አባዬ፡፡ ‹ምነው አባዬ ድኻ በመከራ የገዛውን ወርቅ እንዴት ይጥፋበት ይላሉ› ብለን ሞገትናቸው፡፡ ‹እይውልህ እኛ ሠፈር አራት ኪሎ አዲሴ የሚሏት አንዲት ጎረቤታችን ነበረች፡፡ ቁርስ፣ ምሳና እራት የተዘበራረቁባት፡፡ ለነገሩ ላለው ነው እንጂ ለሌለው ሰው ምግብ ስሙ ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ምግብ - ቁርስ፣ ምሳ እራት የሚሆነው በሰዓቱ ስታገኘው ነው፡፡ በሰዓቱ ካላገኘኸው ያው ምግብ ብቻ ነው፡፡ ከድንጋይ ትፈልቅቀው፣ ከሳጥን ትስረቀው ሳናውቅ አንድ ቀን በድንገት አራት ኪሎ ወርቅ ቤት ሄዳ ወርቅ ገዛች ተብሎ ተወራ፡፡ የቡና ሴቶች ‹ግማሽ ግራም ወርቅ ገዝታ በከረጢት ቋጥራ አስቀመጠችው› ብለው ያሽሟጥጧታል፡፡ 

የገዛች ለት ምሽት እኛ ቤት ቡና ተጠርታ መጣችልህ፡፡ ሴቱ ሁሉ ግጥም ብሏል፡፡ ተርብ ተርቦቹ ደግሞ የዛን ቀን አንድም ሳይቀሩ ተለቃቅመው መጥተውልሃል፡፡ ገና ወደቤት ስትገባ ከሁላችን ለይታ ‹ወይዘሮ የወርቅ ውኃ ደኅና አመሹ› አትልልህም፡፡ አሁን በእርሷ ቤት ወርቅ መግዛቷን ልትነግረን እኮ ነው፡፡ ተያየንና ‹ኡኡቴ› ብልን ዝም አልን፡፡ ገና ከጠፈር ወንበሩ ላይ ሳትደላደል ‹እኔኮ በዚህ ዘመን ድኻ እንዴት ይኖራል፤ እኛስ እሺ› ብላ አረፈችው፡፡ ‹እናንተ እነማን ናችሁ› አለቻት እቴኑ በዓይኗ ቂጥ እያየቻት፡፡ ከምንም ሳትቆጥራት ‹ኧረ እንዴው ተውኝማ፣ ወርቅ እንደዚህ ሰማይ ይንካ› አለች ቆሎውን እየዘገነች፡፡ ‹እኛ ወርቅ ዘመን እንጂ ወርቅ ምን ያደርግልናል› አሏት እማማ ትጓደድ፡፡ ላምሮት ተናደደችና ‹ምን ዳር ዳር ትያለሽ፣ ወርቅ ገዝተሻል› አለችና አፈረጠችው፡፡ ሴቱ ሁሉ አንድ ጊዜ ቤቱን በሁካታ ሞላው፡፡ መቼም እርሷ አፍርጠው ናት፡፡  

ሳቃችንን ሳንጨርስ ‹ቆይ ቆይ እስኪ› አለች አዲሴ ጆሮዋን እንደ አንቴና ሰቅላ፡፡ መቼም ከአራት ኪሎ ሠፈር ጯሂና አስጯሂ አይጠፋም ብለን ጸጥ አልን፡፡ አራት ኪሎ ጠብና ዕርቅ የተለመደ ነው፡፡ ተደባዳቢና ገላጋይ በየተራ ነው፡፡ ዛሬ ትደባደባለህ፣ ነገ ደግሞ በተራህ ገላጋይ ትሆናለህ፡፡ ሁላችን ኮንዶሚኒየም ላይ እንደተሰቀለ ዲሽ ጆሮአችንን አከታትለን ብንሰቅልም  የመንገደኛ ተረብ ብቻ ነው የምንሰማው፡፡ አዲሴ ተነሣችና ሳንዱቁ ላይ በልብስ ተሸፍኖ የተቀመጠውን ራዲዮ እስከ አንጀቱ  ድምጹን ለቀቀችው፡፡ አበደች እንዴ ብለን በግራ ዓይናችን ገላመጥናት፡፡ 

