Quantcast
Channel: የዳንኤል እይታዎች Daniel Kibret's views
Viewing all 266 articles
Browse latest View live

ደብተራ

$
0
0
click here for pdf

 


ከአንዳንድ ሰዎች ጋር የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በተመለከተ ስንነጋገር ‹ደብተራ የጻፈው› ማለት ይቀናቸዋል፡፡ ይሄ ንግግራቸው ከሁለት ስሕተቶች የመነጨ ነው፡፡ አንደኛው ስለ ደብተራ ካለማወቅ ሲሆን ሁለተኛው ስለ መጻሕፍቱ ካለመረዳት የሚመጣ ነው፡፡ ‹ደብተራ› የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉሙ ‹ድንኳን› ማለት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ‹ሐይመት› ከሚለው ቃል ፍች ይለያል፡፡ ‹ሐይመት› ለማንኛውም አገልግሎት የሚውለውን ድንኳን ሲያመለክት ‹ደብተራ› ግን በዋናነት ለቤተ መቅደስነት የሚውለውን ድንኳን ያመለክታል፡፡ ‹ደብተራ ኦሪት› - የብርሃን ድንኳን እንዲል፡፡ 

በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ላይ ነገሥታቱ ከሀገር ሀገር ሲጓዙ አብራቸው የምትጓዝ የጸሎት ታቦት ነበረቻቸው፡፡ ለዚህች ታቦት የምትሆን ድንኳን አዘጋጁ፡፡ ታቦቷ በቤተ መንግሥት ግቢ ተተክላ ትቀመጥና ንጉሡ ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀስ ተነቅላ ትንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህች የቤተ መንግሥት የድንኳን መቅደስ ውስጥ ለአገልግሎት የሚመረጡት በዕውቀታቸውና በንጽሕናቸው የተመሰገኑ ነበሩ፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አባት በዚህች ድንኳን ከሚያገለግሉ ካህናት ወገን ነበረ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በዚህች የድንኳን ቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግሏል፡፡ በዚህች ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት ካህናት አንዱ ሥራቸው ንጉሣውያን ቤተሰቦችን ማስተማር ስለነበር አባ ጊዮርጊስ የዐፄ ዳዊትን ልጆች ሲያስተምር ነበር፡፡ 

በዚህች የቤተ መንግሥት መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ‹በማደሪያው አዳሪው፣ በአዳሪውም ማደሪያው ይጠራል› በሚባለው መሠረት በደንኳኗ (በደብተራ) እነርሱም ‹ካህናተ ደብተራ› እየተባሉ መጠራት ጀመሩ፡፡ ቆይቶም ‹ካህናት› የሚለው ስም ተጎርዶ ‹ደብተራ› እየተባሉ ብቻ ተጠሩ፡፡ ከመነሻው ደብተራ ማለት በዕውቀትና በሕይወት ተመርጦ የቤተ መንግሥቱን የደብተራ ቤተ መቅደስ ለማገልገል የተሰየመ ሊቅ ካህን ማለት ነበር፡፡ 
ካህናተ ደብተራ ከንጉሡ ጋር የተሻለ ቀረቤታ በማግኘታቸው በኋላ ዘመን የርስትና የሹመት ተካፋዮች ሆኑ፡፡ ይህን ላለማጣት ሲሉም አንዳንዶቹ ቀኖናው ከሚያዛቸው ይልቅ ንጉሡ የሚያዛቸውን መቀበል ጀመሩ፡፡ በዚህ የተነሣም ካህናተ ደብተራ ለንጉሡ የሚያደሉና ለእውነት የማይቆሙ እየሆኑ በመምጣታቸው እንደነ አባ በጸሎተ ሚካኤል ያሉ አበው በድፍረት ወቅሰዋቸው ነበር፡፡ በኋላ ዘመን ደግሞ አንዳንዶቹ ከማኅበረሰቡ በተሻለ የተማሩ መሆናቸውን በመጠቅም ጥንቆላና አስማት እንችላለን በማለታቸው ‹ደብተራ› የሚለው ስም የምሁርነት ስም መሆኑ ቀርቶ ከጥንቆላና መተት ጋር የተያያዘ ስም እየሆነ መጣ፡፡

‹ደብተራ› የሚለው ስም አጠፋፍ ›ሐኪም› ከሚለው ስም አጠፋፍ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ‹ሐኪም› የሚለው ስም ትርጉሙ ‹ብልህ፣ ጠቢብ› ማለት ነው፡፡ ሙያን ሳይሆን ጥበብን የሚመለከት ነበር፡፡ ‹ወስመ መምህሩ ዘመሀሮ ጥበበ አርስጣጣሊስ ሐኪም› ይላል፡፡ ‹ጥበብን ያስተማረው መምህሩ ጠቢቡ አሪስጣጣሊስ ነው› ማለቱ ነው፡፡ በዐረብኛም ሆነ በእብራይስጥ ትርጉሙ ይሄው ነው፡፡ የእስልምና ወርቃማው ዘመን በሚባለው ጊዜ ‹ሐኪም› ማለት በእስልምና ሃይማኖት፣ በሳይንስ፣ በመድኃኒትና በፍልስፍና ሁለገብ ዕውቀት ያለው ጠቢብ ሰው ስያሜ ነበር፡፡ በዕብራይስጥ ቋንቋም ሁለገብ ዕውቀት ላለው የሃይማኖት መሪ የሚሰጥ ስም ነው - ሐኪም፡፡
በሀገራችን ‹ሐኪም› የሚለው ስም ለጠቢብ የሚሰጥ ስም ነበረ፡፡ በኋላ ግን ባሕላዊ መድኃኒት ለሚያውቅ ባለሞያ ሁሉ መሰጠት ተጀመረ፡፡ በየጋዜጣው ዛሬ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ‹ሐኪም እገሌ› እያሉ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት ለዚህ ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ሲጀመርም በሞያው የተሰማሩት በዚህ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህን ማስታወስ ለዚህ ይረዳል፡፡ አሁን አሁን ብዙዎቹ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ይህንን ስም ስለሚጠቀሙት ስሙ እንደ ደብተራ ሁሉ ከጥበብና ሞያ ይልቅ ከጥንቆላ ጋር የመያያዝ ዕጣ እየገጠመው ነው፡፡

የደብተራም ዕጣው እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ‹ዐዋቂ፣ ጠቢብ፣ የተመረጠ› ነበር ትርጉሙ፡፡ በኋላ ግን ግብር ስምን ያጠፋልና የአንዳንድ ‹ደብተሮች› ሥራ ስሙን አጠፋው፡፡ ያም ቢሆን ግን በነባሩ ማኅበረሰባችን ደብተሮች የተሻለ የትምህርት ደረጃ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ እነ ደብተራ ዘነብንና እነ ደብተራ አሰጋኸኝን ከቀድሞው፣ እነ ደብተራ ኅሩይ ወልደ ሥላሴንና እነ ደብተራ ዮፍታሔ ንጉሤን ከቅርቡ ማስታወስ ይህንን ያጎላዋል፡፡

እነዚህ ደብተሮች አንዳንድ ጊዜ የሕይወት መሰናክል ቢገጥማቸውም በዕውቀታቸው ግን የሚታሙ አይደሉም፡፡ አንዳንዴም ‹ዕውቀት ያስታብያል› እንዲል መጽሐፉ ወደ መሰናክሉ የሚወስዳቸው ዕውቀታቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ታሪከ ነገሥቱን፣ ዜና መዋዕሉንና ለቤተ መንግሥቱ የቀረቡ ድርሳናቱን የመጻፉ ዕድል የደብተሮች ሲሆን ከገዳማዊ ሕይወት ጋር የተገናኙ የጸሎት፣ የዝማሬ፣ የገድል፣ የመልክዕና የውዳሴ ድርሳናትን የመጻፍ ዕድል ደግሞ የገዳማውያኑ ሊቃውንት ነበረ፡፡ ሁለቱንም ሊቃውንት አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር በዘመኑ ዕውቀት የበለጸጉ መሆናቸው ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ቤተ መንግሥቱንም ገዳማዊ ሕይወቱንም የሚያውቁ ሊቃውንት ይገኛሉ፡፡ መነሻቸው አንደኛው ይሆንና ወደሌላው ይሄዳሉ፡፡ ከገዳሙ ወደ ቤተ መንግሥቱ (ልክ አንደ አባ ባሕርይ) ወይም ደግሞ ከቤተ መንግሥቱ ወደ ገዳሙ (እንደ ቅዱስ ያሬድ)፡፡

የቀድሞ ጸሐፍት አያሌ መጻሕፍትን ማገላበጥ ይወዱ ነበር፡፡ ከግራኝ ጦርነት ጥቂት ቀደም ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው የደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ መነኮስ አባ በኃይለ ማርያም በኢየሩሳሌም አደባባይ ባደረገው ክርክር ወቅት ከ30 በላይ መጻሕፍትን መጥቀሱን ስናይ ይህንን አባባል ያስረግጠዋል፡፡ በጎንደር ዘመን የነበሩት መምህር ኤስድሮስም በጣና ገዳማት ገብተው እስከ 3000 የሚደርሱ መጻሕፍን መመልከታቸውን የጉባኤ ቤት ትውፊት ይነግረናል[1]፡፡ 

የቀድሞ ጸሐፍትን የዕውቀት ልክ ሊነግሩን ከሚችሉ መረጃዎች መካከል የአባ ባሕርይ ‹መዝሙረ ክርስቶስ› የተሰኘው ድርሰት አንዱ ነው፡፡ ባሕርይ በዐፄ ርጸ ድንግልና ከዚያም ጥቂት ቀደም ብለው የነበሩ ሊቅ ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1528 ዓ..ነው፡፡ መጀመሪያ የነበሩት ጋሞ ውስጥ በአንድ ቤተ ክርስቲን አለቃ ሆነው ነው(የብርብር ማርያም አለቃ ነበሩ የሚሉ አሉ)፡፡[2]በኋላ ግን ኦሮሞዎች በአካባቢው እያየሉ ሲመጡ ወደ ጎንደር መጥተዋል፡፡ አባ ባሕርይ መዝሙረ ክርስቶስየተሰኘውን በግጥም የቀረበ ድርሰት ያዘጋጁትለመዝሙረ ዳዊት መመዘኛ(መለኪያ እንዲሆን) በመዝሙረ ዳዊቱ ልክ ነው፡፡ ዓላማቸውም መዝሙረ ዳዊትን የሚገለብጥ ሰው የመዝሙረ ዳዊቱን ልክ በእርሳቸው መዝሙረ ክርስቶስ በመለካት ሳያጓደል እንዲገለብጥ ለማድረግ ነው፡፡ ያዘጋጁት በ46 ዓመታቸው በ1574 ዓ..መሆኑ በዚያው በመጽሐፉ ላይ ተገልጧል[3]፡፡ 

አባ ባሕርይ ይህንን መጽሐፍ ሲያዘጋጁ ምንጭ የሆኗቸውን መጻሕፍት አስቀድመው በመቅድሙ ላይ አስፍረዋል፡፡ ማስፈር ብቻም ሳይሆን ከያንዳንዱ መጽሐፍ ምን ያህል ጥቅሶችን እንደወሰዱም ይገልጣሉ፡፡
1.      ከኦሪት ዘልደት - 17
2.     ከኦሪት ዘጸአት - 17
3.     ከኦሪት ዘሌዋውያን  - 7
4.     ከኦሪት ዘኊልቈ - 2
5.     ከኦሪት ዘዳግም - 11
6.     ከመጽሐፈ መሳፍንት - 2
7.     ከመጽሐፈ ኦሪት ዘሆሴዕ - 1
8.     ከመጽሐፈ ኩፋሌ - 2
9.     ከመጽሐፈ ሄኖክ - 7
10.   ከመጽሐፈ ኢዮብ - 1
11.     ከመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ - 7
12.    ከመጽሐፈ ነገሥት ዳግማዊ - 2
13.    ከመጽሐፈ ነገሥት ሣልስ - 9
14.   ከመጽሐፈ ነገሥት ራብዕ - 2
15.    ከመዝሙረ ዳዊትና ከሰሎሞን ምሳሌያት- 8
16.   ከመጽሐፈ ተግሣጽ- 3
17.    ከመጽሐፈ ጥበብ - 17
18.   ከመጽሐፈ መክብብ - 8
19.   መኃልየ መኃልይ - 2
20.  ከመጽሐፈ ሲራክ - 10
21.    ከትንቢተ ኢሳይያስ - 18
22.   ከትንቢተ ኤርምያስ - 7
23.   ከትንቢተ ሕዝቅኤል - 5
24.  ከትንቢተ ዳንኤል - 13
25.   ከመጽሐፈ እዝራ - 4
26.  ከመጽሐፈ መቃብያን - 2
27.   ከራእየ ኤልያስ - 1
28.  ከትንቢተ ሆሴዕ - 3
29.  ከትንቢተ አሞጽ - 2
30.  ከትንቢተ ሚክያስ - 3
31.    ከትንቢተ ኢዩኤል - 1
32.   ከትንቢተ ዮናስ- 1
33.   ከትንቢተ ዕንባቆም - 2
34.  ከትንቢተ ዘካርያስ - 4
35.   ማቴዎስ፣
36.   ማርቆስ፣
37.    ሉቃስ፣
38.   ዮሐንስ (ከአራቱ ወንጌላውያን በድምሩ) - 103
39.  ከመቅድመ ጳውሎስ - 1
40.  ከሮሜ መልእክት - 27
41.   ከቀዳማዊ ቆሮንቶስ - 10
42.  ከዳግማዊ ቆሮንቶስ መልእክት - 7
43.  ከገላትያ መልእክት - 7
44.  ከኤፌሶን መልእክት - 10
45.  ከፊልጵስዩስ መልእክት - 2
46.  ከቆላስይስ መልእክት - 7
47.  ከቀዳማዊ ተሰሎንቄ መልእክት -  2
48.  ከዕብራውያን መልእክት - 15
49.  ከያዕቆብ መልእክት - 7
50.  ከአንደኛው የጴጥሮስ መልእክት - 7
51.    ከሁለተኛው የጴጥሮስ መልእክት - 4
52.   ከቀዳማዊ የዮሐንስ መልእክት
53.   ከዳግማዊ ዮሐንስ መልእክት
54.  ከሣልሳዊ ዮሐንስ መልእክት (በድምሩ ከሦስቱ መልእክቶች)  - 5
55.   ከሐዋርያት ሥራ - 7
56.  ከዮሐንስ ራእይ - 9
57.   ከመጽሐፈ ሲኖዶስ - 2
58.  ከዲድስቅልያ - 8
59.  ከመጽሐፈ ኪዳን- 15
60.  ከመጽሐፈ ቀሌምንጦስ - 1
61.   ከባስልዮስ - 12
62.  ከአትናቴዎስ ሐዋርያዊ - 9
63.  ከሃይማኖተ አበው - 3
64.  ከዮሐንስ አፈወርቅ - 7
65.  ከመጽሐፈ ሠለስቱ ምእት ርቱዐነ ሃይማኖት- 7
66.  ታሪክ - 7
67.  ፍትሐ ነገሥት - 1
68.  ጎርጎርዮስ - 2
69.  ኤጲፋንዮስ - 2
70.  ያዕቆብ ዘእልበረዲ - 2
71.    መጽሐፈ ባሕርይ - 2
72.   ረድእ ወመምህር - 1
73.   ስንክሳር - 7
74.  ኤፍሬም ሶርያዊ - 11
75.   ያዕቆብ ዘሥሩግ - 1
76.  ድርሳነ አባ ብንያሚ - 3
77.   ድርሳነ አባ ሕርያቆስ - 3
78.  ሳዊሮስ ዘእስሙናይ - 11
79.  አረጋዊ መንፈሳዊ - 2
80.  ፊልክስዮስ - 2
81.   ተአምረ ኢየሱስ - 4
82.  ዜና አይሁድ - 1
83.  ፈላስፋ - 7
84.  ከሊላ ወድምና - 3
85.  ፊሳልጎስ - 5
86.  በረላም - 3
87.  ዜና አበው - 5
88.  ተአምረ እግዝትነ - 1
89.  መጽሐፈ ምሥጢር - 1
90.  አክስማሮስ - 2 

መውሰዳቸውን ይነግሩናል፡፡ እነዚህን መጻሕፍትም በጠቀሱባቸው ቦታዎች ላይ ሲደርሱ በጎን ኅዳግ ላይ ምንጮቹን አሥፍረዋቸዋል፡፡   

አባ ባሕርይ ለማስረጃነት የጠቀሷቸውን መጻሕፍት ብዛትና ዓይነት በአራት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
1.      ከብሉይና ሐዲስ
2.     ከሊቃውንት መጻሕፍት
3.     ከጠቢባን መጻሕፍትና
4.     ከታሪክ መጻሕፍት ናቸው፡፡ 

አባ ባሕርይ በመቅድማቸው ላይ ‹ለዚህ ድርሳነ መዝሙር የሚሆኑ ምስክሮችን ከመጻሕፍተ ኦሪት፣ ከወንጌላውያን፣ ከነቢያት ትንቢት፣ ከሐዋርያት መልእክታት፣ ከሊቃውንት ድርሳናት፣ ከጥንት ጠቢባን ምሳሌዎች ወስጃለሁ፡፡ በቃላቸው ጣዕም የኔ ንግግር ጣዕም እንዲያገኝ ብዬ፡፡ የያንዳንዳቸው ኅብር እንደ ዕንቁዎች ጌጥ እንዲሆን፡፡ የአንድ ኮከብ ብርሃን የሰማይን ሰፊ ሰሌዳ አያስጌጠውም፡፡ የአንድ ዕንቁ ውበትም ብቻውን አንድን ቤት አያሳምረውም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የአንድን ሰው መጽሐፍ ብቻ ማንበብ መጽሐፍን አያሳምረውም፡፡ ነገርም በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ካልሆነ በቀር ጸንቶ አይቆምም[4]› ይላሉ፡፡ በዚህ አባባላቸውም አንድ መጽሐፍ ለማዘጋጀት አያሌ መጻፍትን ማገላበጥና ምስክር ማበጀት አስፈላጊ መሆኑን አጽንተው ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት የደረሷቸው እንዲህ በላዕያነ መጻሕፍት የሆኑ ደባትር ናቸው፡፡ 




[1]በዚህ ረገድ እኔ ያየኋቸው ሊቅ አቡነ ዘካርያስ ናቸው፡፡ ከ5 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ቺካጎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተደርጎ በነበረ ጉባኤ ላይ አቡነ ዘካርያስ ባስተማሩት የ30 ደቂቃ ትምህርት ውስጥ ብሉይና ሐዲሱ ሳይቆጠር ከሊቃውንትና ከጠቢባን ብቻ 30 መጻሕፍትን መጥቀሳቸውን በአድናቆት ተመልክተን ነበር፡፡ መጽሐፈ በርለዓምን በአደባባይ ሲጠቅሱት ያየሁት አቡነ ዘካርያስንና መምህር ደጉ ዓለም ካሣን ነው፡፡
[2]ምናልባብርብር ማርያም( ጌታቸው ኃይሌ፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፣1995፣ 35)
[3]የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፣ 46
[4]EMML 3473 (መዝሙረ ክርስቶስ), 3a

ቆሻሻ መጣል ክልክል ነው

$
0
0



የሰዎችን አስተሳሰብ ሊለውጡ የሚችሉ ንግግሮችን በማድረግ የሚታወቀው ዓምደኛው ዴቪድ ጄ. ፖላይ ‹የቆሻሻ መኪና ሕግ (The Law of the Garbage Truck)  የተሰኘ ተወዳጅና ተደናቂ መጽሐፍ አለው፡፡ ይህንን መጽሐፉን ለመጻፍ መነሻ የሆነው ኒውዮርክ ውስጥ አንድ ቀን በታክሲ ሲጓዝ ያጋጠመው አደጋ ነበር፡፡ እርሱ የሚሄድበትን ታክሲ ከጎኑ የመጣ ሌላ መኪና ሊገጨው ለጥቂት ተረፈ፡፡ ስሕተቱ ከጎን የነበረው መኪና ሾፌር ነበር፡፡ ነገር ግን አደጋ አድራሹ ሾፌር በስሕተቱ ከመፀፀት ይልቅ መስኮቱን ከፍቶ የታክሲውን ሾፌር መሳደብና ማበሻቀጥ ጀመረ፡፡ የታክሲው ሾፌር ግን ፈገግ ብሎ እጁን ለሰላምታ በማውለብለብና ‹መልካም ቀን ይሁንልህ› በሚል የምኞት ቃል አለፈው፡፡
ጄ. ፖላይ ነገሩ ስላስገረመው የታክሲው ሾፌር ጠየቀው፡፡ ‹ጥፋተኛው ያኛው ሾፌር ነው፡፡ ይባስ ብሎም መስኮቱን ከፍቶ ሲሰድብህ ነበር፡፡ አንተ ግን መልካም እንደተደረገልህ ሁሉ ፈገግ አልክለት፤ እንዲያውም እጅህን አውጥተህ ሰላምታ ሰጠኸው፡፡ መልካም ምኞትህንም ገለጥክለት፡፡ ግን ለምን?› ሲል ጠየቀው፡፡ የታክሲውም ሾፌር አሁንም ፈገግ ብሎ ‹ብዙ ሰዎች የቆሻሻ መኪኖች ናቸው፡፡ ቆሻሻውን ተሸክመውም የሚያራግፉበት ቦታ ይፈልጋሉ፡፡ የያዙት ቆሻሻ ስድብ፣ ንዴት፣ ጭንቀት፣ ብልግና፣ ጭቅጭቅ፣ ንዝንዝ፣ ቁጣ፣ ርግማን፣ ተንኮልና ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ልክ የቆሻሻ መኪና ከየቤቱ ቆሻሻውን እስኪሞላ ድረስ እንደሚሰበስበው ሁሉ እነዚህም ከቤታቸው፣ ከትዳር አጋራቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሥራ ቦታቸው፣ ከንግድ ድርጅታቸው፣ ከብሶታቸው፣ ከኪሣራቸው፣ ከደረሰባቸው ችግርና ካጋጠማቸው ፈተና ቆሻሻቸውን ይሰበስቡታል፡፡
አንተ ግን የቆሻሻ መጣያቸው አትሁን፡፡ የቆሻሻ መኪናው ሲሞላ የመጣያ ቦታ ይፈልጋል፡፡ ከዚያ ደግሞ ተመልሶ እንደገና ሌላ ቆሻሻ ይሰበስባል፡፡ እነዚህም ከየቦታው ቆሻሻ ጠባያቸውን ይሰበስቡና አንተ ላይ ሊያራግፉብህ ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ ዝም ብለህ አትቀበላቸው፡፡ የቆሻሻ መኪና ከየቦታው የሰበሰበውን ቆሻሻ ሲያነሣ ቆሻሻ የነበረበትን ቦታ ያቃልለዋል፡፡ ነገር ግን ወስዶ ሌላ ቦታ በማከማቸት የተከማቸበትን ቦታ ያቆሽሸዋል፣ ያሸተዋል፣ ያበላሸዋል፡፡ እነዚህም እንዲሁ ናቸው፡፡ ከየቦታው የሰበሰቡትን ቆሻሻ ጠባይ አንተ ላይ ያራግፉና አንተን ሲያናድዱህ፣ ሲያበሽቁህ፣ ሲያስፀፅቱህ ይውላሉ፡፡ ቀንህን ያበላሹብሃል፡፡ ያደረጉህ ነገር፣ የሠሩህ ሥራና፣ የወረወሩብህ ስድብ አአምሮህ ውስጥ እየተብላላ ቀኑን ሙሉ ጠባይህን አበላሽቶት ይውላል፡፡ 