‹ዛሬ በዋለው የዓለም ገበያ› ይላል ራዲዮኑ፡፡ እርሷ እዚያው እንደተለጠፈች ናት፡፡ እዚህ አራት ኪሎ ያለው የጉልት ገበያ የሚናፍቃት ሴትዮ የዓለም ገበያ ምን ሊያደርግላት ነው ብለን ሳቅን፡፡ ለወትሮው በዱቤ የሰጧት እንዳያንቋት ገበ ድርሽ አትልም ነበር ነበር፡፡ እንዲያውም እማማ ትጓደድ ‹አዲሴኮ ገበያ ብቻ ሳይሆን ገበያው የሚባል ሰውም ትፈራለች› እያሉ ይተርቧት ነበር፡፡ ራዲዮው ‹ዛሬ በዓለም ገበያ ወርቅ በካራት ይህን ያህል ተሽጧል› ሲል ‹እንዴው በደኅና ጊዜ ባልገዛ ይቆጨኝ ነበር፡፡ ለካስ ሰው ልጁን ወርቁ፣ ወርቂቱ፣ ወርቄ፣ ወርቅ አገኘሁ፣ ወርቅ አለማሁ፣ ጥሩ ወርቅ፣ አመለ ወርቅ እያለ የሚጠራው ወርቅ እየተወደደበት ነው› አለችና የግራ እጅ መዳፏን በቀኝ አራት ጣቶቿ ደበደበችው፡፡

ከዚያ በኋላ አዲሴን ማን ይቻላት፡፡ ከሱቅ በዱቤ ዕቃ ስትወስድ እንደ ድሮው መለመን፣ መለማመጥ ቀረ፡፡ ‹ማነህ ባለ ሱቅ፣ እስኪ አንድ አምስት ኪሎ ስኳር አምጣ› ትለዋለች፡፡ ‹እንዴ እማማ አዲሴ፣ በኋላ ባይከፍሉኝስ፤ ያለፈውን በመከራ አይደል እንዴ የከፈሉኝ› ሲሏት ‹ያለፈው አለፈ፣ በቃ እናንተ ሰው ይቀየራል ብላችሁ አታስቡም፤ አምጣ ባክህ፣ ቢበዛ ወርቄን ሽጬ እከፍልሃለሁ› ትላቸዋለች፡፡ ኧረ እንዲያውም አንድ ቀን አንድ ቄስ በዚያ ሲያልፉ ጠራቻቸውና ‹ዛሬ ሲያቃዠኝ አድሯል ይርጩኝ› ትላቸዋለች፡፡ ‹የክርስትና ስምሽ ማነው› ይሏታል ‹እኅተ ወርቅ› ትላቸዋለች፡፡ ቄሱ ደንግጠው ‹እኅተ ማርያም› ማለትዎ ነው› ይሏታል፡፡ ቀኝ እጇን ወደ ጎን እያውለበለበች ‹እርሱ የነዛ የነዛ ስም ነው› አለቻቸው፡፡ ‹ታድያ እኅተ ወርቅ፣ አይ፣ ያልተማረ ሰው ሰጥቶዎት እንዳይሆን› ይላሉ ያልገባቸው ቄስ፡፡ ‹ይኼው ነው አባቴ፣ካልተረዱት ይተውት› አለቻቸው፡፡ 

ድሮ አዲሴ ቀበሌ መሄድ አትወድም ነበር፡፡ ‹እነርሱ መዋጮ ብቻ ነው ሥራቸው› ትላለች፡፡ ወርቅ በገዛች ሰሞን ‹ምነው ስብሰባ በተጠራ፣ ልክ ልካቸውን ነበር የምነግራቸው› ማለት አበዛች፡፡ በልኳ ለብሳ የማታውቅ ሴትዮ ድንገት ተነሥታ ልክ ልክ ነጋሪ ሆችልህ፡፡ የስብሰባው አጀንዳ ‹ሴቶች በልማት ይሳተፉ› የሚል ነው፡፡ አዲሴ ተነሣችና ‹ለሴቶች ዕድገት ወሳኙ ወርቅ ነው፡፡ እኛ ሴቶች ከወንዶች እኩል እንድንሆን ወርቅ ያስፈልገናል› ስትል አንዷ ‹ታዲያ እንደ መሠረት ደፋር አትሮጭም፣ ማን ከለከለሽ› ብላ አሳቀችባት፡፡ ‹የሴቶችን ችግር ለመፍታት ስብሰባ ሳይሆን ሴቶች ወርቅ የሚገዙበት መንገድ መመቻቸት አለበት› ብላ ስትቀመጥ ሰብሳቢዋ ምናልባት መልስ ቢሰጡ ብላ ነው መሰለኝ ለወይዘሮ ወርቅ ያንጥፉ ዕድል ሰጠቻቸው፡፡ ሊያነጥፉላት ነው፡፡ 