ለምን ትፈቅድላቸዋለህ? ፈገግ ብለህ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥረህ፣ ነገሩን አሳልፈህ፣ ለክፋታቸው በጎነት፣ ለስድባቸው መልካም ምኞት፣ ለርግማናቸው ምርቃት፣ ለቁጣቸው ፈገግታ፣ ለትዕቢታቸው ትኅትና መልስላቸውና ቆሻሻቸውን ይዘው እንዲመለሱ አድርጋቸው፡፡ በጭራሽ አንተ ላይ ማራገፍ የለባቸውም፡፡ ለዚህ ነው እኔም በፈገግታ፣ በሰላምታና በመልካም ምኞት የሸኘሁት፡፡ ከቻልኩ በርሱ ላይ ያለውን ቆሻሻ አቀልለታለሁ፡፡ ስላልሰደብኩት፣ ስላላንጓጠጥኩትና ስላልተጨቃጨቅኩት ቀኑን ሙሉ ፈገግታዬን፣ ሰላምታዬንና መልካም ምኞቴን በማሰብ ሲደሰት ይውላል፡፡ ካልተቻለ ደግሞ እኔ ላይ ቆሻሻውን ከማራገፍ ስለተከላከልኩት አትራፊው እኔ ነኝ› ሲል አብራራለት፡፡
ይህንን የሰማው ጄ. ፖላይ ነገሩን ሲያምሰለስለው ከርሞ ‹የቆሻሻ መኪና ሕግ› የተሰኘውን ተወዳጅ መጽሐፉን አዘጋጀ፡፡ ፖላይ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ‹የቆሻሻ መኪና በአንተ ላይ ቆሻሻውን እንዳያራግፍ ከፈለግክ እነዚህን ሕጎች ተግብራቸው› ይላል፡፡ የመጀመሪያው ሕግ ባለጌ፣ ሐሳብ አልባና ቁጡ የሆኑ ሰዎች በአንተ ላይ ቆሻሻቸውን እንዳይጥሉ ምንጊዜም ተከላከል› የሚል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሲያግጥሙህ ከቻልክ ጆሮህን ካልቻልክም ልብህን አትስጣቸው፡፡ ‹ወፎች በጭንቅላታችን ላይ እንዳይበሩ ማድረግ አንችልም፡፡ በጭንቅላታችን ላይ ጎጆ እንዳይሠሩ ማድረግ ግን እንችላለን› የሚል አባባል አለ፡፡ ሰዎች እንዳይሳደቡ፣ እንዳይቆጡ፣ ነገር እንዳያመነጩና እንዳይነታረኩ ማድረግ አንችልም፡፡ ጭንቅላታቸው እነርሱ ላይ ስሆነ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ አንደበት የሚወጣው ክፉ ቃል በጆሯችን በኩል ወደ ልባችን ገብቶ ጎጆ እንዳይሠራ ማድረግ  ይቻላል፡፡ ስናስበው፣ ስናወጣ ስናወርደው፣ ከንፈራችን ስንነክስለት፣ ጠረጲዛ በቡጢ ስንመታና ምነው እንዲህ ባልኩት ኖሮ፣ እንዲህም ባደረግኩት ኖሮ ስንል እንዳንውል ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዴት? ፊት ባለመስጠት፣ ጆሮና ዓይን በመንሣት፣ የልብን በር በመዝጋት፣ ከቁብ ባለመቁጠር፣ ለመርሳት በመሞከር፣ በጭንቅላታችን ላይ እንደሚበሩት ወፎች በመቁጠር፡፡ በመናቅና በማቃለል፡፡ 
ሁለተኛው ሕግ ደግሞ ‹ያለፉ ክፉ ነገሮችን ማስታወስና ቀጣዩን የሕይወት ጉዞህን መፍራት አቁም› ይላል፡፡ ያለፉ ክፉ ትውስታዎችን በአንዳች ነገር ዝጋቸው፡፡ በንስሐ፣ በይቅርታ፣ በካሣ፣ በዕርቅ፡፡ እርሳቸው፡፡ ካልቻልክ ደግሞ በሚጎዱህ መጠን ልክ አታስታውሳቸው፡፡ መርሳት የሚባለው ጸጋ የተሰጠን አንድም ክፉ ነገሮችን ለመርሳት እንድንችል ነው፡፡ ቆሻሻውን አጽዳ፡፡ ሰዎች በአንድ ወቅት ክፉ አድርገውብህ ይሆናል፡፡ እነዚያ ሰዎች በአንተ ላይ ቆሻሻውን አከማቹት ማለት ነው፡፡ አንተም ለዘመናት የቆሻሻቸው ማራገፊያ ሆነህ ይዘኸው እየተጓዝክ ነው፡፡ አራግፈው፡፡ ቆሻሻ ምንም ቢራገፍ በቆሻሻ መኪናው ላይ የሚተርፍ ቅሬት መኖሩ አይጠረጠርም፡፡ አንተም ባለፉት ዘመናት ሰዎች ላይ ቆሻሻ ስታራግፍ አንተ ላይ የቀሩ ትርፍራፊዎች አይጠፉም፡፡ ተሸክመኻቸው አትዙር፤ አራግፋቸው፡፡ ያለፉ ቆሻሻዎችን አለማጽዳት ነገን እንደንፈራው ያደርገናል፡፡ ያለፉ ቆሻሻዎችን በሚገባ ካጸዳናቸው ነጻነት፣ ንጽሕናና ብሩኀ ተስፋን እናገኛለን፡፡ ብዙ ሰዎች የትናንት እሥረኞች ናቸው፡፡ እርሾው መልካም ካልሆነ ሊጡ፣ ብሎም እንጀራው እንደሚበላሸው ሁሉ ትናንትህ ካልጸዳ ነገህ ይበላሻል፡፡
ሦስተኛው ሕግ ደግሞ ›ልትቆጣጠረው በምትችለው ነገር ላይ አተኩር እንጂ ልትቆጣጠራቸው በማትችል ክፉ ነገሮች ላይ ጊዜ አታጥፋ› የሚል ነው፡፡ ሰዎች በሚናገሩት፣ በሚያደርጉት፣ በሚሠነዝሩትና በሚፈጥሩት ነገር ላይ ልብህ አይቁም፡፡  በታክሲ ውስጥ ስትሄድ አንድ ጋጠ ወጥ ሰው ቢገጥምህና የማይሆን ቃል ቢናገርህ ለእርሱ ቦታ አትስጠው፡፡ አንዱ ፌርማታ ላይ ይወርዳል፡፡ ከዚያ በኋላ አታገኘውም፡፡ አንተን ግን ቀኑን ሙሉ ሲበጠብጥህ ይውላል፡፡ ‹ቁንጫ የጠረጉት ለት ባለጌ የመከሩት ለት ይብሰዋል› እንዲሉ ምክር ለሁሉ አይሰጥም፣ መልስ ለሁሉ አይመለስም፤ ክርክር ከሁሉም ጋር አይደረግም፡፡ ዕንቁዎችህን የምትሰጣቸውን ሰዎች ለይ፡፡ ዕንቁላሎችህን የምታስታቅፋቸውን ዶሮዎች ምረጥ፡፡ የዚያን ሰው ተግባር፣ ንግግር፣ ጠባይ፣ ባህልና ልምድ ልትቆጣጠረው አትችልም፡፡ ልጅህ ነው? ጓደኛህ ነው? የትዳር አጋርሽ ነው? የሥራ ባልደረባህ ነው? ጎረቤትህ ነው? በጉዳዩ ላይ ብትበረታበት ለውጥ ለማምጣት ትችላለህ? ከሆነ መልካም፡፡ ካልቻልክ ግን ለምን ዕንቁዎችህን በእሪያዎች ፊት ትጥላለህ? ‹እገሌ እንዲህ ይልሃል›፣ ‹እዚህ ቦታ ስላንተ እንዲህ ሲወራ ሰማሁ› የሚሉትን አትስማ፡፡ አትቆጣጠራቸውም፡፡ ራስህን ተቆጣጠር፣ ራስህን ግራና የራስህን መንገድ ቀይስ፡፡
አራተኛው ሕግ ‹ባገኘህበት ቦታ ሁሉ ጋጠ ወጥነትን ቀንስ፣ ሥልጣኔን ጨምር፣ ጉልቤዎችን ከነ ቆሻሻ መኪናቸው አስቁማቸው› ይላል፡፡ ሰዎች በአንተ ላይ ጋጠወጦችና ያልሠለጠኑ እንዲሆኑ አትፍቀድላቸው፡፡ መርሕህን፣ ጠባይህንና መሥመርህን ግልጽ አድርግላቸው፡፡ ጋጠወጥነትንና አለመሠልጠንን በቸልታና በዝምታ ከተቀበልካቸው እንደልባቸው ይፈነጩብሃል፡፡ ከመጀመሪያው እንዲህ ላሉ ሰዎች ቦታ አይኑርህ፤ ካጋጠሙህም ሐሳብህን ግለጥላቸው፡፡ ካልተመቸሃቸው ወይም ካልተመቹህ ግንኙነትህን አቋርጥ፡፡ ‹ለባለጌ ከሳቁለት፣ ለውሻ ከሮጡለት› አደጋው ከባድ ነው፡፡ ሥልጣን ወይም ጉልበት ስላላቸው ብቻ በአንተ ላይ ቆሻሻ ለመድፋት እንደሚችሉ የሚያስቡ ባለ ሥልጣናት፣ አለቆች፣ ጉልበተኞችና ደፋሮች ይኖራሉ፡፡ ከቻልክ በሕግ ካልቻልክ ግን በርህን በመዝጋት መኪናውን አስቁመው፡፡ የሚፈልጉትን አታድርግላቸው፣ በመንገዳቸው አትሂድ፣ በዕቅዳቸው አትመራ፣ ጠባያቸውን አትጋራ፣ እንዳመጣጣቸው አትመልስ፡፡ ምንጊዜም አንተ ራስህን ብቻ ሁን፡፡ የወረወሩትን አታስበው፣ የጠየቁህንም ሁሉ አትመልስ፡፡ ችግሩን የመፍቻ ሌላ መንገድ አስብ፡፡ የሠለጠነ፣ ሕጋዊ የሆነና፣ ችግሩን የሚፈታ መንገድ ፈልግ፡፡ ጋጠወጥነትን በጋጠወጥነት፣ ስድብን በስድብ፣ ነገርን በነገር፣ ክፋትንም በክፋት አትመልስ፡፡ ያ ከሆነ በመንገዳቸው እየተጓዝክ፣ የቆሻሻቸውም ማራገፊያ እየሆንክ ነው፡፡ ሁለታችሁም ጋ አንድ ዓይነት ሽታ ካለ፣ ሁለታችሁም ጋ አንድ ዓይነት ቆሻሻ አለ ማለት ነው፡፡
አምስተኛው ሕግ ደግሞ ‹በቤተሰቦችህ፣ በልጆችህ፣ በጓደኞችህና በሥራ ባልደረቦችህ ላይ ቆሻሻ ባለመድፋት ጠባይህን እየገራኸው ሂድ› ይላል፡፡ ከቻልክ ከአንተ ቆሻሻ እንዳይወጣ አድርግ፡፡ ካልቻልክስ? ቆሻሻው ማንንም ሳይጎዳ የሚወገድበትን መንገድ ፈልግ፡፡ በተናደደክ ጊዜ ከሰዎች ጋር መከራከርን ተው፡፡ ተደስተህም ሆነ ተናደህ ውሳኔ አትወስን፡፡ ከስሜትህ ሳትበርድ ሰዎችን አታናግር፡፡ ከሰዎች ጋር ለመነጋገሪያ መልካሙ ጊዜ ስሜት በርዶ አእምሮ ቦታውን ሲይዝ ነው፡፡ የተናደድክበትን ሰው ወዲያው አታግኘው፡፡ ውለህ አድረህ፣ ነገሩን አውጥተህና አውርደህ፣ ከተለያየ አቅጣጫም ነገሩን መዝነህ ከዚያ በኋላ አናግረው፡፡ ስድብ ሰውን አይለውጥም፤ ቁጣም አእምሮን አይቀይርም፤ ጭቅጭቅ እንደሚያንጠባጥብ የቤት ጣሪያ ይሆናል፤ ሐሜትም ዞሮ ለራስ ነው፡፡ ለውጥ ማምጣት፣ ችግር መፍታትና ሰዎችን ማረም ከፈለግክ ሌሎች መንገዶችን ሞክር፡፡
‹ከመርገም ውስጥ በረከትን ፈልግ› ይላል ስድስተኛው ሕግ፡፡ ከኪሣራህ፣ ከሕመምህ፣ ከጉዳትህና ከችግርህ ውስጥ ደስታን ለማብቀል ሞክር፡፡ አካልህን ሲያሥሩህ፣ ኅሊናህን ነጻ አድርግ፤ ሰውነትህን ሲያምህ፣ አእምሮህን ጤነኛ አድርገው፤ ገንዘብህን ስትከስር ጤናህንና ሥነ ልቡናህን ሀብታም አትርፍ፤ ወዳጆችህን ስታጣ፣ ትዝታቸውን አስቀር፤ አካልህ ሲጎዳ መንፈስህን ሙሉ አድርግ፤ ያጣህውን ትተህ ያለህን ቁጠር፡፡ ማንም ጥርስህን እንጂ ፈገግታህን ማርገፍ አይችልም፡፡ ማንም ዋንጫህን እንጂ አሸናፊነትህን ሊወስድብህ አይችልም፡፡
‹የቆሻሻ መኪና የማይደርስበት ክልል መሥርት› የሚለው ደግሞ ሰባተኛው ሕግ ነው፡፡ በቤተሰብህ፣ በጓደኞችህ፣ በዘመዶችህ፣ በሥራ አካባቢህና በመንደርህ ይህንን ክልል መሥርት፡፡ ሌሎችን በማሳመን፣ በማስረዳት፣ ሐሳብህን በመግለጥና ነገሩ እንዲገባቸው በማድረግ ‹የቆሻሻ መኪና በዚህ ማለፍ ክልክል ነው› የሚል መርሕ እንዲኖራቸው ማድረግ ትችላለህ፡፡ የምትውልበት፣ የምትሠራበትና የምትኖርበት አካባቢ ከቆሻሻ መኪኖች ነጻ ከሆነ ማንም ወደ አንተ ቆሻሻ ለመድፋት አይመጣም፡፡ በቢሮህ ግድግዳ ላይ ‹ቆሻሻ መድፋት ክልክል ነው› የሚል ለጥፍ፡፡ ሰዎች ይገርማቸውና ይጠይቁሃል፡፡ ‹እዚህ ቢሮ የቆሻሻ መኪና ምን ሊያድርግ ይመጣል? የጽዳት ሠራተኞችስ እንዴት እዚህ ቦታ ቆሻሻ ይደፋሉ? › ይሉሃል፡፡ ንገራቸው፡፡ ቆሻሻው ምን እንደሆነና የቆሻሻ መኪኖች እነማን እንደሆኑ፡፡ ይቀየሩ ይሆናል፡፡ ከጓደኞችህም ጋር ተነጋገሩና ተስማሙበት፡፡ ማንም ቆሻሻውን በራሱም ላይ ሆነ በሌሎች ላይ ላይጭን ተስማሙ፡፡
የመጨረሻው ሕግ ደግሞ ‹በየቀኑ ለመደስት ሞክር፣ የምትወደውን ለመሥራትና የምትሠራውን ለመውደድ ተጣጣር፣ ተግባርህም ሁሉ ለውጥ የሚያመጣ ይሁን› ይላል፡፡ በየቀኑ መደሰት ማለት በየቀኑ መጠጣት፣ አዲስ ልብስ መልበስ፣ ሲኒማ መመልከትና ቀልድ ሲቀልዱ መዋል አይደለም፡፡ አዲስ ነገር ለመሥራትና ትርጉም ያለው ውሎ ለመዋል ወስኖ መነሣት ነው፡፡ መሥሪያ ቤትህ ዕቅድ ይኖረው ይሆናል፡፡ አንተስ አለህ? ወደ ቢሮ የምትሄደው ያስቀመጥከውን ለመሥራት ነው ወይስ የተቀመጠልህን ለመሥራት? ስንት ፋይል ልታይ፣ ስንት ውሳኔ ልትወስን፣ ስንት ምርት ልታመርት፣ ስንት ችግር ልትፈታ፣ ስንት ትርፍ ልታመጣ፣ ስንት ሰው ልታክም፣ ለራስህ ምን አቅደሃል? አካባቢህን ጽዱ፣ ውብ፣ ሥራብኝ ሥራብኝ የሚል አድርገህዋል? ሥራ ቦታህ ላይ ከቀኑ ውስጥ ሩቡን ትውልበታልህ፤ ያ ማለት ከሕይወትህ ሩቡን ታሳልፍበታለህ፤ የሥራ ቦታህን ስታበላሸው ሩቡን ኑሮህን ታበላሸዋለህ፡፡ ያም ብቻ አይደለም፡፡ ሥራህን በወደድከው መጠን ጠዋት ወደ ሥራህ እንደ ጽጌሬዳ ይስብሃል፡፡ ማታም ወደቤትህም በደስታ ይሸኝሃል፡፡
ከቻልክ የምትወደውን ሥራ ሥራ፡፡ ካልቻልክ የምትሠራውን ሥራ ውደድ፡፡ ለመጥላት ምክንያት ከምትፈልግ ለመውደድ ምክንያት ፈልግ፡፡ የምትጠላውን ሥራ እየሠራህ ምንም በጎ ለውጥ ልታመጣ አትችልምና፡፡ ደንበኞችህ ቆሻሻ ተጭነው ይመጡ ይሆናል፡፡ አንተ ግን እንዲያራግፉብህ አትፍቀድላቸው፡፡ ንዴታቸውን አብርደህ፣ ቁጣቸውን አሳስቀህ፣ ችግራቸውን ፈትተህ፤ ያንንም ሁሉ ካልቻልክ ኀዘናቸውን ተካፍለህ መልሳቸው፡፡ ቢሮህን የቆሻሻ ማከማቻ አታድርገው፡፡ ስብሰባ የደስታ ምንጭ፣ የዕውቀት መገብያና፣ የችግር መካፈያ እንጂ የቆሻሻ መጣያ እንዳይሆን ሥራ፡፡ ደስታ ከለውጥ ይገኛል፡፡ የምትጋተረው ከችግሮች ጋር እንጂ ከሰዎች ጋር አይሁን፡፡ ለውጥ እያመጣህ በሄድክ ቁጥር ለራስህ ደስታን እየሸመትክ ትሄዳለህ፡፡
ይህንን ለማድረግ የቆረጡ ሰዎች ይህንን መፈክር ይዘዋል፡፡
ቁም! እዚህ ቦታ ቆሻሻ መጣል ክልክል ነው፡፡

ሕመም አንድም ለትምህርት አንድም ለሞት

$
0
0
ጥንታውያን የአብነት ሊቃውንት ‹ሕመም አንድም ለትምህርት አንድም ለሞት ነው› ይላሉ፡፡ መታመሙን ላወቀ፣ መድኃኒቱን ለፈለገ፣ መድኃኒቱንም በትክክል ለወሰደ፣ ወስዶም ለዳነ ሰው ሕመም ለትምህርት ይሆነዋል፡፡ ሦስት ነገር ይማርበታልና፡፡ አንድም ዳግመኛ እንዳይዘው ጥንቃቄን፣ አንድም ቢይዘው ሊትርፍ የሚችልበትን መፍትሔን፣ አንድም ደግሞ ለሌላው የሚመክረው ልምድን ያተርፋል፡፡ ያለበለዚያ ግን የሕመም መጨረሻው ሞት ነውና ላንዱ ትምህርት የሆነው በሽታ ሌላውን ይገድለዋል፡፡
አሁን ታመናል፡፡ ሕዝቡ የሚያነሣው ጥያቄ፣ መንግሥት የሚሰጠው ምላሽ፣ የሃይማኖት ‹አባቶች› የሚያወጡት መግለጫ፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ከግራ ከቀኝ የሚያናፍሰው ነገር፣ ደጋፊና ተቃዋሚው ከወዲህ ወዲያ የሚሠናዘረው ዱላ ሕመም ላይ መሆናችንን የሚገልጥ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን መታመሙን የሚያምን፣ መድኃኒቱን የሚፈልግና መድኃኒቱንም በተገቢው ሁኔታ የሚወስድ መንግሥትና ሕዝብ ነው፡፡
መጀመሪያ መተማመን የሚያስፈልገው ‹ችግር አለ ወይ?› የሚለው ላይ ነው፡፡ አዎን ችግር አለ፡፡ እየሆኑ ያሉት ነገሮች የሚነግሩን ችግር መኖሩን ነው፡፡ ችግሩ እነ እንትና ያነሣሡት፣ የቀሰቀሱት፣ ያደራጁት ምናምን ማለታችን ችግር መኖሩን አያስቀረውም፡፡ በሀገራችን ‹የጥያቄ ክፉ የለውም፤ የመልስ እንጂ›  ይባላል፡፡ የጥቂቶች ወይም የብዙዎች፣ የእነ አንቶኔ ወይም የነ እንትና መሆኑ ጥያቄውን አይለውጠውም፡፡ ለውጥ የሚያመጣው ለጥያቄው ተገቢውን መልስ መስጠቱ ነው፡፡ ‹በቅርቡ ያልመለሰ እረኛ በሩቁ ሲባዝን ይውላል› እንደሚባለው በየጊዜው ተገቢ መልስ ሳይሰጣቸው፣ ወይም ደግሞ ይዋሉ ይደሩ እየተባሉ፤ ያለበለዚያም የተፈቱ የመሰሉ ነገሮች እንደገና እያመረቀዙ መሆናቸው እየታየ ነው፡፡ 



በሽታው ምንድን ነው? ይኼ የምር የሆነ ውይይትና መግባባት የሚጠይቅ ነው፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም ለፕሮፓጋንዳ ወይም ለጊዜያዊ ድል ወይም የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ወይም ለዶክመንተሪ ፊልም ወይም ደግሞ ለቁጣ ማብረጃ ከሚሆን ወይይት፣ መግለጫና ንግግር ያለፈ ሁሉን ዐቀፍ፣ ለመፍትሔ ብቻ የቆመና በእውነት የሚደረግን ውይይት የሚጠይቅ፡፡ አንድ ዓይነት ሰዎች ተሰብስበው አንድ ዓይነት ንግግር የሚናገሩበት ሳይሆን ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን፣ ወገኖችን፣ አቋሞችንና የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚወክሉ ወገኖች ለአንዲት ሀገር ሲባል ሁሉን ዐቀፍ፣ ግን የምር የሆነ፣ ምናልባትም አንዳንዶቻችንን ሊመረን የሚችል መድኀኒት የሚፈልጉበት ውይይት ነው፡፡  በተለመደው መንገድ መጓዛችንን ትተን አዲስ መድኃኒት በአዲስ መንገድ እንፈልግ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ እየተጓዘ የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ሞኝ ብቻ ነውና፡፡
ከያቅጣጫው የሚሰጡ መግለጫዎች ሆድ ለባሰው ማጭድ የሚያውሱ፣ ከሚያረጋጉ ይልቅ የሚያናድዱ፣ ከሚያስታግሡ ይልቅ የሚያባብሱ፣ ከሚመክሩ ይልቅ የሚያነዝሩ ናቸው፡፡ ራሳቸው ችግር ናቸው እንጂ ችግር የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ሌላው ቀርቶ የሃይማኖት አባቶች እንኳን የሚናገሩት ነገር ሃይማኖት ሃይማኖት የሚል አይደለም፡፡
አሁን የሚታየው የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ነው፡፡ ማዶ ያሉትን አካላት የችግሩ መነሻና መድረሻ ማድረጉ መፍትሔ አያመጣም፡፡ እንዲያውም ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ እዚህ አብረውት ከሚኖሩት የመንግሥት አካላትይልቅ ማዶ ያሉትን ለምን ሰማ? እነዚያስ እዚህ ገብተው ሕዝብ እስኪቀሰቅሱ ድረስ እንዴት ዐቅም አገኙ? ሰው ውጭ ውጭ የሚያየው ቤቱ ምን ሲሆንበት ነው? መልሶ መላልሶ ችግሩ እዚሁ ነው የሚሆነው፡፡ የሚያዋጣው ወደገደለው መግባት ነው፡፡ ወደ ችግሩ፡፡
ቀጥሎ የሚነሣው ድግሞ ‹መድኃኒቱስ ምንድን ነው?› የሚለው ነው፡፡ ሁሉንም ወገኖች የሚወክለውና ለሀገሪቱ ሁነኛ መድኃኒት ለመፈለግ የሚደረገው የምር ውይይት ነው መድኃኒቱን ሊያመጣው የሚችለው፡፡ ከአንድ አቅጣጫ የሚመጣ መድኃኒት የሚያድንበት ጊዜ አብቅቷል፡፡ አሁን ሁሉን አግባብቶ ሁሉንም ሊያድን የሚችል መድኃኒት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በዚህ ሂደት የሚፈራም የሚናቅም መኖር የለበትም፡፡ የሚገለል የሚጣልም መኖር የለበትም፡፡ መድኃኒት አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልግ እንጂ የሚፈለግ ላይሆን ይችላል፡፡ የሚያድን እንጂ የሚወደድ ላይሆን ይችላል፡፡ መድኃኒት ፍለጋው ይህንን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሂደት ልናድናት ቆርጠን መነሣት ያለብን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ሥርዓቶች፣ ፖሊሲዎች፣ አደረጃጀቶች፣ አወቃቀሮች፣ ሊቀየሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ከጠላትነት ወደ ተነጋጋሪነት፣ ከአጥር ወደ ድልድይ፣ ከተጻራሪነት ወደ ተደጋጋፊነት መምጣት ያስፈልግ ይሆናል፡፡
በተበታተነ ሁኔታ በየአካባቢው የሚነዱትን እሳቶች ለማጥፋት ከመሯሯጥ ይልቅ ልብን ሰብሰብ አድርጎ የማያዳግም መፍትሔ መስጠቱ ነው የሚሻለው፡፡ በተለይም መንግሥት ይህ ይጠበቅበታል፡፡ እየሮጡ መስማት እየሮጡ መርሳትን ያመጣልና ቆም ብሎ ሰምቶ ቆም ብሎ መፍትሔ መስጠት ነው ብልሃቱ፡፡ 
ኮሶ ሲያሽር እየመረረ ነው፡፡ ወይ ሁላችን አናሸንፋለን፤ አለያም ሁላችንም እንሸነፋለን፡፡ ወይ ሁላችንም ለሕመሙ ትክክለኛውን መድኃኒት አግኝተን ተምረን እንድናለን፤ አለያም መድኃኒቱን አጥተን ሞተን እናርፋለን፡፡ ምርጫው ሁለት ነው፡፡ ሕመም አንድም ለትምህርት አንድም ለሞት ነውና፡፡
‹ሕመምተኛ ሲሻለው የዳነ ይመስለዋል፤ ሕመምተኛ ሲያቃዠው የሞተ ይመስለዋል› ይባላል፡፡ አንድ ነገር በትክክል መነሻው ሳይታወቅ፣ ችግሩም ሳይፈታ፣ በራሱ ጊዜ ጋብ አለ ማለት ሕመሙ ዳነ ማለት አይደለም፡፡ ብርድ እንዳገኘ የጉንፋን ቫይረስ ሁኔታው ሲመቻችለት እንደገና ይነሣል፡፡ ሕመምተኛው ሲሻለው የዳነ እየመሰለን ከምንተወው በሚገባ ሕመሙን መርምረን ተገቢውን መድኃኒት መስጠቱ የተሻለ ነው፡፡ ዛሬ የተነሡት ነገሮች ጋብ ቢሉ እንኳን ባንድ በኩል ጥለውት የሚያልፉት ጠባሳ፣ በሌላ በኩል በትክክል ባለመፈታታቸው ምክንያት በባሰ ሁኔታ ዳግም መነሣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እንደምናየው ከሆነ በሀገሪቱ የሚከሰቱ ለውጦች የሰውን አስተሳሰብ፣ አነዋወር፣ መስተጋብርና አሰላለፍ እየለወጡት ነው፡፡ ዛሬ እንደትናንቱ የሆነ የለም፡፡ ነገም እንደዛሬ የሚሆን አይገኝም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ‹በሽተኛ ሲያቃዠው የሞተ ይመስለዋል› እንደተባለው ሀገሪቱ ያለቀላት የሚመስላቸው ወገኖች የሀገሪቱን ታሪክ የማያውቁ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ የባሰ ችግርና መከራ፣ ከዚህ የባሰ ውጥንቅጥና ፈተና አሳልፋ የምትኖር ሀገር ናት፡፡ አሳልፋ የማታልፍ ሀገር ናት፡፡ በየዘመኑ ከሕመማቸው መማር ያልቻሉ መንግሥታትና ኃይላት አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን አሁንም አለች፡፡
ሕመሙን ከማባባስ፣ በሕመሙ ለማትረፍም ከመሮጥ፣ ሕመሙን በትክክል አክመን ከሕመሙ እኛው ተምረን እንውጣ፡፡ ካልሆነ ግን ሞተን ለሌሎች የታሪክ መማሪያ እንሆናለን፡፡      

የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ታወቁ

$
0
0



click her for pdf
ጋዜጣዊ መግለጫ
ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደውና ለሀገራቸውና ለወገናቸው ላቅ ያለ አገልግሎት የሰጡ ዜጎች የሚከብሩበት የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ በአቤል ሲኒማ አዳራሽ ይከናወናል፡፡ በዕለቱ የክብር እንግዶች፣ ተሸላሚዎች፣ ዕጩዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና መገናኛ ብዙኃን  በሚገኙበት ሥነ ሥርዓቱ ይከናወናል፡፡
የበጎ ሰው ሽልማት ኮሚቴ ያለፉትን ሦስት ዝግጅቶች ሂደት ሲያከናውን እንደኖረው ለዚህ ክብር መብቃት አለባቸው የተባሉ ዜጎች በሕዝቡ የተጠቆሙ ሲሆን፤ በየዘርፉ ከተጠቆሙት ዜጎች መካከልም ሥራዎቻቸው ተመዝነው ሦስት ሦስት ዕጩዎች ተለይተዋል፡፡ በእነዚህ እጩዎች ላይ አምስት አምስት ዳኞች (በየዘርፉ) ደምጽ እየሰጡ ነው፡፡ የየዘርፉ ተሸላሚዎችም ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓም በሚካኼደው ሥነ ሥርዓት ይከበራሉ፡፡
መገናኛ ብዙኃንና ሌሎች የመገናኛ አካላት እጩዎችን በማስተዋወቅና በማክበር ለሀገራቸው በጎ የሚሠሩ ዜጎችን ለማብዛት የበኩላቸውን እንዲወጡ እየጠየቅን ዕጩዎቹን በየዘርፋቸው እንደሚከተለው እንገልጣለን፡፡ 



1.    መምህርነት
·         ተ/ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው (በአዲስ አበባ ዩኚቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር)
·         ተ/ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የነበሩ)
·         መ/ር አውራሪስ ተገኝ (ምሥራቅ ጎጃም፣ ቢቡኝ ወረዳ የሚገኙ፤ በዘውዴ ልየው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር)
2.   ንግድና ሥራ ፈጠራ
·         አቶ ብዙአየሁ ታደለ (የኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ ባለቤት)
·         አቶ ሳሙኤል ታፈሰ (የሰንሻይን ሪል እስቴት ባለቤት)
·         አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ (የኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ መሥራች)
3.   ማኅበራዊ ጥናት
·         ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (የግእዝ መዛግብትን በማጥናት የታወቁ ሊቅ)
·         ዶክተር አንዳርጋቸው ጥሩነህ (በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የታሪክ ምሁር)
·         ፕሮፌሰር ባየ ይማም (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን ሊቅ)
4.   ሳይንስ
·         ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ (በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ላይ የሠሩ ሳይንቲስት)
·         ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ (በኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳር  ላይ የሠሩ ሊቅ)
·         ዶክተር ወንዱ ዓለማየሁ (የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ እንዲቋቋም ታላቁን ሥራ ሠሩና፣ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ቤ ት ለቤት በመጓዝ የብዙዎችን ዓይን ያበሩ ሳይንቲስት)
5.   ቅርስና ባ ህል
·         የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም(አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)
·         ኢንጅነር ታደለ ብጡል (የአኩስምን ሐውልት በማስመለስ፣ የኢትዮጵያን ቅርሶች በማስተዋወቅና የታላላቅ ሰዎችን ታሪክ በመመዝገብ የታወቁ ምሁር)
·         መ/ር ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር (የኢትዮጵያን ቃላዊ ቅርሶች የሚሰበስቡ ሊቅ)
6.   መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት
·         ኢንጅነር ዘውዴ ተክሉ (የአዲስ አበባን ከተማ ካስተዳደሩትና ለውጥ ካመጡት ከንቲባዎች አንዱ)
·         ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር (የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ለብዙ ዓመታት የመሩ የአካባቢ ሳይንስ ሊቅ)
·         ዳኛ ስንታየሁ ዘለቀ (በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የኮንስትራክሽን ችሎት የሚያገለግሉ ዳኛ)
7.   ስፖርት
·         አቶ ጌቱ በቀለ (በሰበታ አካባቢ ስፖርትን ለማሳደግ የሠሩ ሰው)
·         ጋቶች ፓኖ (ከጋምቤላ ክልል ለብሔራዊ ቡድን የተመረጠ የቡና ክለብ የእግር ኳስ ተጨዋች)
·         ዶክተር ይልማ በርታ (የአትሌቲክስ ስፖርት አሠልጣኝ)
8.   ኪነ ጥበብ (ድርሰት)
·         አቶ አስፋው ዳምጤ (የሥነ ጽሑፍ ሰው፣ ሐያሲና ደራሲ)
·         ወ/ሮ ፀሐይ መላኩ (ሴት የረዥም ልቦለድ ደራሲ)
·         አቶ አውግቸው ተረፈ (የአጫጭር ልቦለዶች ደራሲና ተርጓሚ)
9.   ሚዲያና ጋዜጠኛነት
·          መንሱር አብዱል ቀኒ (የስፖርት ጋዜጠኛ)
·         አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ (በኢትዮጵያ የኅትመት ሚዲያ ላይ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ አንጋፋ ጋዜጠኛ)
·         አቶ ደረጀ ኃይሌ (በቃለ መጠይቅ ጥበቡ የሚታወቅ ጋዜጠኛ)
10.  በጎ አድራጎት
·         ዶክተር ቦጋለች ገብሬ (የከምባቲ መንቲ ገዚማ-ቶፔ ‹የከምባታ ሴቶች አንድ ላይ ተነሥተዋል› የተሰኘው ድርጅት መሥራችና በከማባታ ሴቶች ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጡ ሴት)
·         ወ/ሮ ፀሐይ ሮቺሊ (የሰላም ሕጻናት ማሳደጊያ መንደር መሥራች)
·         ወ/ሮ ዘውዲቱ መሸሻ (ሕይወት የሕጻናትና ቤተሰብ መርጃ ድርጅት መሥራች)

ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ

$
0
0


ሀገር ሰላም እንድትሆን፤ ሰላም ሆናም በብልጽግና ጎዳና እንድትራመድ ከታሰበ ሁለት ነገሮች የግድ ያስፈልጓታል፡፡ ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥትና መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ፡፡ ማዳመጥ ከመስማት ይለያል፡፡ መስማት ጆሮ ለተፈጠረለት ሁሉ የሚቻል ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ስናነብ እንኳን ስንትና ስንት ድምጾችን ፈልገንም ሳንፈልግም እንሰማለን፡፡ ማዳመጥ ግን ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ ይሁነኝ ብሎ መስማት፣ ሰምቶ ማስተዋል፣ አስተውሎም መመለስ፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ስንልም ይሁነኝ ብሎ ሕዝቡን የሚሰማ፣ ሰምቶ ሕዝቡ ምን እንዳለው የሚያስተውልና ከዚያም አስተውሎ መልስ የሚሰጥ መንግሥት ማለት ነው፡፡ ለሕዝብ የመናገር ነጻነት ብቻውን ምንም አያደርግለትም፡፡ የመደመጥ መብት ከሌለው በቀር፡፡ ሰሚ ከሌለ እንኳን ሕዝብ ፈጣሪ አይናገርም፡፡ ቢናገርም ጥቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን መላእክት እስኪፈጠሩ ድረስ ፈጣሪ ፍጥረታትን በአርምሞ ብቻ የፈጠረው፡፡ ለምን? ቢሉ ሰሚ ሳይኖር መናገር ምን ያደርጋል ብሎ፡፡ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ግን ‹ብርሃን ይሁን› ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን፡፡ አሁን ሰሚ ተገኝቷልና መናገር ዋጋ አለው፡፡
ሕዝብም መናገሩ ብቻ ጥቅም የለውም፡፡ የተናገረውን የሚያዳምጠው መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው ሲያጣ ጩኸቱን የሚያዳምጠው አጥቶ ቤቱ እንደተዘረፈበት ውሻ ‹ነባህነ ነባህነ ከመ ዘኢነባህነ ኮነ - ጩኸን ጩኸን እንዳልጮኽን ሆን› ብሎ አይቀመጥም፡፡ ራሱን በራሱ ማዳመጥ ይጀምራል፡፡

የልቤን መከፋት ሆዴ እያዳመጠ
ሊመረው ነው መሰል ነገር አላመጠ
የሚል የቆለኛ ፉከራ አለ፡፡ 

 ሰውዬው በልቡ መከፋቱን ለሰው ቢናገር ቢናገር የሚሰማው አጣ፡፡ እርሱ ሰሚ ሲያጣ ሆዱ ግን የልቡን መከፋት እየሰማ ይቃጠል ጀመር፡፡ በኋላም ሆዱ እየቆረጠ ሲሄድ ጊዜ ነው ይህንን የፎከረው፡፡ ሕዝብ ራሱን ማዳመጥ ሲጀምር ‹ሊመረው ነው መሰል› የሚለው ፉከራ ላይ እየደረሰ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሚሆነውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕዝብን በርእዮተ ዓለም፣ በሐሳብና በአመለካከት አንድ ለማድረግ እጅግ ጽኑ ትግል፣ እጅግ ብርቱ ጥረት፣ እጅግ ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ሕዝብን በቀላሉ የሚያስተባብረው አንድ ነገር ነው፡፡ መጠቃት ወይም መገፋት፡፡ ያን ጊዜ ወዲያ ማዶ ሆኖ አንዱ የተጣራውን ወዲህ ማዶ ሆኖ ሌላው ይሰማዋል፡፡
እዚያ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ተጣራ
እዚህ ማዶ ሆኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ ተነቃቃ ይህ ነገር ለኛ ነው
ማለት የሚችለው የሚዳምጥ መንግሥት ካለ ብቻ ነው፡፡
መንግሥት ሕዝብን ይሁነኝ ብሎ ነው ማዳመጥ አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕዝብ የተናገረው ላይደርሰው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕዝብ ያልተናገረውን ሊሰማ ይችላል፡፡ ሕዝብ የተናገረው ለመንግሥት ካልደረሰው ወይም ሕዝብ  ያልተናገረውን መንግሥት ከሰማ እወደድ ባዮች ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ትተው መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ ይነግሩታል ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ብዛት ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ውጥንቅጥም ነው፡፡ በእምነት፣ በርእዮተ ዓለም፣ በመፍትሔ አቅጣጫ፣ በባህልና ቋንቋ፣ በዕውቀትና ሥልጣኔ፣ በዕድሜና ጾታ የተወነቀጠ ነው - ሕዝብ፡፡  ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚህን ሁሉ በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ መንግሥትን የሚወዱና የሚደግፉ፣ መንግሥትን የሚጠሉና የሚቃወሙም አሉ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚህን በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡
ሕዝቡ ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? ለምን እንዲህ አለ? ምን ስለ ሠራሁ ወይም ምን ስላልሠራሁ ነው? የትኛውን ችግሬን ስፈታው የሕዝቡ ጥያቄ ይመለሳል? ብሎ ማስተዋል ነው ሕዝብን መማዳመጥ ማለት፡፡ ሕዝቡ ስላልገባው ነው? ስላልተረዳ ነው? ስላልተማረ ነው? ስላልሠለጠነ ነው? እያሉ ጠያቂውን የችግሩ መነሻ ማድረግ ሕዝብን ያለመስማት ዋናው መገለጫው ነው፡፡ ‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› እያልን ‹ሕዝብ ንጉሥ ነው› የሚለውን እንዴት መቀበል ያቅተናል? ‹ደንበኛ አይሳሳትም› እያልን ‹ሕዝብ አይሳሳትም› የሚለውን እንዴት ማመን ይሳነናል?
በደርግ ጊዜ አንድ የገጠር ሕዝብ ያምጻል፡፡ መሬት ሲከፋፈል የመሬት ኮሚቴዎች በጉቦ አስቸገሩት
ከዛፍ ወደዛፍ ላይ ትዘላለች ጦጣ
መሬትን ያገኘ ኮሚቴን ያጠጣ
ብሎ ዘፈነ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ የመንደር ምሥረታ ተባለና የኖረበትን ቀዬ ልቀቅ ተባለ፡፡
ቤቱን አፍርሱ አሉን የበላንበትን
ማፍረስስ አልጋውን ትኋን ያለበትን
ብሎ ዘፈነ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ልጆችህ ይዝመቱ ተብሎ ወታደር ተመራበት፡፡
ልጅህን አምጣ ይላል የኛ ዘመናይ
እኔ ልጄን ስወልድ አዋልዶኛል ወይ
ብሎ ገጠመ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ በመጨረሻም ከእንግዲህ ደርግ ጠላታችን ነው፡፡ ለጠላታችን ለደርግ አንገዛም ብሎ ተማማለ፡፡ ነገሩ እየከረረ መሄዱን የሰሙ ካድሬዎች ወረዱና ሕዝቡን ሰበሰቡት፡፡ ሲነግሩት ዋሉ፡፡ ሲሰማቸው ግን አልዋለም፡፡ ስብሰባው ሲያልቅ ‹ጠላቶቻችን ይውደሙ› ብሎ ካድሬው መፈከር አሰማ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ድምጽ እጁን አውጥቶ ‹ይውደሙ› አለ፡፡ ካድሬዎቹም ደስ ብሏቸው ስብሰባውን በመፈከር አሳርገው ሄዱ፡፡ ለአለቆቻቸው ሕዝቡን አሳምነው እንዳስፎከሩት ተናገሩ፡፡ ሕዝቡ ያለው ሌላ እነርሱ ያዳመጡት ሌላ፡፡
ሕዝብን ማዳመጥ ማለት ሕዝብ የሚለውን ለማዳመጥ መቻል ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅኔ ሕዝብ ነውና ሕዝቡን ለማዳመጥ ባለቅኔ መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ማዳመጡን በሚሰጠው ምላሽ ነው የሚገልጠው፡፡ ምላሹ የሚወሰነው ለማዳመጥ በሰጠው ማስተዋል ነው፡፡ የመጣው ከዚህና ከዚያ፣ ከነ እንቶኔና ከነ እንትና ነው ማለቱን ትቶ ሕዝብ ተናግሯል ብሎ የሚያምን ከሆነ፣ ያንንም ይዞ ከየዓይነቱ ሕዝብ ጋር የሚመክር ከሆነ፡፡ መክሮም መንግሥት የሚፈልገውን ሳይሆን ሕዝቡ የጠየቀውን የሚመልስ ከሆነ፣ ያ መንግሥት ‹ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት› ይባላል፡፡
ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት መንግሥትን የሚሰማ ሕዝብ መፍጠር ይችላል፡፡ ሕዝብ የሚያከብረውን፣ የሚወደውንና ይሰማኛል ብሎ የሚያምነውን መንግሥት ይሰማል፡፡ መደማመጥ የጋራ ነው፡፡ ሕዝብ ፈጣሪው የሚለውን የሚሰማውኮ ፈጣሪዬ የምለውን ይሰማኛል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ፈጣሪ አይሰማኝም ካለማ ፈጣሪውን መስማት ያቆማል፡፡ ማንም የማያዳምጠውን አያዳምጥም፡፡ ፈጣሪም ‹ኑ እንዋቀስ› ያለው የሚወቀስ ነገር ኖሮት ሳይሆን ሕዝቡን እንደሚያዳምጥ ሲናገር ነው፡፡
ሕዝብ መንግሥት አያዳምጠኝም ብሎ ተስፋ ሲቆርጥ ቀስ በቀስ መንግሥትን ማዳመጥ ያቆማል፡፡ መንግሥት የመናገሪያ መሣሪያ ስላለው ብቻ ይናገራል፡፤ ሕዝብም ጆሮ ስላለው ብቻ ይሰማል፤ ግን አያዳምጥም፡፡ ነገሩን እውነት ነው ብሎ አይቀበለውም፡፡ ለእኔ ነው ብሎ ልብ አይለውም፡፡ አዳምጦም የሚፈለገውን ምላሽ አይሰጠውም፡፡
አንተ ስትናገር ያልፋል በእኔ ላይ
እኔም ስናገርህ ያልፋል ባንተ ላይ
ከንግዲህ ሆነናል ወንዝና ድንጋይ
የተባለውኮ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ወንዝ በድንጋይ ላይ ሲያልፍ ይጮኻል ግን ድንጋዩ አይሰማውም፡፡ ድንጋዩም ውኃው በላዩ ላይ ሲያርፍ ይጮኻል፤ ግን ወንዙ አይሰማውም፡፡
ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥትና እርሱ የሚፈጥረው መንግሥትን የማያዳምጥ ሕዝብ እንዲህ ናቸው፡፡