‹ድኻ ወርቅ አይግዛ፣ ከገዛም ይጥፋበት› ትል ነበር አያቴ፡፡ ወ/ሮ አዲሴ ትናንት ግማሽ ግራም ወርቅ ስለገዛሽ ወሬሽ ሁሉ ምነው ወርቅ ብቻ ሆነሳ› ሲሉ ሁሉም የኮረኮሩት ያህል በሳቅ ፈነዳ፡፡ ‹ባለፈው እዚህ ሠፈራችን ያለ ጎረምሳ መጽሐፍ አሳተመ ተብሎ ደስ አለን፡፡ ምንም ቢሆን ያሳደግነው ልጅ ነው ብለን፡፡ እሱ ግን ፊደል የፈጠረ እንጂ መጽሐፍ ያሳተመ አልመሰለውም፡፡ ቡና ልንጠጣ ቤታቸው ስንሄድ የዛሬው የቡና ቁርስ የኔ ግጥም ነው ብሎ ግጥም ሊያነብልን ጀመረ፡፡ ምነው ሸዋ! ሐዲስ ዓለማየሁም እንዲህ አላደረጉ፡፡ ደግሞኮ
አራት ኪሎ ኪሎ
አራት ኪሎ ኪሎ
የድንጋይ አሎሎ› የሚል ግጥምኮ ነው፡፡› ሰብሳቢዋማ ከጠረጴዛው መነሣት እስኪቸግራት ተደፍታ ነው የሳቀችው፡፡ ያው ወ/ሮ ወርቅ ያንጥፉ ከሳቅክላቸው ማንጠፍ ነው፡፡ ‹ይባስ ብሎ ቀበሌ አዳራሽ ልጆቹን ሰብስቦ ‹ታዋቂው ደራሲ› የሚል ፖስተር ለጥፎ ልምድ አካፍላለሁ ይላቸዋል፡፡ ‹እርሟን ጠምቃ፣ ሰጠች ጠልቃ› አሉ፡፡
አንበሳ ተኝቶ ፍየል ዘለለችው
ንቆ ቢያሳልፋት ሞኝ አደረገችው› አለ የሀገሬ ሰው፡፡ በብጥሌ ወረቀት አላሳተምንም እንጂ ስንት ግጥም ነበረንኮ፡፡
መቶ ታምሳ ዜማ የሚሰማብሽ
ድኻ ባለጠጋ የማይጠፋብሽ
ፀሐይ እንደ እንግሊዝ የማይጠልቅብሽ
የሁሉ እኩል ሀገር አራት ኪሎ ነሽ› ብሎ እንደመግጠም ‹አራት ኪሎ ኪሎ፣ የድንጋይ አሎሎ› ብሎ አሎሎ የሚያህል ግጥም የጻፈን ልጅ ልምድ አካፍላቸው ማለት በአሎሎ ደብድባቸው እንደ ማለት ነው፡፡› ሳቅና ጭብጨባ አጀባቸው፡፡ ድኻ ወርቅ አያግኝ ማለት ይኼ ነው፡፡ አሁን እኛን የቸገረን እንዲህ እንደ አዲሴ የሚባርቅባቸው ድኾች ናቸው፡፡ ሥልጣን አይቶ ለማያውቀው ሥልጣን ትሰጡትና ይባርቅበታል፡፡ የቢሮውን መኪና በሠፈራችን እያፈጠነ ካላሳየን ሞቶ ይገኛል፡፡ በታክሲ ሲሰቃይ ለከረመ ሰው ቪ ኤይት መኪና መስጠት በውኃ ጥም ለከረመ ሰው ቅቤ አቅልጦ እንደማጠጣት ነው፡፡ ሁለቱም ጤና አይሆናቸውም፡፡ አበሉ፣ ስብሰባው፣ ግብዣው፣ ፊርማው፣ ብርቅ ይሆንበታል፡፡ ቀበሌውና ክፍለ ከተማው የግል ንብረቱ ይመስለዋል፡፡ እኛም አሽከሮቹ እንመስለዋለን፡፡ የተሾመ ሰሞን ብርቅ ስለሚሆንበት ያገኘውን ገንዘብና መሬት ይጠበጥበዋል፡፡ ያልራሰ መሬት ማለትኮ ነው፡፡ ምን ውኃ ይመጥነዋል፡፡ ‹አይቶ አያውቅ ዳቦ ፍሪዳው ነው› ይባላል፡፡ አንድ ስብሰባ ላይ አንዲት እንግሊዝኛ የሰማ ዕለት እኛን ሰብስቦ እርሷን ካልተናገረ ይሞታል፡፡ ውጭ ሀገር ሄዶ አንዲት ነገር ካየ፣ ብርቅ ስለምትሆንበት ‹ቻይና ሳለሁ፣ ኮርያ ሳለሁ› እያለ መከራ ያሳየናል፡፡ ድኻ ወርቅ አይግዛ የተባለውኮ ለዚህ ነው፡፡ 