በ4ኛው የበጎ ሰው ሽልማት መሳተፍ ለምትፈልጉ

$
0
0

4ኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓም ከቀኑ በ7፡30 በአዲስ አበባ 22 አካባቢ በሚገኘው አቤል ሲኒማ ይከናወናል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር መሳተፍ ለምትፈልጉ 150 ሰዎች መግቢያ ተዘጋጅቷል፡፡
 
ዛሬ፣ ረቡዕ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓም ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ በኢሜይል begosew2008 @gmail .com ስምዎትንና የስልክ ቁጥርዎትን ይላኩ፡፡ ቀጥሎ ማረጋገጫ(Confirmation) ይላክልዎታል፡፡ ማረጋገጫው ከደረሰዎ በኋላ ከዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2008 ዓም ጀምሮ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው ምርፋቅ ካፌና ሬስቶራንት በመሄድ ስልክ ቁጥርዎን በመንገር ካርዱን መውሰድ ይችላሉ፡፡
 
መልካም ዕድል

‹ሀገር ማለት ሰው ነው›፤ እስኪ ሙት በለኝ!

$
0
0
click here for pdf


ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገርሙኝ ዘፈኖች አንዱ ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው ነው፡፡ እሥራኤላዊና ጂፕሲ ይህንን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? እላለሁ፡፡ አይሁድ በመላው ዓለም ለ1900 ዓመታት ያህል ተበትነው ሲኖሩ በየአካባቢው ሰው ነበራቸው፤ያውም እንደ ብረት የጠነከረ ማበረሰብ፤ ሀገር ግን አልነበራቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ አይሁድ ሀገር ፍለጋ ከሺ ዓመታት በላይ መኳተን አልነበረባቸውም፡፡በአውሮፓ የሚኖሩት ጂፕሲዎች የታወቀ ማኅበረሰብ አላቸው፡፡ነገር ግን ሀገር የላቸውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮ ጂፕሲ የሚባል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ጂፕሲ የሚባል ሀገርም ይኖር ነበር፡፡ ግን የለም፡፡
በአሜሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ‹በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን› የምትባል ሀገር ግን የለቺም፡፡ 1.3 ሚሊዮን የሚደረሱ ግሪኮች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ‹የአሜሪካ ግሪኮች› የምትባል ሀገር ግን የለችም፡፡ ‹ግሪክ ሲሠራ አሜሪካ ይኖራል፣ ሲያረጅ ግሪክ ይጦራል› የተባለው ሀገር ሰው ብቻ ስላልሆነ ነው፡፡ 
ሰዎች ተሰብስበው ሀገር ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ በየሀገሩ የተሰበሰቡ ማኅበረሰቦች ‹ኮሙኒቲ› ይባላሉ እንጂ ሀገር አይባሉም፡፡ ሀገር ሀገር ለመሆንና ለመባል ከሰው በተጨማሪ የምትፈልገው ብዙ ነገር አላትና፡፡ ሀገርን ሀገር ለማስባል መሬትም ያስፈልጋል፤ መሬት ሳይኖርህ ሰው ስለሰበሰብክ ብቻ ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡ ያውም የእኔ የምትለው፣ የምትሞትለትና የምትለፋለት ታሪካዊ መሬት ያስፈልግሃል፡፡ አይሁድ በ1930 አካባቢ በኡጋንዳ ኡዋሲን ጊሹ (Uasin Gishu County) በተባለ ቦታ እንዲሠፍሩና ሀገር እንዲኖራቸው ታስቦ ነበር፡፡ እንደ ቴዎዶር ኸርዝል ያሉ ታላላቅ የጽዮናዊነት መሪዎችም ለጊዜውም ቢሆን  ተስማምተውበት ነበር፡፡ብዙኀኑ አይሁድ ግን ‹ሀገር ማለት የሆነ መሬት አይደለም፡፡ ታሪካዊ መሬት ነው› ብለው ተቃወሙትሀገር ማለት የሆነ መሬት ብቻ ቢሆን ለአይሁድ ከዛሬዋ እሥራኤል ይልቅ በአየር ንብረትና በተፈጥሮ ማዕድን፣ ብሎም በአቀማመጥ ኡጋንዳ ትሻላቸው ነበር፡፡ 

ባድሜ ለምትባል ከጦርነቱ በፊት ብዙው ሕዝብ ሰምቷት ለማያውቅ መሬት የተደረገውን ጦርነት የረሳ ሰው ነው ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚል፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለባድሜ የተደረገው ጦርነት ለማን የተደረገ ነው ሊባል ነው፡፡ በሄግ ፍርድ ቤት የነበረው ክርክርስ የመሬት ክርክር እንጂ የሰው ክርክር ነበር እንዴ?
ሀገር ማለት ሰው ቢሆን ኖሮሰው ስለ ሀገሩ ሲያነሣ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሸለቆውን፣ ሜዳውን፣ ጫካውን እያነሣ ለምን ይዘፍን ነበር ፡፡
‹ያገሬ ተራራ ወንዛ ወንዙ ለምለም
እማማ ኢትዮጵያ ኑሪ ለዘላለም› ለምን ይል ነበረ፡፡
ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ይሄ የኔ ክልል፣ ጎጥና መንደር ነው የሚለው ክርክር ከየት ይመጣ ነበር? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ የተለየና የታወቀ የሀገር ድንበርና ካርታ ለምን ያስፈልግ ነበረ? ሰውማ የትም ነው የሚኖረው፡፡ ካርታ አያሻውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለምን የአብዛኞቹ ሀገሮች ብሔራዊ መዝሙር ስለ መሬቱና ስለ ድንበሩ ያወራል? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ለሰው ፓስፖርትና ቪዛ ለምያስፈልገዋል? ሰው ያለበት ቦታ ሁሉ ሀገሬ ስለሆነ ለምን እንደፈለግኩ ወጥቼ አልገባም? አንድ ሰው ወደ አንድ ሀገር ገባ የሚባለው ወደ መሬቱ ሲገባ እንጂ የሀገሩን ሰው ሲያገኝ ነው እንዴ? ምናልባትም ከአንታርክቲካ በቀር ቪዛ መጠየቅ ያለበት ሀገር አልነበረም፡፡ እርሱ ሰው የለበትምና ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› የሚለው አይመለከተውም፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ በሰማይ የሚሄድ አውሮፕላን ‹የአየር ክልሌን ጣሰ› ብሎ መሟገት ምን የሚሉት ሞኝነት ነው? ሰውን አልጣሰ፣ የጣሰው አየር ነው፡፡
ደግሞም አገር ማለት መሬት ብቻ አይደለም፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ አንታርክቲካ ሀገር ይሆን ነበር፡፡ ያማ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ የሚገኙ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ሰው አልባ ደሴቶች(nonecumene)‹ሀገር› ተብለው በተባበሩት መንግሥታት ይመዘገቡ ነበር፡፡ ሀገር ማለት መሬት ቢሆን ኖሮ መሬት ያለው ሁሉ ሀገር ይኖረው ነበር፡፡ የአሜሪካ ሕንዶች፣ የአውስትራልያ አቦርጅኖች፣ ከጥንት ጀምሮ የሚኖሩበት መሬት አላቸው፡፡ የራሳቸው የሆነ ሀገር ግን የላቸውም፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን የራሳቸው የሆነ የሚኖሩበት መሬት ነበራቸው፤ ሀገር ለመሆን ግን መዋጋት ነበረባቸው፡፡ ደቡብ ሱዳኖችን ያንሁሉ ዘመን ያዋጋቸው የመሬት ጥያቄ ሳይሆን የሀገርነት ጥያቄ ነው፡፡ የራሳቸውፖለቲካዊ መሬት አግኝተው እንኳን ሀገር ለመሆን ገና እየተሠሩ ነው፡፡ ፍልስጤማውያን ይብዛም ይነስ የሚኖሩበት መሬት አላቸው፡፡ አገር ግን የላቸውም፡፡
አገር ከዚህ ሁሉ በላይ ነው፡፡ ሰው፣ ሰው የኖረበትና ታሪክ የሠራበት መሬት፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከሰው፣ ሰው ከማኅበረሰብ፣ ሰው ከመሬት፣ ሰው ከአራዊት፣ ሰው ከተፈጥሮ፣ ሰው ከወራሪ ጋር የነበረው ትግል፣ ውጊያና ወዳጅነት፤ የተረተው ተረት፣ ያወጋው ወግ፣ የፈጠረው አፈ ታሪክ፣ ያከማቸው ትዝታ፣ ሰው ለመሬቱ፣ ለወገኑና ለእምነቱ የከፈለው መሥዋዕትነት፤ የዘፈነው ዘፈን፣ ያቅራራው ቀረርቶ፣ የፎከረው ፉከራ፤ ያገኘው ድልና የተሸከመው ሽንፈት፤ ያደረሰው በደልና የደረሰበት በደል ይሄ ሁሉ ነው ሀገር፡፡
መገለጫው ቅርስ፣ መዋሐጃው ባህል፣ መታያው ልብስና መዋቢያው ጌጣጌጥ፣ መገናኛው ቋንቋ፣ መዝናኛው ጭፈራ፤ ማስተማሪያው ተረት፣ መክበሪያው ዓመት ባል፣ መጠበቢያው ምግብ፣ መቆዘሚያው እንጉርጉሮ፣ መተከዣው ልቅሶ፣ መተኪያው ልደት፣ ማሳረጊያው ቀብር፤ መገምገሚያው ምግባር፣ ማነወሪያው ነውር፤ መኩሪያ ጀግንነቱ፣ ማፈሪያ ገመናው፤ መደበቂያ ቤቱ፣ መመረሪያ ጫካው፤ ይሄ ሁሉ ነው ሀገር፡፡ ታሽቶ ተገርኝቶ ያመጣው አንድነት፣ ተጣልቶ ተባልቶ ያመጣው ልዩነት፣ እንደ ዘሐ ዘጊ የተጠላለፈው፣ እንደ እግር ሠንሠለት የተቆላለፈው፣ ሲፈተል፣ ሲገመድ፤ ሲባዘት፣ ሲዳውር፤ ሲከካ፣ ሲሰለቅ፤ ሲጣላ፣ ሲታረቅ፤  ሲያውቅና ሲማይም፤ ሲሠለጥንና ሲደኸይ፤ ሲሰፋና ሲጠብ፤ የኖረውና የኖረበት፣ የኖረለትም ነው ሀገር፡፡
ሀገር ትዝታ ነው፡፡ የትም ቦታ ስትሄድ ጠምዶ የሚያመጣህ፡፡ ምንም ሥጋ ብትቆርጥ ከብቱ ትዝ ይልሃል፤ ምንም ቢች ዳር ብትዝናና ወንዙ ትዝ ይልሃል፤ ምን በሽቱ ብትታጠን አፈሩ ይሸትሃል፤ ምን በሥጋጃ ላይ ብትሄድ ጉዝጓዙ ይመጣብሃል፡፡ በኮምፒውተር እየሠራህ ያቦካኸው ጭቃ ይናፍቅሃል፤ በጄት እየበረርክ አህያና በቅሎው ያምርሃል፤ ማንሐተን ተቀምጠህ ሰባተኛ፣ ሎንደን ተቀምጠህ ቂርቆስ፣ ኖርዌይ ሆነህ ጅግጅጋ፣ ካናዳ ሆነህ ሐረር ይወዘውዝሃል፡፡ ሀገር ማለት ትዝታ ነው፡፡
ሀገር ማለት ከምትገልጠው ብታስበው፣ ከምትኖርበት ብትሞትበት፤ ከምትስቅለት ብታለቅስለት የምትመርጥለት ነገር ነው፤ ሀገር ማለት ትተህው ብትሄድ ትቶህ የማይሄድ፣ በራቅከው ቁጥር ልብህ ውስጥ የሚቀር፣ ባወቅከው ቁጥር የምትንገበገብለት፤ በተረዳኸው ቁጥር የምትሳሳለት፣ አንተን እርሱ ውስጥ እንደምታገኘው ሁሉ እርሱንም አንተ ውስጥ የምታገኘው፤ የተሠራህበት ውሑድ፤ የተቀረጽክበት ማንነት ነው ሀገር፡፡
ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመድ የሌለው ሰው ወደ ሀገሩ ለመምጣት ባልናፈቀ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዘመዶቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር ውጭ የሚኖሩለት ሰው ‹ሀገሬን ሀገሬን› እያለ መከራ ባላየ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰዎች በየዘመናቱ የበደሉት ሰው ሀገሬ በደለችኝ ባለ ነበር፡፡ ሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰው ስለ ሀገሩ ሲያስብ ተራራውና ወንዙ፣ አዕዋፉና አራዊቱ፣ ማሳውና ቀየው ለምን ትዝ ይለው ነበር፡፡ በሀገር ማለት ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ያሸነፈ አትሌት፣ ድል ያደረገ ኳስ ተጨዋች ባንዴራው ሲሰቀል ለምን ያለቅስ ነበር?
‹አዙረሀ አዙረህ ሀገሬ መልሰኝ
በሹም ታዘዘ አፈር አታልብሰኝ› ብሎ ለምን ያንጎራጉር ነበር፡፡ ዐጽሙ በአፈሩ እንዲያርፍ ለምን ይናዘዝ ነበር፡፡ ለምን ሙሾውን፣ የሠርግ ዘፈኑን፣ ወጉን ማዕረጉን ይፈልገው ነበር፡፡
ሀገር በአርምሞ እንጂ በንግግር፣ በተግባር እንጂ በዝርዝር ሊናገሩለት የማይቻል ነገር ነው፡፡ ውጥንቅጥ ሰበዞች የሰፉት ሞሰብ፣ዓይነተ ብዙ  ድርና ማጎች የሸመኑት ጋቢ፣ ልዩ ልዩ ቅመሞች የሠሩት ወጥ፣ ብዙ ገባሮች የፈጠሩት ዓባይ፣ ብዙ ትውልዶች የከመሩት ተራራ፣ ከአራቱ አቅጣጫ ተሰብስቦ በአንድ ወፍጮ የተፈጨ እህል፣ ከየአበባው ተቀስሞ በአንድ ቀፎ የተሠራ ማር፣  ከየእህሉ ወጥቶ በአንድ ማድጋ የተጠመቀ ጠላ፣ ከየ እንጨቱ ተለቅሞ በአንድ ጽንሐ የታጠነ ዕጣን ነው ሀገር፡፡
ሀገር ማለት ሰው ነው? እስኪ ሙት በለኝ

4ተኛው የበጎ ሰው ሽልማት

$
0
0

4ተኛው የበጎ ሰው ሽልማት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓም በአቤል ሲኒማ ተከናውኗል፡፡ በዕለቱ በየዘርፉ የተሸለሙት የሚከተሉት ናቸው፡፡



                 1.   በመምህርነት ዘርፍ


 መምህርአውራሪስተገኝ


 
መምህርአውራሪስተገኘየካቲት 27 ቀን 1959 .በጎጃምክፍለሀገርተወለዱ፡፡ከጎንደርመምህራንኮሌጅበሂሳብትምህርትዲፕሎማተመርቀዋል፡፡ከደብረብርሃንመምህራንኮሌጅየርዕሰመምህርነትስልጠናወስደዋል፡፡ከአዲስአበባዩኒቨርስቲንግድሥራኮሌጅበቢዝነስአስተዳደርናቴክኖሎጂበባችለርዲግሪተመርቀዋል፡፡

 
1979 /ጀምሮ18 ዓመታትበመምህርነትሙያያገለገሉትአቶአውራሪስባስተማሩባቸውአካባቢዎችለትውልዱየዕውቀትንወጋገንአብርተዋል፡፡መንግሥትየመጀመሪያደረጃትምህርትንለሁሉምማዳረስየሚልየሚሊኒየምየልማትግብከማስቀመጡአስቀድመውባስተማሩባቸውቃንጣባብጫየመጀመሪያደረጃ/ቤት፣ከበሴየመጀመሪያደረጃ/ቤት፣ዓለማየሁበዛብህየመጀመሪያደረጃ/ቤትባሉባቸውአካባቢዎችትምህርትለሁሉምሕፃናት›የሚልእቅድበመቅረፅ1980መጨረሻሁሉምሕፃናትእንዲማሩአድርገዋል፡፡
ለሰዎችበጎበማድረግየሚደሰቱትአቶአውራሪስየአርሶአደርልጆችንበየገጠሩበመዞር፤እስከሁለትቀንየእግርጉዞበመጓዝእናበአርሶአደሮችቤትበማደር፤ከአርሶአደሮችጋርየጠበቀጓደኝነትናማኅበራዊትስስርበመፍጠር፣አርሶአደሮችልጆቻቸውንወደትምህርትእንዲልኩየማሳመንስራዎችንበመስራትበቆዩባቸውየአንደኛደረጃርዕሰመምህርነትሙያበእርሳቸውበጎተፅዕኖ15 ሺህህፃናትበላይከመሃይምነትነፃአውጥተዋል፡፡ከህፃናትበተጨማሪበቢቡኝወረዳበግብርናሙያየተሰማሩአርሶአደሮችእናበጥንታዊየአብነት/ቤትየሚማሩተማሪዎችጎንለጎንዘመናዊትምህርትእንዲማሩአድርገዋል፡፡በወረዳውየማኅበረሰብንእሴትበመጠበቅማኅበረሰቡለዘመናዊትምህርትየነበረውንአሉታዊ ግንዛቤሙሉበሙሉቀይረዋል፡፡
ለማስተማርአቅምየሌላቸውንአርሶአደሮችልጆቻቸውንቤታቸውይዘውበማሳደግአስተምረዋል፡፡ለአካልጉዳተኛህፃናትምለመንቀሳቀሻአጋዥመሳሪያበመግዛትበርቀትምክንያትከትምህርትእንዳይቀሩአድርገዋል፡፡ከዚህየሚተርፋቸውንየወርደመወዝለተማሪዎቻቸውየኩራዝመብራትየሚሆንናፍጣገዝተውበመስጠትጠንክረውእንዲያጠኑበፅናትይመክሩነበር፡፡ሌሊትበቢቡኝወረዳባሉአርሶአደርመንደሮችበመዞርተማሪዎቻቸውእየጠኑመሆናቸውንይቆጣጠሩነበር፡፡በዚህምምክንያትአብዛኛውየቀለምልጆቻቸውበአገርውስጥናበውጭዩኒቨርስቲዎችበከፍተኛማዕረግተመራቂእንዲሆኑአስችሏቸዋል፡፡
በቡቡኝወረዳሁለተኛደረጃ/ቤትባለመኖሩተማሪዎችአንደኛደረጃትምህርታቸውከጨረሱበኋላብዙርቀትተጉዘውበብዙችግርይማራሉ፡፡አልያምትምህርታቸውንያቋርጣሉ፡፡ይህንችግርለመፍታትአቶአውራሪስተገኝበጎአድራጊለማፈላለግበእግራቸውተጉዘዋል፣ቤታቸውንሸጠዋል፡፡በመጨረሻምአቶዘውዴከተባሉግለሰብብር 3.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍተደርጎላቸውሁለተኛደረጃ/ቤቱእንዲሰራአድርገዋል፡፡አቶአውራሪስየተለያዩተቋማትንበማስተባበርሁለትቤተመጻሕፍትአሰርተዋል፡፡30 በላይየሚሆኑወላጆቻቸውንያጡህፃናትንአሳድገዋል፡፡
መምህር አውራሪስ ተገኝ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቀ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሠረት በመምህርነት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እንኳን ደስ አለዎት፡፡
 
           2. በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ

አቶሳሙኤልታፈሰ

አቶሳሙኤልታፈሰቂርቆስአካባቢከችግረኛቤተሰብየተወለዱኢትዮጵያዊየቢዝነስሰውናቸው፡፡የመጀመሪያደረጃትምህርታቸውንበፈለገዮርዳኖስ/ቤትእየተማሩሳለበልጅነታቸውጥቃቅንየተለያዩሥራዎችንበመሥራትቤተሰቦቻቸውንናራሳቸውንከመደገፍጀምረውአሁንላሉበትትልቅደረጃደርሰዋል፡፡አቶሳሙኤልየዛሬ1977 .ከሰዎች 10,000 ብርተበድረውደረጃ 9 ንግድፈቃድአውጥተውሥራቸውንበሕንፃዎችቀለምእናበጣራእድሳትጀምረውንግዳቸውንአስፋፍተዋል፡፡
አቶሳሙኤልበአሁኑሰዓት6,200 በላይሠራተኞችንየሚያስተዳድረውየሰንሻይንኮንስትራክሽንየግልማኅበርባለቤትናሥራአስኪያጅሲሆኑድርጅቱበዋናነትበኮንስትራክሽንኢንቨስትመንትላይተሰማርቷል፡፡ድርጅቱበቡታጅራቡሬያቤሎእናየቤንሻንጉልጉምዝአካባቢዎችአጅግአስቸጋሪየሆኑናተራራማመንገዶችንበመስራት15 በላይየሚሆኑየመንገድፕሮጀክቶችንአሳክተዋል፡፡ድርጅቱአሁንምበግዙፍየመንገድፕሮጀክቶችላይበመሳተፍላይነው፡፡
አቶሳሙኤልበሪልእስቴትዘርፍበመሰማራትምበገርጂ፣መሪ፣እና CMC (ሲኤምሲ) አካባቢየጋራአፓርትመንቶችንናቪላቤቶችንእየሰሩለህብረተሰቡአቅርበዋል፡፡ሰንሻይንግሩፕወደሆቴልኢንቨስትመንትበመግባትምማሪዮትኤክስኪዉቲቭአፓርትመንትኢንተርናሽናልሆቴልንበአዲስአበባእዉንያደረገሲሆንማሪዮትሆቴልንበአዲስአበባ፤ሒልተንሆቴልንደግሞበአዋሳለመገንባትበመንቀሳቀስላይይገኛል፡፡
አቶሳሙኤልየዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በበጎአድራጎትሥራበመሰማራትሰንሻይንፋውንዴሽንንበማቋቋምመማርለማይችሉወገኖች (ህፃናት) /ቤትከፍተዉበማስተማርላይናቸው፡፡
Ø  በነቀምትየዛሬ 8 ዓመት8,ሚሊዮን ብር1-10ክፍልየሚስተምር/ቤትበመገንባት 400 ተማሪዎችበመቀበልለህፃናቱበየወሩ 200 ብርየኪስገንዘብእየከፈሉያስተምራሉለህፃናቱምአስፈላጊውንዩኒፎርምናየትምህርትመረጃያቀርባሉ፡፡
Ø  በአክሱም 400 ልጆችየሚማሩበት/ቤት11,ሚሊዮን ብርከፍተውበየወሩ 200 ብርየኪስገንዘብእየሰጡያስተምራሉ፡፡
Ø  በጉራጌዞን18,ሚሊዮን ብር/ቤትአቋቁመው 350 ልጆችንበማስተማርላይናቸው፡፡በየወሩ 200 ብርየኪስገንዘብእየሰጡያስተምራሉ፡፡
Ø  በደብረ ብርሃንአንኮበርአካባቢም 4ኛውን/ቤትለመሥራትበዝግጅትላይናቸው፡፡
በተጨማሪምአዲስአበባላይ 30,000 ካሬሜትርወስደው35 ሚሊዮንብርየአረጋውያንመንደርበመሥራትላይሲሆኑ 400 አረጋውያንንለመርዳትአቅደዋል፡፡2010 .የአረጋውያንመንደሩንለመጨረስታቅዷል፡፡እንዲሁምበግሼንሌላኛውየአረጋውያንመንደርበመስራት 600 አረጋውያንንለማቀፍእየተንቀሳቀሱነው፡፡
አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሠረት በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
 እንኳን ደስ አለዎት፡፡


             3. በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ


ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

መኖሪያቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ የግዕዝ ጥናቶች ባለሞያ ናቸው፡፡ ዊኪፒዲያ ‹widely considered the foremost scholar of the Ge'ez language alive today.› ይላቸዋል፡፡ የተወለዱት ግንቦት 24 ቀን 1924 ዓም በሰሜን ሸዋ ሸንኮራ ሲሆን እኤአ ከ1945- 1951 ድረስ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተምረዋል፡፡ አኤአ በ1957 ከኮፕቲክ የነገረ መለኮት ኮሌጅ (ካይሮ፣ ግብጽ) በባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ የተመረቁ ሲሆን በዚያው ዓመት በካይሮ ከሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በቢ. ኤ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ እኤአ በ1962 ደግሞ ጀርመን ቱቢንገን ከሚገኘው ከኤበርሃርድ ካርልስ ዩኒቨርሲቲ (Eberhard Karls University, Tübingen) በሴማውያን ቋንቋዎች ፊሎሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች በማጥናት፣ የካታሎግ ሥራ በመሥራትና በጉዳዩ የሚያጠኑትን በማማከር ይታወቃሉ፡፡ በሚኒሶታ የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ሪጀንተስ ኤሚሪተስ ፕሮፌሰርሲሆኑ በሂል ሙዝየምና የብራና መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት ደግሞ ኪዩሬተር ኤሚሪተስናቸው፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እኤአ ከ1962-1969፣ እንዲሁም ከ1971-1974 ዓም የአማርኛ ሰዋሰው፣ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ የግዕዝ ሰዋሰው፣ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ፣ የዐረብኛ ሰዋሰው እና የሴም ቋንቋዎችን ሰዋሰው አስተምረዋል፡፡
እኤአ በ1976 ዓም በሂል ሙዝየምና የብራና መጻሕፍት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሥራ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከ5000 የሚበልጡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትን በማጥናትና ካታሎግ በማድረግ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን የብራና መጻሕፍት ካታሎግ ለሚያዘጋጁ ባለሞያዎች፣ የፓልግራፊ (paleography) የተጻፉበትን ዘመን መወሰን (dating) እና ሌሎች ሥልጠናዎችን ሲሰጡ ኖረዋል፡፡ በእነዚህ ዘመናትም የተለያዩ የጥናት መጽሔቶች የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የግዕዝ ሀብታችንን በተመለከተ በታወቁ ዐለም ዐቀፍ የጥናት መጽሔቶች ላይ ከ200 በላይ የጥናት ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን አያሌ መጻሕፍትንም በአማርኛና በእንግሊዝኛ አዘጋጅተዋል፡፡ አማርኛ መማሪያ ለጎልማሶች፣ አማርኛ መማሪያ ለጎልማሶችና ለመምህራን፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ ባሕረ ሐሳብ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ሐተታ ዘርአ ያዕቆብ፣ ግዕዝ በአዲስ ዘዴ (ግዕዝ በቀላሉ)፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች በአማርኛ ካዘጋጇቸው መካከል የሚተቀሱት ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጥናት ጽሑፎች አዘጋጅተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለሕዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በማኅበራዊ ጥናት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እንኳን ደስ አለዎት፡፡
 

                                       4. በሳይንስ ዘርፍ


ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ
ሎሬትዶክተር መላኩ ወረደ የተወለዱት አዲስ አበባ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእርሻ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና ዶክትሬታቸውን ደግሞ በ(Genetics and Plant Breeding) ከአሜሪካ አግኝተዋል፡፡
በአምቦ ሐሮያ እና በጂማ የግብርና ኮሌጆች በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን ወንጂ ስኳር ፋብሪካ በተመራማሪነት ተቀጥረው በሚሠሩበት ወቅት ‹አረማሞ› በመባል ለሚታወቀውና ምርት ስተጉል ለነበረ በሽታ መፍትሔ ያገኙ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ በዶክትሬት ጥናታቸው በዓለም ላይ በሚገኙ አራት ሺሕ የስንዴ ዝርያዎች የፕሮቲን ይዘት ላይ ምርምር አድርገው አራቱን በጣም ምርታማ የሆኑትን ለይተዋል፡፡ ከአራቱ ሦስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ፖርቱጋል ውስጥ የሚበቅለው አራተኛውም ከኢትዮጵያ የተወሰደ ነው በሚል ታሪክ ጠቅሰው ሞግተዋል፡፡ በዚህና በተለያዩ አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ናቸው በሚሏቸው የብዝኃ ሕይወት ላይ በዓለም መድረኮች ሁሉ ሽንጣቸውን ገትረው በሚያደርጉት ሙግት ይታወቃሉ፡፡
ሎሬትዶ/ር መላኩ ወረደ በወቅቱ የመጀመሪያውና ብቸኛው የነበረውንየዛሬውን የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲቲዩትና የዚያውን የኢትዮጵያዕፅዋጀነቲክ ሀብት ኢትዮጵያን በጠቅላላ ዞረው ያላትን የብዝኃ ሕይወት በማሰባሰብ ተቋሙን መሠረት አስይዘው አቋቁመውታል፡፡ ዛሬ ተቋሙ ያሠራውን ሕንፃም በስማቸው ሰይሞታል፡፡ ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ በተጨማሪም የሐዋሳ ግብርና ኮሌጅ መሥርተው ለረዢም ዓመታትም በመምህርነትና በዲንነት አገልግለዋል፡፡

በአገራችን የሚገኘው ነባር የሰብል ዘር ከመጥፋቱ በፊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማንበር ዘዴና የምርምር ተግባራት በተጨማሪ በገበሬው ማሳ ላይ ማንበርና ምርታማነቱን ብሎም ተመራጭነቱን ተጓዳኝ የሚያደርግ A Dynamic Farmer Based Land Race Conservation and Utilizationየተባለ አሠራር በዓለም ብቸኛው በመሆን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ይህ ዘዴ ከአገራችን አልፎ በመልማት ላይ ባሉ በርካታ አገሮች በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡    
ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ ከአብዛኛው ሳይንስቶች የሚለያቸውና ብዙ ጊዜም በአደባባይ ሲናገሩ የሚደመጡት ‹‹ለገበሬው ዕውቀት ቦታ መሰጠት አለበት፤ እነርሱን ማዳመጥ አለብን፤›› በሚለው አመለካከታቸው ነው፡፡ ‹‹ሳይንቲስቱ የራሱን ግኝት እነርሱ ላይ መጫን ሳይሆን የእነርሱን ባህላዊ አሠራር መሠረት አድርጎና አቀናብሮ መጓዝ ያስፈልጋል›› በሚለው አቋማቸውና ተግባራቸው ይታወቃሉ፡፡
ሎሬት ዶ/ር መላኩ በግብርናው መስክ ባደረጉት ምርምር (Alternate Nobel) ተብሎ የሚታወቀውን የ(Livelihood Award) ያገኙ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ ሎሬት ዶ/ር መላኩ ከ20 በለጡ ጥናቶች በአለማቀፍ ጆርናሎች በመጽጻሕፍትእና በልዩ ልዩ መልኩ አሳትመዋል፡፡በአሁኑ ወቅትም በሕመም ምክንያት ከቤት መንቀሳቀስ ባይችሉም ምክራቸውንና እርዳታቸውን የሚፈልጉ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ተቋማትን በምክራቸው እያገዙ ይገኛሉ፡፡
ሎሬት ዶ/ር መላኩ ወረደ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በሳይንስ ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እንኳን ደስ አለዎት፡፡

              5. በቅርስና ባህል ዘርፍ

 ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል ክብረት
ኢንጂኒየር ታደለ ብጡል የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ በ1919 ዓ.ም ነው፡፡ አራት ኪሎ በሚገኘው በዐለ ወልድ ቤተክርሰቲያን መንፈሳዊ ትምህርት እስከ ዳዊት ድረስ ተምረዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ የአስኳላ ትምህርታቸውን ቀድሞ ባላባትና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይባሉ በነበሩ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ ወደ ሀገረ አሜሪካም አቅንተው በስትራክቸራል ዲዛይን በሲቪል መሐንዲስነት ሙያ ተመርቀዋል፡፡ በዚህ ሙያቸውም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በርካታ የግንባታ ሥራዎች ላይ ተካፋይ ሆነዋል፡፡ የምህንድስና ትምህርት ከመማራቸው አስቀድመው በባንክ ባለሙያነት ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል፡፡
ኢንጂኒየርታደለ ብጡል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የማታ ትምህርትን ያስጀመሩ ናቸው፡፡ በታዋቂው አርበኛ የተሰየመውን ወንድይራድ ትምህርት ቤትን ከሌሎች ጋር በመሆን አቋቁመዋል፡፡ በድርሰቱም ዘርፍ በደራሲ ከበደ ሚካኤል፣ በዐፄ ቴዎድሮስ፣ በልዑል ዓለማየሁ፣ በሐኪም ወርቅነህ እሸቱ ላይ ከጻፏቸው መጻሕፍት በተጨማሪ የአማርኛ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትን በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ በአጠቃላይ ከአስራ አምስት በላይ መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፡፡
ኢንጂኒየርታደለ ብጡል የተለያዩ ባሕላዊ እና ትውፊታዊ ቅርሶችን ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በራሳቸው ወጪ በመግዛት በመሰብሰብ ይታወቃሉ፡፡ የሰበሰቧቸውን ቅርሶችንም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ሙዚየሞች በመለገስ ታሪካዊ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡
የአክሱም ሐውልት ብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባል በመሆንም የተለያዩ ኃላፊነቶችን ወስደው ሰርተዋል፡፡ ሐውልቱን ለማስመለስ ከሌሎች ጋር በመሆን ከአስራ ሰባት ዓመታት በላይ ታግለዋል፡፡ ኢንጂኒየር ታደለ የአክሱም ሐውልትን ለማስመለስ እንደ አርበኛም ጣሊያኖችን በመከራከር፣ እንደ ባለ ሀብት በገንዘባቸው፣ እንደ ምንሕድስና ባለሙያነታቸው የሐውልቱን አመላለስ የምህድስና ጉዳዮች አጥንቶ እንዲተገበር በማድረግ በወርቅ ቀለም የደመቀ ታሪክ ለመጻፍ በቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአክሱም ሐውልት መመለስ ጋር ተያይዞ “ኢትዮጵያዊ ፅናት” የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም እና 640 ያህል ገፆች ያሉት መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ 
ኢንጂኒየርታደለ ብጡል ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው በዳኞች ውሳኔ መሰረት በቅርስና ባህል ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እንኳን ደስ አለዎት፡

6. መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ
 

       ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የካቲት 11 ቀን 1936 ዓ.ም ትግራይ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ እንዲሁም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በባይሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመው አጠናቀዋል፡፡ በመቀጠል ወደ እንግሊዝ ሄደው ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡
ከዚያም በ1961 ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመልሰው በዩኒቨርሲቲ መምህርነትና በሳይንስ ፋኪልቲ ዲንነት፣ ሰርተዋል፡፡ ወደ አስመራ ዩኒቨርሲቲ ተልከው በፕሬዘዳንትነት ለስምንት ዓመታት በከፍተኛ ኃላፊነት መርተዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ በኋላም የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂ ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ቀጥሎም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በሥነ ሕይወትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከ30 በላይ ጥናቶችን በማሳተም፣ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ የሥነ ሕይወት ሀብታችንን የሚገልጹ መጽሐፎችን በማሳተምና በመሳሰሉት ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከዚህ አልፈው በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ማኅበረሰብ፣ ገበሬዎችና ከብት አርቢዎች የሥነ ሕይወት ሀብት ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ሕግ በተጨማሪም የአፍሪካን የባዮ ቴክኖሎጂ ሴፍቲ ሕግ በማርቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃም አገራችንንና አፍሪካን በመወከል በብዝኃ ሕይወትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በተመረኮዙ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በግንባር ቀደምትነት ተሳትፈዋል፡፡ በተለይ ጂ 77 ተብለው ለሚታወቁ ሀገሮች ዋንኛ ተከራካሪ ሆነው በመሪነት በተጫወቱት ሚና በሥነ ሕይወት ደኅንነትና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እንዲከበር፣ ታዳጊ ሀገሮች አገር በቀልና የማህበረሰብ መብቶች እንዲከበሩ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡ በታሪክ የተመዘገቡ ውጤቶችንም አስመዝግበዋል፡፡
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በአገራችን የአካባቢ ሥነ ሕይወትና ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ጉዳይ ሲነሳ ከማንም በላይ በታላቅ ክብር ስማቸው የሚነሳ የተከበሩ ሳይንቲስት ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በብዙ የምርምርና የትምህርት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች ዘንድ የከበረ ስም አትርፈዋል፡፡ በተሰማሩበት መስክ የአገርንና የህዝብን ጥቅም በማስቀደም በተለይም የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮች ጥቅም እንዲጠበቅ በቁርጠኝነት ጠንክረው ሰርተዋል፡፡ በተዳቀሉ እህሎች በእርዳታ ሰበብ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡና ትውልድ እንዳይበላሽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ተከራክረዋል፡፡ በአጭር መግለጫ ተገልጾ በማያበቃው ሥራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት "የምድር ሻምፒዮን"ተብለው ተሸልመዋል፡፡
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እንኳን ደስ አለዎት፡፡

                      7. በስፖርት ዘርፍ


ዶ/ር ይልማ በርታ
ከጉራጌ ዞን ምሁር የተገኙት የአትሌቲክስ አሠልጣኙ ዶ/ር ይልማ በርታ ገና የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረ ዘይት እየተከታተሉ ነበር ከስፖርት ጋር የተዋወቁት፡፡ የመረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና አትሌትክስን ቢያዘወትሩም በተለይ በሩጫው ዓለም በመካከለኛው ርቀት ሸዋን በመወከል ተወዳድረዋል፡፡
በጅማ መምህራን ማሠልጠኛ የመምህርነት ሥልጠና የወሰዱት ዶ/ር ይልማ ለሁለት ተከታታይ ክረምቶችም በደብረ ዘይት የሰውነት ማጎልመሻ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በደቦ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የቋንቋ አስተማሪ ተደርገው ቢመደቡም እርሳቸው ግን በትርፍ ሰዓታቸው ያሠለጥኑት የነበረውን ስፖርት የበለጠ ለማጠናከር ወደ ጅማ መምህራን ማሠልጠኛ ለተጨማሪ ሦስት ዓመት ከግማሽ ተመልሰው በመግባት የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ተከታተሉ፡፡
በመስከረም 1974 ዶ/ር ይልማ በርታ በቺኮዝሎቫኪያ ቻርለስ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል አገኙ፣ በቼክ ታዋቂው ዩኒቨርሲቲ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርትን እየተከታተሉ ከ800 እስከ 1500 ሜትር ድረስ በመካከለኛ ርቀት ተወዳዳረው ጥሩ ውጤትን ለዩኒቨርሲቲው አስመዝግበዋል፡፡ የመጀመሪ ዲግሪያቸውን በአትሌቲክስ ያገኙት ዶ/ር ይልማ በርታ በዛው ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመሥራት ተቀባይነት አገኙ፡፡ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በ1981 በስፖርት ኮሚሽን የመካከለኛ ርቀት አሠልጣኝ በመሆን ሥራ ጀመሩ፡፡
ወደ የመን በማቅናት የስፖርት አሠልጣኝ በመሆን የሠሩት ዶ/ር ይልማ በርታ ከየመን እንደ ተመለሱ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የ5ሺህ እና 10 ሺህ አሠልጣኝ በመሆን በርካታ ጀግና አትሌቶችን አፍርተዋል፡፡
ዶ/ር ይልማ በርታ ለዓለማችን ካበረከቱዋቸው ታላላቅ አትሌቶች መካከል ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ ሥላሴ ቀዳሚው ነው፡፡ የኢትዮዽያ አየር መንገድ ለዘረጋው የፓይለት ፕሮጀክት ከመለመሉዋቸው በርካታ አዳጊ አትሌቶች መካካል ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አንዱ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም በኃይሌ ብቃት የተማረኩት ዶ/ር ይልማ ኃይሌን እና ሦስት ጓደኞቹን ለብሔራዊ ቡድን መረጡዋቸው፡፡ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በወቅቱ የ5 እና 10 ሺህ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ  በነበሩት ዶ/ር ይልማ የሠለጠነው ኃይሌ በ1992 የደቡብ ኮሪያ የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5 እና 10 ሺህ አሸናፊ በመሆን ዓለምን በድል እንዲቀላቀል አደረጉት፡፡
በተለይ ከኃይሌ ጋር በርካታ ድሎችን ያጣጣሙት ዶ/ር ይልማ በሲዲኒ ኦሎምፒክ ከጉልበት ጉዳት ጋር እየታገለ ያሸነፈበትን ውድድር መቼም አይረሱትም፡፡ የብሔራዊ ቡድኑና የኃይሌ የማራቶን አሠልጣኝ በነበሩበት ወቅትም ኃይሌ በበርሊን ማራቶን የዓለም ሪከርድን እንዲሰብር አስችለውታል፡፡ የኢትዮዽን ቡድን በመምራትም በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና በርካታ ወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን በአሠልጠኝነት አግኝተዋል፡፡ በድል ያሸበረቀ ውጤታማ ታሪክ ያላቸው ዶ/ር ይልማ የተሰማቸውን በቀጥተኛ ተናጋሪነታቸውና ዕውቀታቸውን ለሌሎች በማጋራት ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ከዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ጋር ለረጅም ዓመት የሠሩት ዶ/ር ይልማ ‹በኮስትሬ ስኬት የተደበቁ ምርጥ አሰልጣኝ› ይሏቸዋል የስፖርቱ ተንታኞች፡፡ ከመካካለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ብሎም በመሰናክል ሩጫ ውጤታማ መሆናቸውን በመጥቀስ ተገቢውን ክብር ያላገኙ ታላቅ ሰው ይሏቸዋል፡፡
ዶ/ር ይልማ በርታ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቀ ተግባራቸው በዳኞች ውሳኔ መሰረት በስፖርት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ እንኳን ደስ አለዎት፡፡