አላያችሁም እንዴ በድንገት ሀብታም የሆነን ሰው፡፡ ሳይነግራችሁ ታውቁታላችሁኮ፡፡ የውሻ ማሠሪያ የሚያህል የአንገት ወርቅ፣ ክብደት መለኪያ የሚሆን የእጅ ሰዓት፣ የሚታይ ከናቴራ፣ ከከናቴራው ላይ አዲስ ሸሚዝ፣ በሸሚዙ ላይ አዲስ ሹራብ፣ በሹራቡ ላይ አዲስ ኮት፣ በኮቱ ላይ አዲስ የውጭ ካፖርት፣ በካፖርቱ ላይ ስካርፕ ደርቦ ታዩታላችሁ፡፡ ይህን ስታዩ ‹ድኻ ወርቅ አይግዛ› በሉና ሽሹ፡፡ መኪና ከገዛማ አይጣልባችሁ፡፡ በግራ እጁ መሪ ይዞ፣ ወንበሩን ወደ ኋላ ስቦ፣ ልጥጥ እያለ፣ የአስፓልት ውኃ እየረጨባችሁ ያልፋል፡፡ 

እና አዲሴ ተይን እባክሽ፣ አንቺ ዛሬ ወርቅ ስትገዥ የችግራችን ሁሉ መፍቻ ወርቅ መሰለሽ፡፡ የክፉ ሐኪም ምክር አትምከሪን፡፡ ክፉ ሐኪም ሥጋው የገጠጠ በሽተኛ በቀበሌ ደብዳቤ በነጻ እየታከመ እያየ ከምግብ በፊትና ከምግብ በኋላ ሦስት ጊዜ የሚዋጥ መድኃኒት ያዛል፡፡ ይህ ማለትኮ ሰውዬውን አትድንም ተስፋ ቁረጥ ማለቱ ነው፡፡ መድኃኒቱንስ በነጻ አገኘ፡፡ ምግቡን ማን ይሰጠዋል? አሁን ያስቸገሩን እንዳንቺ ያሉት ናቸው፡፡ ሲበሉ የበላን፣ ቤት ሲሠሩ የሠራን፣ አበል ሲከፈላቸው የተከፈለን፣ ሲሾሙ የተሾምን፣ የእነርሱ ችግር ሲፈታ የእኛ የተፈታ የሚመስላቸው የአእምሮ ድኾች፡፡ ድኃ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ወርቁ ጠፍቶባቸው ከሥልጣን ሲወርዱ፣ ከሀብት ሲናዱ ምን እንደሚመስሉ አይተናቸዋላ፡፡
ሞቅ አድርገን አጨበጨብንላቸው፡፡ ራሷ ሰብሳቢያችን አጨበጨበች፡፡ እኔም ከእርሷ ወስጄ ‹ድኻ ወርቅ አይግዛ ከገዛም ይጥፋበት› እላለሁ፡፡
አሉኝ የምንዳየ እናት አባዬ፡፡   

የ፳፻፱ ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት እጩዎች

$
0
0

                               


መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ዘርፍ
1.    ዶ/ር መስፍን አርአያ (ለብዙ ዓመታት የዐማኑኤል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ የአእምሮ ሕክምና ባለሞያ) 
2.   አቶ ገመቹ ዲቢሶ(ዋናው ኦዲተር)
3.   አቶ ማቴዎስ አስፋው(የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር)


ሚዲያና ጋዜጠኛነት
1.    እሸቴ አሰፋ (የሸገር ጋዜጠኛ)
2.   ንጉሤ አክሊሉ (ለብዙ ዓመታት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ያገለገለና በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛ)
3.   ሸገር ሬዲዮ ጣቢያ


ማኅበራዊ ጥናት
1.    ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
2.   ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ
3.   ፕሮፌሰር ካሣሁን ብርሃኑ



ለኢትዮጵያ መልካም የሠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች
1.    ቦብ ጌልዶፍ
2.   ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን
3.   ፕሮፌሰር  ጃኮብ ሽናይደር


ቅርስ፣ ባሕልና ቱሪዝም
1.    ጉዞ አድዋ
2.   አቶ ገብረ ኢየሱስ
3.   የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መዛግብት ማዕከል
         

              ሳይንስ
        1.     ዶ/ር ቦጋለ ሰሎሞን (የካንሰር ስፔሻሊስት)
2      .     ሎሬት ዶክተር ለገሠ ወልደ ዮሐንስ(ከዶክተር አክሊሉ ለማ ጋር በመሆን የብልሐርዚያን መድኃኒት ያገኙ)            
3       .   ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ንጉሤ ተበጀ(በአአዩ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር)
      ኪነ ጥበብ(በቴአትር ዘርፍ)
    1.    ተስፋዬ ገሠሠ
    2.   ጌትነት እንየው
    3.   ዓለማየሁ ታደሰ
   
              ንግድና የሥራ ፈጠራ
   1.  ኢንጅነር ጸደቀ ይሁኔ (የፊሊን ስቶን ባለቤት)
   2.አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ (የእሹሩሩ ባለቤት)
   3.ሸዋ ዳቦ (ለ60 ዓመታት በዱቄትና ዳቦ ዘርፍ የሠራ ተቋም)
        

                             መምህርነት
1.    መ/ር ፈቃደ ደጀኔ (ከ1970 ዓም ጀምሮ በመምህርነት በመርሐ ቤቴና አርሲ ያስተማሩ፤ በገጠር ትምህርት ቤት ያሠሩ፣ ልጆችን እየረዱ የሚያስተምሩ)
2.   መ/ር ሰሎሞን ጸደቀ (በወሎ ቦረና፣ ጋሞጎፋ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወለጋ፣ ጉራጌ ዞን ከ1973 ዓም ጀምሮ የሠሩ፤ በገጠር ትምህርት ቤቶችን ያሠሩ፣ ለገጠሩ ሕዝብ የልማት ተቋማትን ያስገነቡ፣ ትምህርታቸው የሚያቋርጡ ተማሪዎች የሚረዱበትን መንገድ የፈጠሩ)
3.   አቶ ማሞ ከበደ ሸንቁጥ (የታወቁ የትምህርት ባለሞያ፣ በተለይም ደግሞ በጎልማሶች ትምህርት ላይ ለውጥ ያመጡ)
      

    በጎ አድራጎት
1.         መቅደስ ዘለለው (የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት ድርጅት(IFSO) መሥራችና መሪ)
2     .  ዳዊት ኃይሉ( የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ባለቤት፤ ለብዙ ችግረኛ ሕሙማን በነጻና በሚችሉት ክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ)
3     .    ሰሎሞን ይልማ (በደብረ ዘይት ከተማ ችግረኞችን በመርዳት የሚታወቅ ወጣት)

Viewing all 266 articles
Browse latest View live


<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>