                  8. በኪነ ጥበብ (ድርሰት) ዘርፍ

    አቶ አውግቸው ተረፈ

አውግቸው ተረፈ የኅሩይ ሚናስ የብዕር ስም ነው፡፡ የተወለዱት በጎጃም ክፍለ ሀገር በቢቸና አውራጃ በ1942 ዓም ነው፡፡ ዋና ትምህርታቸው ነባሩ የቤተ ክህነት ትምህርት ነው፡፡ በስማቸው የተጻፉ ጥቂት መጻሕፍት ቢኖሩም በአንባብያን ዘንድ ጎልተው የወጡ ሥራዎቻቸው ግን በአውግቸው ተረፈ ስም የታተሙት ናቸው፡፡
አቶ አውግቸው መርካቶ አሮጌ መጻሕፍት መሸጥ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አጫጭር ልብ ወለዶችን ኢ ልብ ወለድና የትርጉም ሥራዎችን፣ የሕጻናት ተረቶችንና መዝገበ ቃላት በማሰናዳት ከመታወቃቸውም በላይ ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመን መጨረሻዎቹ ዓመታት በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በአርታኢነት አገልግለዋል፡፡
አቶ አውግቸው ተረፈ በትክክለኛ ስማቸውና በሌሎች የብዕር ስሞቻቸው ከሃያ በላይ መጻሕፍትን የደረሱና የተረጎሙ ሲሆን ለኅትመት ከበቁ ሥራዎቻቸው የሚከተሉት በአንባቢያን ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ ከፈጠራ ሥራዎቻቸው መካከል ‹ወይ አዲስ አበባ› ‹ዕብዱ› እና ‹የፕሮፌሰሩ ልጆች›፣ ከትርጉም ሥራዎቻቸው መካከል የባልዛክ ‹ምስኪኗ ከበርቴ› የኦ.ሄንሪና የሌሎች ደራስያን ስብስብ የሆነውን ‹ያንገት ጌጡ›፣ የዳንኤላ ስቲል ‹ጽኑ ፍቅር› እና ‹ምስጢራዊቷ ሴት›፤ የሃሮልድ ሮቢንስ ‹ጩቤው› ሲገኙበት፣ ከኢ ልብወለድ ሥራዎቻቸው መካከልም በባቢሌ ቶላ የተጻፈው ‹የትውልድ ዕልቂት› ይገኝበታል፡፡
የአቶ አውግቸው መጻሕፍት ቀለል ባለ አቀራረብ ማኅበራዊ ሂስ የሚሰጡ የንባብን ፍላጎት የሚያነሳሱና በውጪው ዓለም ከፍተኛ ተነባቢነት ያገኙ እንዲሁም ዘመን አይሽሬ ከተሰኙ ደራስያን ተመርጠው የተተረጎሙ ናቸው፡፡
አቶ አውግቸው ተረፈ በአንድ ወቅት የደረሰባቸውን የእዕምሮ ሕመም መነሻ በማድረግ የጻፉት ‹ዕብዱ› የተሰኘው መጽሐፍ በአእምሮ ሕክምና ሰጪዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱና ለተሻለ ጥናት ግፊት በማሳደሩ፤ የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አውግቸው ይታከሙበት የነበረውን ሕንጻ በስማቸው ሰይሞላቸዋል፡፡
አቶ አውግቸው ተረፈ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በኪነ ጥበብ (ድርሰት) ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እንኳን ደስ አለዎት፡፡

1.                      

                 9. በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ

አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ

አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ በ1929 ዓም በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጢቾ አውራጃ፣ በጢቾ ከተማ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሩሲ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምርት ቤት፣ ሁለተኛውን ደግሞ በአዲስ አበባ ተምረዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ቢገቡም በወቅቱ በተፈጠረው ረብሻ ተባረው ሳይጨርሱት ቀርተዋል፡፡ በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በማታው መርሐ ግብር በፖለቲካ ሳይንስና በአስተዳደር በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም በሀገር ውስጥና በውጭ አጫጭር የጋዜጠኛነት ኮርሶችን ወስደዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የጋዜጠኛነት ሙያ መተዋወቅ ከጀመረበት ከ1950ዎቹ በኋላ ወደ መገናኛ ብዙኃን መጥተው ሞያውን ካስተዋወቁና ተጽዕኖ መፍጠር ከቻሉ ጥቂት ጋዜጠኞች አንዱ ናቸው፡፡
በ ‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›፣ በ ‹አዲስ ዘመን›ና በ ‹ድምጽ› ጋዜጦች ላይ ኮርኳሪ የሆኑ መጣጥፎችን በመጻፍና ማኅበራዊ ሂስ በማቅረብ እንዲሁም ታሪክ አዘል ድርሳናትን በመከተብ የሚታወቁት አጥናፍ ሰገድ ይልማ በጻፏቸው መጣጥፎችና ባዘጋጇቸው ጋዜጦች ሰበብ በንጉሡም ሆነ በደርግ  ሥርዓት ተመስግነዋል፤ ተቀጥተዋልም፡፡
ጋዜጠኛነት በዕውቀት የሚደገፍ፣ በእውነት የሚዘገብና ያለ አድልዎ የሚሠራ የተከበረ ሞያ እንደሆነ የሚያምኑትና በተግባርም ለመተርጎም የጣሩት አጥናፍ ሰገድ ይልማ በመጠሪያ ስማቸውና በብዕር ስማቸው ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን መጣጥፎች ሠርተዋል፡፡ ወጣቶችም ለሞያው ዲሲፕሊን እንዲገዙ አድርገዋል፡፡ የታላላቅ ሰዎችን የሕይወት ልምድ ሕዝቡ እንዲካፈለው አመቻችተዋል፡፡ የነገሥታትንና የዐርበኞችን የተዳፈነ ታሪክ ሰነዶችን ፈትሸው በማውጣት አስነብበዋል፡፡
የደርግ ሥርዓት ካለፈ በኋላም በተመሠረቱ የግል ጋዜጦች ላይ አስተዋጽዋቸው የጎላ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ደግሞ በደራሲነት ስማቸው መጠራት ጀምሯል፡፡ ‹የበደል ካሣ› የሚል ልቦለድ፣ ‹የአቤቶ ኢያሱ አነሣስና አወዳደቅ›፣ እንዲሁም በቅርቡ ‹የሕይወቴ ምሥጢር› በሚል ርእስ ለ50ኛ የጋብቻ በዓላቸው ማስተዋሻ የሚሆን መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡
አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ልምዳቸውን ለማካፈል የማይሰስቱ፣ የወጣት ደራስያንን ሥራዎች በማርታት የሚተባበሩ፣ በየመድረኩ የአንጋፋ ጋዜጠኞችንና ደራስያንን ታሪኮች በመዘከር የሚያብራሩ፣ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች የሚገለግሉ፣ አንጋፋ ደራሲና ጋዜጠኛ ናቸው፡፡
አቶ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በሚዲያና ጋዜጠኛነት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
 እንኳን ደስ አለዎት፡፡ 

                    10. በበጎ አድራጎት ዘርፍ


ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ
ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ በከንባታ ጠንባሮ ዞን ተወለዱ፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ከ4ኛ ክፍል በላይ የተማረች ብቸኛዋ ሴት ነበሩ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በእስራኤል ለመከታተል ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው በእስራኤል ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ በፊዚዮሎጂ እና ማይክሮ ባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ወደ አሜሪካ ተጉዘው በፓራሲቶሎጂ የድምረቃ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከማሳቹስቴስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ አገራቸው ሲመለሱ የነበራቸውን 5000 (አምስት ሺህ) የአሜሪካ ዶላር ግብአት አድርገውና ከእህታቸው ጋር ተባብረው ኬ.ኤ.ም.ጂ የተሰኘውን ድርጅት እ.ኤ.አ በ1997 በከንባታ ጠንባሮ በአላባ ዞን አቋቋሙ፡፡ ድርጅቱ በወቅቱ በሰፊ ተዛምቶ የነበረውን የኤች.አይ.ቪ በሽታን መከላከል፣ የሴቶችን መጠቃት፣ የልጃገረዶችን ግርዛት፣ ጠለፋንና ሌሎችም ለሴቶች ጎጂ የሆኑ የባህል ተጽእኖዎችንና ልምዶችን የመግታት አላማ አንግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኬ.ኤም.ጂ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በ26 ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠና የተለያዩ መርሀግብሮችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በቀጥታ ከ481ሺህ በላይ፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ከ2ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግረና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች (ከዚህ መካከል 70% የሚሆኑት ሴቶች ናቸው) በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡
የሴቶችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልእንደ ግርዛት፣ ጠለፋ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲሁም ጆሮ ያልደረሱ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን መግታትና ሴቶች በክብር እንዲኖሩ ማድረግ ዓላማቸውሆነ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን ጊዜ፣ ቁሳቁስ፣ እውቀት፣ ከሰው መግባባትና ህይወት የሰጣቸውን እድል ሁሉ ተጠቅመው በማህበረሰባቸው የለውጥ ምክንያት ለመሆን ተነሱ፡፡
ዶ/ር ቦጋለች እጅግ ብዙ የሆኑ ለራሳቸው ኩራትና እርካታ ለህብረተሰባቸውም አለኝታ የሚሆኑ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ እሳቸው የመሯቸው መርሃ ግብሮች በከንባታ የሚገኙ ሴቶች ለራሳቸው መብት እንዲቆሙ፣ ኑሯቸውን የሚመሩበት የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውና በራሳቸው እንዲተማመኑ አስችሏቸዋል፡፡ በህብረተሰቡም ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በከንባታ ጠንባሮ እ.ኤ.አ በ1999 100% የነበረ የሴቶች ግርዛት ስርጭት እ.ኤ.አ በ2008 በተደረገ ጥናት 3% ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህን ተከትሎም ከግርዛት ጋር ተያይዞ ሴቶች በወሊድ ወቅት የሚደርስባቸው ስቃይና ሞት ቀንሷል፡፡ አስር ሚሊዮን ችግኞችንም በማስተከል የአካባቢው ሥነ ምህዳር እንዲሻሻል ጥረዋል፡፡
ዶ/ር ቦጋለች በማህበረሰቡ አስተሳሰብ ላይ በወንዶችም ጭምር ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ የማኅበረሰብ ውይይትን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥመው በሁሉም የገጠር ክፍሎች ተግባራዊ ማድረጋቸው ይህ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህ ምክንያትም እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም ያልተገረዘች ሴት ባል ማግባት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ እናም ያልተገረዘች ሴት ባል ማግባት ችላለች፡፡
ዶ/ር ቦጋለችየእናቶችና ማህጸን ሆስፒታል ከንባታ ላይ እንዲሠራ፣ ሴት ተማሪዎች የሥራ እድል እንዲያገኙ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አይደፈሬ የነበረውን የጎጂ ባህል ተጽእኖ ሰብረው በማህበረሰብ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ በኬ ኤም ጂ አማካይነት ያከናወኗቸው ሥራዎችና የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች በአገራችን ለወጡ አዳዲስ ህጎች በግብዓትነት ጠቅመዋል፡፡
ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ የላቁ ተግባሮቻቸው የተነሣ በዳኞች ውሳኔ መሰረት በበጎ አድራጎት ዘርፍ የ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ እንኳን ደስ አለዎት፡፡ 

የበጎ ሰው ሽልማት የ2008 ልዩ ተሸላሚ
      ለቤተሰባቸው ስምንተኛ ልጅ ናቸው፡፡ ልጅነታቸውም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያጌጠ ብቻ ሳይሆን ‹‹አስኳላ›› ተብሎ ይጠራ በነበረው ዘመናዊ ትምህርት የታጀበ ነበር፡፡ ለግብረ ዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት በተወለዱበት ቀዬ ከአጠናቀቁ በኋላ በ14 ዓመታቸው አዲስ አበባ የመጡት እኚህ በዛሬው ቀን ስማቸውን በአክብሮት የምንጠራው የዓመቱ በጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ፤ በአርበኛነታቸው፣ በደራሲነታቸውና በአሳታሚነታቸው ይታወቃሉ፡፡
      በ1928 ዓ.ም. ፋሽስት ጣልያን ያወጀውን ጦርነት ይፋ ሲያደርግ፤ ‹‹ሀገሪቷ አትደፈርም፣ ባንዲራዋም እንዲረክስ አንፈቅድም›› ካሉ ወጣቶች መካከል ራሳቸውን መድበው አኩሪ ተጋድሎ ፈጽመዋል፡፡ በራሪ ወረቀት አሰናድተው የዓለም መንግሥታት ማኅበር ጦርነቱን አስመልክቶ ያሳየውን ቸልታ በብርቱ ተቃውመዋል፡፡ በወቅቱ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ለማኅበሩ ለማሳወቅ ወደ ጄኔቭ አምርተው ነበርና የእኝህ ሰው ተቃውሞና ነቀፌታ መወደድን አላተረፈም፡፡ ስለሆነም የሀገር ግዛት ሚኒስቴር እሳቸውንና ጽሑፋቸውን አሳድዶ ያዘ፡፡ ‹‹ባለን የጦር መሣሪያ እንዋጋ ብለህ ቅስቀሳ አካኺደሃል፤ ንጉሡን አዋርደሃል›› ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው እኝህ አርበኛ፤ ኢትዮጵያዊ ወኔ ቀስቅሷቸው እንጂ በልቦናቸው ክፋት አድሮ እንዳልጻፉት ተናገሩ፡፡ ቀደም ሲልም ሌቦችና ጉቦኞች ከሥልጣናቸው መውረድ እንዳለባቸው የሚጠቁም ግጥም ጽፈው በማሠራጨታቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበርና፤ አሁንም ማንኛውም ጽሑፍ ለመንግሥት ሳያሳውቁና ሳያስፈቅዱ አሳትመው ቢያሠራጩ መንግሥታዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በሚኒስትሩ በኩል ተናገራቸው፡፡
      የጣልያን ጦር እየገፋ ሲመጣ ‹‹የኢትዮጵያ ፋና›› ብለው ለሚጠሩት በራሪ ዕትማቸው፤ ስለ ጠላት እንቅስቃሴ መረጃ ያስነብቡ ነበር፡፡ የሕይወት ታሪካቸውም እንደሚያስረዳው ‹‹ሃገሪቱ ምንም ዓይነት ሚዲያ ባልነበራት በዚያ ወቅት የመንግሥትና የሕዝቡ አፈ ቀላጤ ብቸኛው ሰው›› ሆነው ነበር፡፡ ሕዝቡ እንዳይዘናጋና በጽንዓት ተጋድሎውን እንዲፈጽም እየጻፉ፣ የጻፉትን እያሳተሙ፣ ያሳተሙትን በነፃ እያሠራጩ ሳለ፤ ከቅርብ ሰዎቻቸው መካከል እንዱ የሚያደርጉትን ትግል ለጣልያን ጠቆመባቸው፡፡ ለጣልያን አድረው የነበሩ ሌሎች ግለሰቦችም፤ ተጠቋሚው ሰው ‹‹የተረገመ ነው፤ ሃገሩን የከዳ፣ ክብሩን ነጻነቱን አበሻን የጎዳ›› በሚል ግጥም አዋርዶናል፤ ብለው አቂመውባቸው ተከታተሏቸው፡፡ ማተሚያ ቤታቸውም ሊዘጋባቸው እንደሆነ ገመቱ፡፡ የተፈራው አልቀረም፤ ጣልያኖቹ ወደሳቸው መጡና አስረው ወሰዷቸው - ወደ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ፡፡ ማተሚያ ቤቱ ሲፈተሸ ግን የተባሉት ጽሑፎች ሳይገኙ ቀሩ፡፡ እሳቸውም ‹‹የቅስቀሳ ጽሑፍ አልበተንኩም›› አሉ፡፡ ሆኖም ግን ለፍርድ ግራዚያኒ አደባባይ ቆሙ፡፡
      የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ጄነራል ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ ሰበብ ጣልያን የበቀል እርምጃውን መውሰድ ሲጀምር እኝህ ባለታሪክ ‹‹ከሴረኞቹ ጋር የቀረበ ወዳጅነት አለህ›› ተብለው ይታደኑ ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣ የኅትመት ሥራቸውን አቋርጠው፣ ቀስቃሽ ጽሑፎችን መበተን አቁመው፣ ከአርበኞች ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ከባላምባራስ አበበ አረጋይ ጋር ተጋድሎአቸውን ያስመሰክሩ ጀመር፡፡ የጦር ስልት መንደፍ፣ አርበኛው ለአንድነቱ እንዲተጋ ማድረግ ሥራቸው ሆነ፡፡ የውስጥ አርበኞችን መዋቅር እንዲዘረጉ፣ የመረጃ ማቀነባበርና የማቀበል ሐላፊነትም እንዲረከቡ ሹማምንቱ ወሰኑ፡፡ የቀዘቀዘውን የአርበኞች ትግል ዳግም ለማነሣሣት በማኅበር ስም መንቀሳቀስ አዋጭ እንደሆነ ተረድተውም ‹‹የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር›› እንዲቋቋም ዓላማ ነደፉ፤ መዋቅሩን ዘረጉ፤ ተግባሩን አብራሩ፤ የማደራጀቱን ሥራ እነ ራስ አበበ አረጋይ ይዘው እውን አደረጉት፡፡
      የውስጥ አርበኝነት ሥራቸውን እንዲሠሩም ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ‹‹ከአርበኞቹ ጋር አልተስማማሁም›› ብለው ለአንድ የጣልያን አገልጋይ እጃቸውን ሰጡና ቃለ መሐላ ፈጽመው፤ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ያለውን የጣልያንን ጦር እንቅስቃሴና ጠቅላላ ሁኔታ መሰለል ቀጠሉ፡፡ በአርበኛነት ዘመናቸው የስት ልጆቻቸው እናት የሆኑት ወ/ሮ ቀለሟ ገብረ ወልድ በወረርሽኝ ሕመም መሞታቸውን ሰምተው ክፉኛ አዘኑ፡፡ ወ/ሮ ዓለሚቱ ንጉሤንም አግብተው ሁለተኛውን ትዳራቸውን መሠረቱ፡፡
      ኢትዮጵያ የነጻነት ክብርዋ ሲመለስላት የኅትመት ሥራውን በአዲስ መንፈስ ተያያዙት፡፡ የማተሚያ መሣሪያዎቻቸው ተወርሰው ወደ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት እንዲዛወሩ ጣልያን አመቻችቶ የነበረ ሲሆን፤ ተስፋ ሳይቆርጡ ከግእዝ ወደ አማርኛ እየተረጎሙ፣ እያባዙ፣ የጸሎት መጻሕፍትን እያሠራጩ ከወረራው በፊት የነበረውን ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡
      የነዮፍታሔ ንጉሤን፣ የነ ከበደ ሚካኤልንና የብላታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን መጻሕፍት ከደራስያኑ እየተቀበሉ አትመው ማሠራጨታቸውን ቀጠሉ፡፡ ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያ (ማሽን) ከውጪ ሃገር አስመጥተው ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ትምህርት ነክ የሆኑ መጻሕፍትን በብዛት አትመው ለማሠራጨት ቆርጠው ተነሡ፡፡ ማተሚያ ቤቱን ተከሉ፡፡ የሕይወት ታሪካቸውን የያዘው መጽሐፍ እንደሚያስረዳው፤ ማተሚያ ቤቱ በኢትዮጵያ የኅትመት ኢንዱስትሪ ታሪክ በግሉ ዘርፍ የመጀመሪያውን ቦታ የያዘ ነው፡፡
      ማተሚያ ቤቱ በግእዝና በአማርኛ የተጻፉ፤ የጸሎት፣ የድርሳናት፣ የተአምራት፣ የገድላት፣ የትርጓሜና የወንጌላት መጻሕፍትን አትሟል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓትና፣ የሰዋስው ፅንሰ ሐሳብን፣ ልብ ወለድ ድርሰቶችን፣ የኢትዮጵያ ታሪክንና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚያስተዋውቁ ከ 360 በላይ መጻሕፍትን አትመው አሠራጭተዋል፡፡ እኒህ የጥበብ ሰው ተርጉመዋል፣ አስተርጉመዋል፡፡ የልዑል መኮንን የሕይወት ታሪክ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የአመራር ጉዞ ጽፈዋል፡፡ ማተሚያ ቤቱ በስማቸው የሚጠራ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ 80 ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ልጆቻቸውም ይኸው ማተሚያ ቤት ሥራው እንዲቀጥል ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ በአርበኛነት ዘመናቸው ለፈጸሙት ጀብዱም የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡ በደርግ ዘመን በጽፎቻው የተነሣ ለመታሠር በቅተዋል፡፡
      እኝህ በሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት መሥራችነት፣ በአርበኛነት፣ ማተሚያ ቤት በመመሥረትና በአታሚነት የሚታወቁ፤ በግጥሞቻቸው ሀገር የመውደድን ትርጉም ይሰብኩ የነበሩት አባት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ 97 ዓመታቸው ነው፡፡ የተወለዱት ግንቦት 26 ቀን 1892 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ፣ ቡልጋ ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ በየመጽሐፎቻቸው ቡልጋን ያነሧታል፡፡ የእሳቸው ሐሳብ ያረፈበት የፊደል ገበታ በየቤታችን ግድግዳ ተለጥፎ፣ በእጅም ተይዞ ተምረንበታል፡፡ የአማርኛ ሆሄ በያዘው በዚህ የፊደል ገበታም የሚከተለው ዓረፍተ ነገር ሠፍሮ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ዕውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ፤ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ፤›› ለእኝህ የተከበሩ አርበኛ፣ የብዕርና የኅትመት ባለሞያ፤ ‹‹የዓመቱ በጎ ሰው›› የተሰኘው የሽልማት ድርጅታችን ‹‹ልዩ ተሸላሚ›› ሲያደርጋቸው ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡
ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ !


ሦስቱ የሕዝብ ማስጠንቀቂያዎች

$
0
0
ሕዝብ ለመሪው በሦስት ደረጃ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው ‹አርም› የሚል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ ሦስት ነገሮችን አምኗል ማለት ነው፡፡ አንድም መሪው በጎ ኅሊና አለው፤ ለማረም የሚችል ዐቅም አለው፤ ችግሩ የተፈጠረው ከአሠራሩ ላይ ነው ብሏል፡፡ አንድም ደግሞ ሕዝቡ መሪው እንደማንኛውም ፍጡር ተሳሳተ እንጂ ራሱ ስሕተት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሊያርም ይችላል ብሎ አምኗል፡፡ በመጨረሻም ሕዝብ መሪውን ይወዳል፣ ስሕተቱን ግን ይጠላል ማለት ነው፡፡
 
እዚህ ላይ የደረሰ መሪ የታደለ የሚሆነው ስሕተቶቹን ነቅሶ ‹ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ› ለማረም ከቻለ ነው፡፡ የሚሳሳት ፈጣሪ እንደሌለ ሁሉ የማይሳሳት መሪ የለም፡፡  መሪዎችን ታላቅና ታናሽ የሚያደርጋቸው ስሕተታቸውን ለማመንና አምነውም ለማረም ያላቸው ዐቅምና ቁርጠኛነት ነው፡፡ መሪ የሕዝቡን ጥቆማ ሰምቶ፣ የሕዝቡንም ልብ አድምጦ ችግሩን በጊዜ ካረመ ስሕተቱ ከሥራ የመጣ እንጂ ከመሪው ጠባይ የመነጨ አይደለም ብሎ ሕዝብ በመሪው እንዲተማመን ያደርገዋል፡፡ ‹ከሰው ስሕተት፣ ከብረት ዝገት አይጠፋም› ብሎ ያልፈዋል፡፡ ሕዝብ የነገረውን ስሕተት ከማረም ይልቅ ‹እኔ ደኅና ነኝ ችግሩ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው› እያለ ችላ ካለው ሕዝብ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ይሻገራል፡፡ ጃን ሜዳ ሠፍሮ እያደመ ራስ ተፈሪን ወደ ዙፋን ያመጣው መሐል ሠፋሪ ጦር (ሠራዊቱ) ነበር፡፡ በኋላም አርሙ ቢላቸው አላርም ሲሉ በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ይኼው ሠራዊት ነው፡፡    
 
ሁለተኛው የሕዝብ ማስጠንቀቂያ ‹ታረም› የሚል ነው፡፡ ሕዝብ  መሪውን ‹ታረም› ካለ ሁለት ነገሮችን አስቧል፡፡ ‹መሪው ልክ ነበር ነገር ግን  እንደማንኛውም ፍጡር ተሳስቷል› የሚለው ሐሳቡን ቀይሯል፡፡ ‹መሪው ስሕተቱን ሊያርም ይችላል› ከሚለው ወጥቷል፡፡ ይህንን ዕድል ላይመለስበት አልፎ መሪው ስሕተት የሚሠራ ሳይሆን ስሑት (የተሳሳተ) መሪ ነው፡፡ ስሕተቱ ከሥራ ሂደት ሳይሆን ከአመራሩ፣ ከአስተሳሰቡና ከአካሄዱ የመጣ ነው፡፡ ተግባሩ እንዲስተካከል መሪው መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝቡ አምኗል ማለት ነው፡፡ ከኩርንችት በለስ፣ ከአጋምም ወይን ሊለቀም አይችልም፡፡ ውኃው እንዲስተካከል ምንጩ መስተካከል አለበት ብሎ ሕዝብ ማሰብ ጀምሯል፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን መሪው ራሱን ሊያረም የሚችል መሪ ነው ብሎ አምኗል፡፡
 
በዚህ እከን ላይ የደረሰ መሪ ራሱን ፈትሾ፣ መርምሮና አንጥሮ እንደ ወይን ግንድ እየገረዘ ሸለፈቱን መጣል አለበት፡፡ ሌላውን ሰውነት ለማዳን ሲባል ሕመምተኛው የሰውነት አካል እንደሚቆረጠው ሁሉ ሀገርን ለማዳን ሲባል የሚቆረጡ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ አካሄዶች፣ መሪዎች፣ ፖሊሲዎችና መርሖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹ታረም› የተባለ መሪ እነዚህን አርሞ እንደ እባብ ሳይሆን እንደ ንሥር ታድሶ ከመጣ፤ ጥፋቱ ከአፈጻጸሜ የመጣ ነው፣ ሕዝቡ ስላልገባው ነው፣ ስላልተማረ ነው፣ ስላልሠለጠነ ነው፣ እያለ የመሥዋዕት በግ ፍለጋ ካልኳተነ፤ ‹ችግሩ እኔ  ነኝ፤ መፍትሔውም የእኔ መለወጥ ነው› ብሎ ካመነ፤ አምኖም ከሠራ፤ ሠርቶም ከተለወጠ፡፡ ሕዝቡ፡-
‹አሁን ወጣች ጀንበር
ተሸሽጋ ነበር› ብሎ ይቀበለዋል፡፡
ይህንን ሁሉ ትቶ መሪው በሕዝቡ ትዕግሥት ላይ ከቀለደ፤ ሕዝብም ለትዕግሥቱ ምላሹ ካለፈው የባሰ፣ ከተስፋው ያነሰ ሲሆንበት፤ ሕዝብ አመለካከቱን ይቀይራል፡፡ አርም፣ ታረም ማለት ዋጋ አልባ መሆኑን ይረዳል፡፡ ሊያርም ሊታረም የሚችል መሪና አመራር የለም ብሎ ያምናል፡፡ ችግሩ መሠረታዊ ነው ብሎ ይረዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስተኛውንና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያውን ይሰጣል፡፡ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን ሆ ብሎ ወደ ሥልጣን ያመጣው ወታደር፣ ስሕተቶቻቸውን ማረም ሲያቅታቸው በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያደረገው ወታደር፤ በ1966 ደግሞ ሥልጣናቸውን አሳጣቸው፡፡ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ‹ታረም› የሚል መልእክት እንዳለው ንጉሡ ቢረዱ ኖሮ የ66ቱን ነገር ያስቀሩት ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ‹ታረም› የሚለውን አልረዳ ሲሉ ‹ተወገድ› የሚለው የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ መጣ፡፡ 
 
ደርግም እንዲህ ነበር፡፡ በ66 አብዮቱ ሲፈነዳ፣ መሬት ላራሹ ሲታወጅ የሕዝብ ድጋፍ ነበረው፡፡ ቆይቶ ስሕተት ሲያበዛ ‹አርም› የሚለው መልእክት ከያቅጣጫው መጣ፡፡ ሰልፎች፣ ወረቀቶች፣ ተቃውሞዎች መጡ፡፡ ከማረም ይልቅ ‹መረምረም› ስለመረጠ የመጀመሪያውን ዕድል አሳለፈው፡፡ ከውስጥና ከውጭ ጠብመንጃ አንሥተው ግራ ቀኝ የወጠሩት ኃይሎች ‹ታረም› ቢሉትም መታረም ትቶ ማውደምን መረጠ፡፡ የ1981 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ‹ተወገድ› የሚለውን መለከት ነፋ፡፡ ደርግ የሚተርፍ መስሎት ለፋ፡፡ ግን ተወገድ ከተባለ በኋላ መትረፍ በተአምር ብቻ ነበርና ሊተርፍ አልቻለም፡፡
 
ይህ ‹ተወገድ› የሚለው ሦስተኛው  ማስጠንቀቂያ የመጨረሻው የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ መሪው ታምሞ አይደለም፡፡ ራሱ በሽታ ነው፡፡ ተቸግሮ አይደለም፡፡ ራሱ ችግር ነው፡፡ ደክሞ አይደለም፡፡ ራሱ ደካም ነው፡፡ ተፈትኖ አይደለም፤ ራሱ ፈተና ነው ብሎ አምኗል፡፡ ስለዚህም መፍትሔው መወገድ ብቻ ነው ብሎ ይቆርጧል፡፡ ቆርጦም ይሠራል፡፡ ሕዝብ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ መመለስ ብዙ ጊዜ ከባድ ነው፡፡ ማረምንም መታረምንም ከሚቀበልበት እርከን አልፏልና ቀሪው ዕድል የሚሆነው በሰላም መሰናበት ነው፡፡
 
የአንድ መሪ ብስለት በሁለት ደረጃ ይለካል፡፡ የመጀመሪያው ሲቻል በፊተኛው፣ ሳይቻል በቀጣዩ ደረጃ ላይ መንቃት፣ ነቅቶም  ተገቢውን ማድረግ፡፡ ያም ዘመን ካለፈና ጀንበር ካዘቀዘቀች ደግሞ ራሱንም ሀገሩንም ሳያጠፋ መልካም የወንድ በር ማዘጋጀት ነው፡፡
ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማዕ፡፡  




ተቀምጠው የሰቀሉት

$
0
0



የኢራቅ ኩርዶች እንዲህ ይተርካሉ፤
አንዲት የልዑል ልጅ ነበረች፡፡ አንድ የምታፈቅረው ልጅም ነበረ፡፡ ታድያ ከአንድ የቤተ መንግሥቱ ጠባቂ ጋር ትመካከርና ይህንን ፍቅረኛዋን ክፍሏ ድረስ ታስገባው ነበር፡፡ የቤተ መንግሥቱ ጥበቃ የተወሰነ ገንዘብና ልብስ ትሰጠው ስለነበር በደስታ ምሥጢሩን ይደብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ልዕልቲቱና ፍቅረኛዋ አፕል ቆርጠው እየተጫወቱ ይበሉ ነበር፡፡ ሁለቱም አፋቸውን ከፍተው የአፕሉን ቁራጭ አንዳቸው ወደሌላቸው አፍ ወርውሮ የማስገባት ጨዋታ ነበር የሚጫወቱት፡፡ 
እየተሳሳቁ የአፕል ቁራጭ ወደየአፎቻቸው ሲወረውሩ ልዕልቲቱ የወረወረችው የአፕል ቁራጭ ድንገት የፍቅረኛዋ ጉሮሮ ውስጥ ተቀረቀረ፡፡ ውኃ ብትሰጠው፣ ማጅራቱን ብትመታው ሊወርድለት አልቻለም፡፡ ኡኡ ብላ እንዳትጮህ ልጁ ማነው? እንዴትስ መጣ ? ለሚለው ጥያቄ የምትመልሰው የላትም፡፡ በዚህ መካከል ልጁ ትንፋሽ አጥሮት ሞተ፡፡

የልጁ የመውጫ ሰዓት ሲደርስ የጥበቃ ሠራተኛው መጣ፡፡ እንደቀድሞው ግን ልጁን ደብቆ ሊያስወጣው አይችልም፡፡ አሁን ያለው ሬሳው ነው፡፡ ‹እባክህን የምትችለውን ሁሉ አድርገህ ይህንን ሬሳ አውጣልኝ፤ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ አደርግልሃለው› አለቺው፡፡ የጥበቃ ሠራተኛውም ‹ምንም ችግር የለውም፤ የምፈልገው ግን ገንዘብ ወይም ልብስ አይደለም› አላት፡፡ እርሷም ‹ምንም ችግር የለም፡፡ ብቻ በቶሎ አውጣልኝ› ብላ ለመነችው፡፡ የጥበቃ ሠራተኛው ሬሳውን ቆሻሻ አስመስሎ ደብቆ  አወጣው፡፡ እርሷም እፎይ አለች፡፡
የጥበቃ ሠራተኛው ተመልሶ መጣና ቃል በገባችው መሠረት የሚፈልገውን ነገር እንድታደርግለት ጠየቃት፡፡ ‹ምን?› አለች ልዕልቲቱ፡፡ ‹ካንቺ ጋር መተኛት ነው የምፈልገው› አላት፡፡ ፀሐይ እንደበዛባት ቅል ክው አለች፡፡ ተናደደች፡፡ ‹ምን ደፋር ነህ ከልዕልት ጋር ለመተኛት የምታስብ፤ አሁን ከዚህ ጥፋ› አለቺው፡፡ እሺ ብሎ ወጣና የፍቅረኛዋን አስከሬን ይዞላት መጣ፡፡ ይኼኔ የምታደርገው ግራ ገባት፡፡ ያላት አማራጭ የሰውዬውን ፈቃድ ማሟላት ብቻ ሆነ፡፡ ተሸነፈች፡፡ በአንድ ቀንም ሦስት ነገሮችን አጣች፡፡ ፍቅረኛዋን፣ ክብሯንና የወደፊት ተስፋዋን፡፡ ፍቅረኛዋን በሞት፤ ክብሯንም በአገልጋይዋ እግር ሥር በመውደቅ፤ የወደፊቱንም ተስፋዋን ድንግልናዋን በማጣት፡፡ 
በዚህ ብቻ አላበቃችም፡፡ ያ የጥበቃ ሠራተኛ እየመጣ ‹አጋልጥሻለሁ› ይላታል፡፡ ያን ቀን ሬሳውን ይዞ የመጣበትን ጆንያም ያሳያታል፡፡ እርሷም ትፈራለች፡፡ በፍርሃትም የማትፈልገው ሰው እግር ሥር ትወድቃለች፡፡ ከእርሱም ጋር ትተኛለች፡፡ ይህ ግን ሊያዛልቃት አልቻለም፡፡ ባርነት ሰለቻት፡፡ ችግሮችን ለመጋፈጥ ካልፈለግህ ችግሮችን እያነገሥካቸው ትሄዳለህ› ይላሉ ኩርዶች፡፡ ችግርን ካታለልከው መልሶ ይይዝሃል፤ ከተጋፈጥከው ግን ጥሎህ ይሸሻል የሚል አባባልም አላቸው፡፡ 
ልዕልቲቱ አሁንም ችግሩን መፍታት ሳይሆን ማምለጥ ፈለገች፡፡ አንድ ሌሊት የጥበቃ ሠራተኛው ተደብቆ ወደእርሷ ሲመጣ ለአባቷ የምታዘጋጀውን የልዑሉን ወይን አሰናድታ ጠበቀቺው፡፡ በደስታ እየደጋገመ ጠጣ፡፡ ከእርሷም ጋር ከተኛ በኋላ እንደ ተሸነፈ ቦክሰኛ በድካም ተዘረረ፡፡ አርሷም እየጎተተች ወስዳ በልዑሉ መኝታ በር ላይ አጋደመችው፡፡ ሊነጋጋ ሲል ጠባቂዎቹ አዩት፡፡ ጠጋ ብለው ሲያሸቱት አፉ የወይን ጠጅ ይሸታል፡፡ የወይን ጠጁ ሽታ የልዑሉ ወይን መሆኑን ይመሰክራል፡፡ የልዑሉን ወይን ሰርቆ ጠጥቷል ብለው በአደባባይ ሰቅለው ገደሉት፡፡ ነገሩም በዚህ የተቋጨ መሰለ፡፡ ነገር ግን የዕብድ ቀን አይመሽም፡፡ ኩርዶች እንዲህ ይላሉ፡፡ የምትሠራው በር ምንጊዜም ልትሄድበት የምትችል መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ለአንድ ጊዜ መውጫ ብለህ በሩን ከሠራኸው ከበሩ በኋላ ወዴት እንደምትሄድ ግራ ይገባሃል፡፡ በሩን ከነ መንገዱ አስበው፡፡ መንገዱን ከነ መዳረሻው፤ መዳረሻውንም ከነመቆያው፤ መቆያውን ከነ መክረሚያው፡፡ 
የጥበቃው ሠራተኛ በአደባባይ ሲሰቀል፤ የወይኑ ጣዕም አፉ ላይ ቀርቶ ስለነበር እየደጋገመ ከንፈሩን ይልስ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ የጠጣው የወይን ጠጅ ጣዕም ነው ተብሎ ተወራ፡፡ ይህንን ወሬ የሰማ የሌላ ልዑል ልጅም ይህንን ወይን ያዘጋጀቺውን የልዑሉን ልጅ ለማግባት ፈለገ፡፡ እናም ወደ ልዕልቲቱ አባት ሽማግሌዎች ላከ፡፡
ይህ ዜና ለአባቷ የምሥራች ለልዕልቲቱ ግን መርዶ ነበር፡፡ ድንግልናዋን አጥታለች፡፡ በኩርድ ደግሞ ድንግል ያልሆነቺውን ልጅ እንኳን ልዑላን ተራዎቹ ሰዎች አያገቡም፡፡ እስካሁን ችግሩን ከመጋፈጥ እየሸሸች፣ ነገር ግን አንዱን ችግር በሌላ ችግር እያለፈች መጥታለች፡፡ አሁን የመጋፈጫው ሰዓት ደረሰ፡፡ ችግርን በመፍትሔ መፍታትና ችግርን በሌላ ችግር ማለፍ ይለያያሉ፡፡ ችግርን በችግር ካለፍከፈው ጊዜ እየገዛህ ነው፡፡ ችግርን በመፍትሔ ካለፍከው ደግሞ ልብ እየገዛህ ነው፡፡ ይላሉ ኩርዶች፡፡ 
የልዕልቲቱ አባት ጋብቻውን መቀበሉን ስትሰማ እንደተለመደው ልዕልቲቱ አንድ ዘዴ ቀየሰች፡፡ አንዱን ታማኝ አገልጋይዋን ጠራችውና አንድ እፍኝ ወርቅ ሰጥታ እንዲህ ስትል አዘዘችው ‹በመላዋ ኢራቅ ዙር፡፡ በመልክም፣ በቁመትም፣ በጠባይም እኔን የምትመስል ልጅ ፈልገህ ለደንገጡርነት አምጣልኝ›፡፡ ሰውዬውም ለወራት ያህል ከቦታ ወደ ቦታ ዞረ፡፡ በመጨረሻም አንዲት ልጅ አገኘ፡፡ ልዕልቲቱ ስታያት ቁርጥ እርሷን ትመስላለች፡፡ እንዲህ አለቻት ልጅቱን፡፡ አሁን አንቺ ልዕልት ሆነሻል አሉ፡፡ የልዑሉንም ልጅ ታገቢያለሽ፡፡ የጫጉላውንም ጊዜ አብረሽው ታሳልፊያለሽ፡፡ እኔም ያንቺ ደንገጡር ሆኜ አንቺንና ልዑሉን ለጊዜው እታዘዛለሁ፡፡ ልክ የጫጉላው ጊዜ እንዳለፈ ግን ትቀይሪኛለሽ፡፤ እንቺ ወደ ደንገጡርነትሽ እኔም ወደ እመቤትነቴ እመለሳለሁ፡፡ ለዚህ ውለታሽም ለጥሎሽ የሚመጣውን ሀብት ሁሉ ትወስጃለሽ› አለቻት፡፡ ልጂቱም በደስታ ተፍነከነከች፡፡ 
የሠርጉ ቀን ደረሰ፡፡ ደንገጡሯዋ የሙሽራ ልብስ ለበሰች፡፡ እመቤቲቱ ደግሞ የአገልጋይ ልብስ ለበሰች፡፡ ማንም ሊለያቸው የቻለ የለም፡፡ ልዑሉ መጣ፡፡ ሙሽራዋን ይዞ ሄደ፡፡ አገልጋይዋም ተከትላ ሄደች፡፡ በልዑሉ ቤት የነበረው ድግስ ሲያልቅ ልዑሉና ሙሽራዋ ወደ ጫጉላ ቤት ገቡ፡፡ አገልጋይዋም ከውጭ ቀረች፡፡ ታስበዋለች፡፡ ይህ ዕድል የእርሷ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አይደለም፡፡ አሁን እርሷ ነበረች እዚያ ውስጥ መሆን የነበረባት፤ ግን ችግርን ለማለፍ ብላ በፈጠረችው ችግር ምክንያት ውጭ ቆማለች፡፡ እዚህ ደረጃ ሳትደርስ ነገሮችን አስተካክላ በክብር ልትወጣ ትችል የነበረባቸውን ዕድሎች ታስታውሳለች፡፡ ዕድሎች ሁሉ አምልጠዋታል፡፡ ችግሮችን በሌላ ችግር በመተካት ዕድሎችን አምክናቸዋለች፡፡ ስለዚህም ክብሯን ለሌላዋ አሳልፋ ሰጠቻት፡፡ ሕዝቡ ጫጉላ ቤት ያለቺው እርሷ መስላቸዋለች፡፡ ግን አይደለችም፡፡ የተመረጠችው እርሷ፣ ወደ ሠገነት የወጣችው ሌላዋ፡፡ የተዳረችው እርሷ፣ ያገባችው ሌላዋ፡፡
የጫጉላዎቹ ቀናት አለፉ፡፡ ልጂቱ ግን ወደ አገልጋይነቷ ልትመለስ አልቻለችም፡፡ አንድ ቀን መታጠቢያ ቤት ውስጥ እመቤትና ደንገጡር ተገናኙ፡፡ ደንገጡሯም ‹አሁን በቃሽ ወደቦታሽ ተመለሽ፡፡ ለውለታሽ ያዘጋጀሁትን ስጦታሽን ውሰጅ; አለቻት፡፡ እመቤቲቱም ‹የዋሕ ነሽ፡፡ ላየው የማልችለውን አሳየሺኝ፤ ላገኘው የማልችለውን ሰጠሽኝ፤ ልደርስበት የማልችለው ቦታ አደረሽኝ፡፡ ያኔ እሺ ስልሽ ይህንን ሁሉ አላውቅም ነበር፡፡ አልጋው እንዲህ የሚመች መሆኑን አልቀመስኩም ነበር፡፡ ክብሩ እንዲህ የሚያጓጓ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ምቾቱ እንዲህ ልብ የሚለሰልብ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ላንቺ ከደንገጡርነት ወደ እመቤትነት መምጣት ቀላል ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ከእመቤትነት ወደ ደንገጡርነት መውረድ ከባድ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ነገር ከቀመስኩ በኋላ ትተውልኛለች ብለሽ ማሰብሽ ሞኝነትሽ ነው፡፡ አልጋ አንዲህ በቀላሉ የሚተው አይደለም፡፡ ሀብቱ ሁሉ የእኔ መሆኑን እያየሁ ያንቺ ስጦታ የሚያጓጓኝ ይመስልሻል› አለቻት፡፡ 
›እነሆ› ይላሉ ኩርዶች፡፡ እነሆ በዚህ የተነሣ አገልጋይቱ እመቤት፣ እመቤቲቱም አገልጋይ ሆነው ኖሩ፡፡ ተቀምጣ የሰቀለቺውን ቆማ ማውረድ አቅቷት፡፡ 
ኤድመንተን፣ ካናዳ

ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት

$
0
0

አዋላጇ ጠፍታ ልጁም በእግሩ መጥቶ
እናቲቱ ሞተች ልጅዬውም ሞቶ

የሚል የልቅሶ ግጥም አለ። ነፍሰ ጡር እናት ስትወልድ ልጁ በእግሩ ከመጣ አደጋ ነው ይባላል። ጎበዝ አዋላጅ አግኝታ ልጁ በአናቱ እንዲመጣ ልታግዛት ይገባል። ያ ካልሆነ ግን ባልተስተካከለ መንገድ የመጣውን ልጅ ለመውለድ የምታምጠው እናት፣ ለረዥም ጊዜ በማማጧ የተነሣ ደክማ ለሞት ትዳረጋለች። ልጇም የመሞት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። መውለድ ደስታ የሚሆነው ልጁ በሰላም ተወልዶ፣ ለእናቱ ጤናና ደስታ ካመጣ ነው። መውለድ ካልተስተካከለ ማርገዝ ብቻውን ድካም ነው። ለዚህ ነው ነፍሰ ጡሮች በሕክምና እርዳታ ሲታገዙ ቆይተው፣ በሕክምና እርዳታ እንዲወልዱ የሚመከረው።



ሀገር ለውጥን ልትወልድ የምትችለው የለውጥን ጽንስ በጤናማ መልኩ አርግዛ በጤናማ መልኩ እንድትወልድ የሚረዷትን ሐኪሞች ካገኘች ነው። ጽንሱ ጤናማ መሆኑን በየጊዜው የሚከታተሉ፤ ችግር ሲፈጠር ወዲያው መፍትሔ የሚሰጡ። ስትወልድም ልጁም እናቲቱም ጤንነታቸው በተጠበቀበት መንገድ እንድትወልድ የሚረዱ አዋላጅ ሐኪሞች ያስፈልጓታል። ይህ ሲጠፋ ልጁም እናቲቱም ለሞት ይዳረጋሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ለውጥን ፀንሳ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ የማታገኘው ጎበዝ አዋላጅ ሐኪም ነው። በዚህ ምክንያትም ብዙ ጊዜ ልጇ ሞቶባታል። ያውም በእርሷም ላይ ከባድ አደጋ አድርሶ። ማኅፀኗን ጎድቷት ስለሚሄድ፣ ሌላ ልጅ ለመጸነስ ዘመናትን እንዲፈጅባት አድርጎ።

የቅርቡ ታሪካችንን እንኳን ብንመለከተው፣የልጅ ኢያሱን ዘመን ፀንሳ ነበር። ነገር ግን ካለፉት ዘመናት በተለየ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ሂደት ባለቤት እንዲሆን ከዘመኑ በቀደመ ሐሳብ የተነሣውን ወጣቱ ንጉሥ ሐሳቡን የሚያዋልድለትና ፅንሱ በእግሩ መጥቶ እናቱንም ራሱንም እንዳይገድል የሚያደርግ ሐኪም አጥቶ፣ ሀገሪቱ ያንን ዕድል አመከነችው። የተገኙት አዋላጆች ሳይሆኑ አምካኞች ነበሩ። ልክ ፈርዖን በግብጽ፣እሥራኤላውያን ላይ አሠማርቷቸው እንደነበሩት የአዋላጅ አምካኞች።

በ1953 ዓ.ም ኢትዮጵያ እንደገና ሌላ የለውጥ ልጅ ፀንሳ ነበር። ነባሩ ንጉሣዊ ሥርዓት ከመሠረቱ ሳይናጋ ነገር ግን ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥርዓታዊ ለውጥ ለመውለድ ፀንሳ ነበር። አዋላጅ ግን አላገኘችም። ያንን ሐሳብ በሚገባ ፀንሳ በሚገባ እንድትወልድ የሚያደርጉ አዋላጆች ብታገኝ ኖሮ፣የጥንቱን ከዘመኑ ያጣጣመ ሥርዓት ገንብታ ለመጓዝ ትችል ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፤ ጨነገፈ።

በ1966 ዓ.ም ሌላ የለውጥ ልጅ ፀነሰች። ሀገሪቱን ወደተሻለ ሥርዓት ሊወስድ የሚችል ተስፋ የሰነቀ ልጅ። ምን ዋጋ አለው። አዋላጆች አላገኘችም። ልጁን ጤናማ ሆኖ እንዲወለድ ከማገዝ ይልቅ አዋላጆቹ እርስ በርሳቸው ሲጨፋጨፉና ሲቧቀሱ፣ ልጁ ‹ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት› ብለው በተነሡ የወታደር አጨናጋፊዎች እጅ ወደቀ። አንዲት የገጠር ሴት ለመውለድ ደርሳ አዋላጅ ጠራች። የቀን ጎደሎ ሆኖባት የማይችል ሰው እጅ ወደቀችና እርሷም ልጇም ሞቱ። አልቃሽ፡-

እንዲህ ያል ክፉ ቀን ክፉ ሰው ላይ ጥሏት
እንኳን ልጅ ልታገኝ እርሷንም ገደሏት፤

ብላ ገጠመች ይባላል። ኢትዮጵያም በ66 እንዲህ ነው የሆነቺው። ሐኪሞች ልጆቿ፤ የራስዋን ልጅ ማዋለድና ማሳደግ ሲገባቸው፣ የማደጎ ልጅ ከሶቪየት አምጥተው ልጅሽ ይሄ ነው አሏት። በማኅፀንዋ የተፀነሰውን የራስዋን ልጅ ገድለው የሰው ልጅ አሳቀፏት። የአዋላጆቹ ጠብም ልጇን እንዴት እናዋልዳት? መሆኑ ቀርቶ፣የትኛውን ልጅ ትታቀፍ? የሚለው ላይ ሆነ። እንኳን አዲስ ልጅ ልትወልድ እርሷም በወሊድ ምክንያት በተከሠተ ሕመም ለዘመናት ትሰቃይ ጀመር።

ያ ዘመን አልፎ 1983 ዓ.ም መጣ። ሁሉንም ያሳተፈ፤ የኅብረተሰብም የሐሳብም ብዝኃነትን የተቀበለ፤ ሀገሪቱ ስትመኘው የኖረቺውን ልጅ ልትወልድ የምትችልበት ዕድል ገጠማት። አሁንም ግን አዋላጆች ጠፉ። ያንን ለውጥ በፖለቲካ ብስለት፣ በዕውቀትና በትዕግሥት፣ በአመራርና በጥበብ አዋልደው፣ሀገሬ ዴሞክራሲና ዕድገትን ከነ ቃጭሉ ዱብ እንድታደርግ የሚያስችሉ አዋላጆች ጠፉ። ሁሉም የራሱን ብቻ ሲሰማና ‹ልጁ እንዲፀነስ የታገልኩት እኔ ነኝና እኔ ብቻ ልወስን› ሲል ሀገሬ ልጇን አጣችው። እርሷ ለመፅነስ እንጂ ለመውለድ ሳትታደል ቀረች።

ከሕዝቡ አብራክ ተከፍሎ በኢትዮጵያ ማኅፀን የተፀነሰውን ያንኑ ልጇን ተባብሮ ከማዋለድና እርሱኑ ተከባክቦ ከማሳደግ ይልቅ አሁንም ኮሚኒዝሙን፣ ማኦኢዝሙን፣ ዴሞክራሲውን፣ ቀያይጠንን እንደ አሻንጉሊት ሰፍተን፣ ‹ልጅሽ ይሄ ነው› አልናት። የብሔረሰቦችን ጥያቄ ልንግባባበትና ሀገር ልንመሠርትበት በምንችለው መንገድ መፍትሔውን መውለድ ሲገባን፣ ዘወትር የሚያጣላንንና የሚያበጣብጠንን የማደጎ ልጅ አመጣን። ከራሳችን አብራክ በራሳችን ማኅፀን ለኛ የሚሆን የፌዴራሊዝም ልጅ ልንወልድ ሲገባን የማደጎ ልጅ አመጣን። ይኼው አሁን በሂደት ልጁ የኛ ልጅ አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያ የወለደችው ልጅ አለመሆኑን እየነገረን ነው። ከኛ ፍላጎት፣ ባህል፣ አስተሳሰብና ታሪክ ጋር መኖር አቅቶታል። የገዛ ልጃችን ዕዳ ነው የሆነብን። ሀገሬ ልጅ አልወጣላትም።

በ1997 ዓ.ም ሀገሬ ሌላ ልጅ ፀንሳ ነበር። ዴሞክራሲን። የአስተሳሰብ ብዙኅነትን ልትወልድ ነበር። እኛም ትወልዳለች ብለን የገንፎውንና የአጥሚቱን እህል አዘጋጅተን ነበር። ግን ምን ያደርጋል፤ ሐኪም አላገኘችም። ‹እኔ ብቻ› የሚል ሐኪም ገጥሟት፤ የዛሬውን እንጂ የነገውን የማያይ ስግብግብ አዋላጅ ገጥሟት፤ ምንጊዜም በሆስፒታሉ ውስጥ ‹ብቸኛው ስፔሻሊስት ሐኪም› እየተባለ መኖር የሚወድ ራስ ወዳድ ሐኪም ገጥሟት፤ ጊዜያዊ ችግሮችን ለዘላቂው ጥቅም ሲል መታገሥ የማይችል ሐኪም ገጥሟት፤ ወይ ‹ሁሉን ማግኘት አለያም ሁሉን ማጣት› የሚባል የማዋለጃ መሣሪያ የያዘ ሐኪም ገጥሟት ሀገሬ ልጇ ሞተባት።

እርሷም ትፀንሳለች እኛም እንፈጫለን
ለልቅሶ ነው እንጂ ለእልልታ አልታደልን፤

አለ አሉ፤ ኀዘን የጎዳው ባል። ሚስቱ በፀነሰች ቁጥር ለአራሷ የሚሆን እህል በቤቱ ይፈጫል። ነገር ግን ወለደች ተብሎ እልል ሳይባል፣ ሞተባት ተብሎ ይለቀሳል። ይሄ ነበር ባልን እንዲህ እንዲያንጎራጉር ያደረገው። ሀገሬም እንዲህ ነው የሆነቺው።

አሁንም ሀገሬ ፀንሳለች። እኛም ሊያግባባንና ሊያስማማን የሚችል ሥርዓተ መንግሥት፤ የብዙኃኑን ውክልና የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሂደት፤ የትብብር መነሻ የሚሆን፣ ከአጥር ይልቅ ድልድይ የሚገነባ ፌዴራሊዝም፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብርና የሚጠብቅ የፖለቲካ ምኅዳር ትወልዳለች ብለን ተስፋ እያደረግን ነው። ይህ እንዲሆን ግን ማዋለድ ያስፈልጋል። ኃይልና ጉልበትን፣ ዘረኝነትና ጽንፈኝነትን፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልና እኔ ብቻ ዐውቅላችኋለሁን፣ እኔን ምን አገባኝና እኔ የለሁበትምን፣ አግላይነትንና ጠቅላይነትን፣ ጥገናዊነትንና ጊዜያዊነትን ትተን ሀገሬ ለሁላችንም የሚሆን፣ ሁላችንም እልል ብለን የምንቀበለው፤ ሁላችንም የአራስ ጥሪ የምናመጣለት፣ ሁላችንም በመወለዱ ገንፎ የምንበላበት፣ ሁላችንም ልደቱን የምናከብርለት፣ ከሩቅ ያሉት እንደ ሰብአ ሰገል ገሥግሠው፣ ከቅርብ ያሉት እንደ እረኞቹ ነቅተው ሄደው የሚያመሰግኑት ልጅ እንዲወለድልን ማዋለድ አለብን። ምሁራኑ፣ የፖለቲካው ልሂቃን፣ ደጋፊዎች፣ ተቃዋሚዎች፣ የእምነት መሪዎች፣ የሚዲያ ተዋንያን፣ ነጋድያን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወታደራዊ አለቆች፤ ሀገራችን የፀነሰቺውን ልጅ በሰላም እንድትገላገል እንርዳት። አንዱ እግሩን፣ አንዱ እጁን፣ አንዱ ጆሮውን፣ አንዱ ጭንቅላቱን እየሳበ፣ ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን የየራሱን ልጅ ለማዋለድ ቢጥር ልጁ ይሞታል እንጂ ልጅ አይሆንም። ሀገሬም ፀንሳ በወለደች ቁጥር እየተጎዳች፣ እየደከመች ትሄዳለች።

እናት በተደጋጋሚ ልጆች ሞተውባት በስተመጨረሻ ተወልዶ የሚያድግላትን ልጅ ‹ማስረሻ› ትለዋለች። ያለፈውን መከራና ስቃይ ሁሉ የሚያስረሳ ማለቷ ነው። ሀገሬ ማስረሻ የሆነ ልጅ ትፈልጋለች። እልህና ኃይለኝነት አልጠቀመንም። ዘረኝነትና መከፋፈል አልፈየደልንም፣ ጥላቻና ሽኩቻ አላሳደገንም፤ ግዴለሽነትና ራስ ወዳድነት አላራመደንም። አሁን ሰከን ብሎ፤ ከስሜታዊነትም ወጥቶ፣ሀገሬ የፀነሰቺውን ልጅ እንዴት በሰላም ልትገላገል እንደምትችል መነጋገር፣ መመካከርና መተባበር ያስፈልጋል። ኑ! ሀገሬን እናዋልዳት፤ ኑ፡፡ እስከ መቼ ልጅ ይሙትባት?

ካልጋሪ፣ ካናዳ

ከአሸናፊዎች መዳፍ -ወደ- የተሸናፊዎች ወገብ

$
0
0
‹ሰላም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ አትገኝም› የሚል ወርቃማ አባባል አላቸው የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች (First Nations)፡፡ አደን ልዩ ችሎታቸው የነበረውና በዚህች ሀገር ከሺ ዓመታት በፊት ሠፍረው መኖር የጀመሩት እነዚህ ሕዝቦች አያሌ የእርስ በርስ ጦርነቶችንና ችግሮችን ለመፍታት የቻሉት በዚህ ምክንያት እንደነበረ ይነገራል፡፡
ሁለት ጎሳዎች በአደንና በእርሻ ቦታ ወይም በድንበር ምክንያት በተፈጠረ ችግር ወደ ጦርነት ይገባሉ፡፡ የእነዚህ ጥንታውያን ሕዝቦች ሽማግሌዎች ግን ጦርነቱ በአንደኛው አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አይፈቅዱም፡፡ ጦርነቱ ሲደረግ የተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው የሚታገሡት፡፡ የዚህን ምክንያቱን ሲያስረዱ ደግሞ ‹ሁለቱም ወገኖች የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ መቅመስ አለባቸው› ይላሉ፡፡ የችግር መፍቻው መንገዳቸው ወደ ባሰ ችግር እየወሰዳቸው መሆኑን ከምክርና ከትምህርት ይልቅ በተግባር እንዲያዩት ጊዜ ይሰጧቸዋል፡፡
በኋላ ግን በመካከል ይገባሉ፡፡ ‹ጦርነቱ በአንደኛው ወገን አሸናፊነት መጠናቀቅ የለበትም› የሚል እምነት አላቸው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ቀን ጣላቸው፤ ችግር ለያያቸው፤ መንገድ አጣላቸው እንጂ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ የእነዚህ ወንድማማቾች ትግል በአንደኛው አሸናፊነት ከተጠናቀቀ ሰላም አይገኝም፡፡ አሸናፊው ጨቋኝ፣ በቀለኛ፣ ጉልበተኛና ዘራፊ ሆኖ ይቀራል፡፡ ተሸናፊው ደግሞ ቂመኛ፣ ቀን ጠባቂ፣ በጥላቻ የተሞላና ባዕድ ሆኖ ይኖራል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ ቦታ መቀያየራቸው አይቀርም፡፡ የሕዝቡም ችግር ይቀጥላል፡፡ 

ለካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች መፍትሔው አንድ አሸናፊ መፍጠር ሳይሆን ሁለት ተሸናፊ ማግኘት ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ጦራቸውን መሬት ተክለው፤ እግራቸውን አጣጥፈው፣ ምንጣፍም ላይ ተቀምጠው መነጋገርና መደራደር አለባቸው፡፡ እስኪስማሙ ድረስ መነጋገር፤ እስኪግባቡ ድረስ መደራደር፡፡ ሲያቅታቸው በሽማግሌዎቹ እየታገዙ ወደ አንድ የመግባቢያ ሐሳብ መምጣት፡፡ ያን ጊዜ ሁለቱም ወገኖች ከሁለቱም ለተሻለ ሉዐላዊ ሐሳብ ተሸናፊ ሆነው ይወጣሉ፡፡ ለዚህ ነው ‹ሰላም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ አትወጣም› የሚሉት፡፡ ‹የተሸናፊዎች ወገብ› ሲሉ በባሕላቸው ስምምነቱ የሚፈጠረው ከወገብ ጎንበስ ብሎ በትኅትና የመጨረሻውን ሐሳብ በመቀበል ስለሆነ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም ከተሸናፊዎች ወገብ እንጂ ከአሸናፊዎች መዳፍ መምጣት አይችልም፡፡ ሁሉም ወገን ለዚህች ሀገር የተሻለውን ሐሳብ ለማምጣትና በዚያም ለመመራት ወገቡን መስበር አለበት እንጂ የእርሱን ሐሳብ በሌሎች ላይ በአሸናፊነት ጭኖ ማለፍ የለበትም፡፡ ካለፈው ታሪካችን ይህን መማር አያቅተንም፡፡ የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች እንዳሉት በኛም ሀገር የአንድ ወገን አሸናፊነት አሸናፊውን ጨቋኝ፣ በቀለኛ፣ ጉልበተኛና ዘራፊ ሆኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ ተሸናፊውን ደግሞ ቂመኛ፣ ቀን ጠባቂ፣ በጥላቻ የተሞላና ባዕድ ሆኖ በየዘመናቱ የራሱን ጥያቄና የራሱን የነጻነት ትግል እንዲጀምር በር ከፍቶለታል፡፡ ምጣድ ላይ ጢቢኛ ተጋግሮ ላይኛው የዳቦው ክፍል ታችኛውን በእሳት በመለብለቡ ሲስቅበት ‹የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ስትገለበጥ ትቀምሰዋለህ› አለው ይባላል፡፡
ተጋድሏችንና ጥረታችን እገሌን አስወግደን፣ በእገሌ መቃብር ላይ ሐውልት ለመሥራት፤ አንዱን በሌላኛው ለመተካት፤ ከአንደኛው አገዛዝ ወደሌላኛው ለመሸጋገር ከሆነ በላሸቀ ጎማ በዳገት ጭቃ ላይ እንደመንዳት ይቆጠራል፡፡ ጎማው በተሽከረከረ ቁጥር ጭቃው እያንዳለጠው መኪናውን ወደኋላ እንጂ ወደፊት አይወስደውም፡፡ አሁንም ይቅደምና ይውደም የትግላችን መፈክር ከሆኑ ያለፉት ዘመናት ትግሎቻችን ካመጡልን ለውጥ የተሻለ አናመጣም፡፡ አሁንም ‹እኛ› እና ‹እናንተ› እየተባባልን አንዱ ለሌላው መብት ሰጭ፣ ዋስትና ሰጭ፣ ምሕረት ሰጭ ሆኖ ከቀረበ ሥጋት እንጂ ሰላምን ማምጣት አይቻልም፡፡
ጉዞው አንድ አሸናፊ ወገንን ከፈጠረ ጊዜ የሚያፈነዳውን ፈንጂ የመቅበር ሥነ ሥርዓት ይሆናል፡፡ ጉዞው አሸናፊ ሐሳብን ከፈጠረ ግን የፈንጂ ማምከኛ እንደመሥራት ይቆጠራል፡፡ የምንጋደለው ሁላችንም ወደ ውይይቱና ድርድሩ አዳራሽ ለመግባት እንድንችል፤ የሁላችንም ሐሳብ የሚፋጭበትና የተሻለው ሐሳብ አሸናፊ የሚሆንበትን ሥርዓት ለመዘርጋት እንድንበቃ፤ ከጭንቅላታቸው ይልቅ በጡንቻቸው፣ ከሐሳባቸው ይልቅ በመሣሪያቸው የሚተማመኑት ወገኖች ተሸንፈው ወደ ተሸናፊዎች መድረክ እንዲመጡ ለማድረግ ከሆነ ትግሉ ፈዋሽ ነው፡፡
በአፍሪካችን ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪው ምዕራፍ በጦርነት ያሸነፉ ኃይሎች የአሸናፊነት ልምድ ብቻ ስለሚኖራቸው ሰላም የምትፈልገውን የተሸናፊነት ባሕርይ ለመያዝ አለመቻላቸው ነው፡፡ በናይጄርያ የሚኖሩ ዮሩባዎች ‹ከበሮን እንዲመታ አድርጎ መሥራትና ከበሮን ለኢሻይ ኦ ሉዋህ መምታት ይለያያሉ› የሚል አባባል አላቸው፡፡ [ኢ ሻ ኦሉዋህ - ‹የእግዚአብሔር ሥራ ሳይፈጸም አይቀርም› የሚል የዩሩባ ባሕላዊ ዘፈን ነው] ነጻነትን ማምጣትና በነጻነት የምትኖርን ሀገር መገንባት የተለያዩ መንገዶችንና ችሎታዎችን ይጠይቃሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ተዋጊዎች ከሰሜን ሱዳን ነጻ የሆነች ሀገር በዘመናት ትግል ፈጠሩ፡፡ በሰላምና በነጻነት የምትጓዝ ሀገር መፍጠር ግን አቃታቸው፡፡ ሰላም ከአሸናፊዎች መዳፍ ልትወጣ አትችልምና፡፡ ከአሸናፊዎች መዳፍ የምትወጣ ሰላም ሰላማዊነቷ ለአሸናፊዎቹ ብቻ ነው፡፡ ተሸናፊዎቹ ምንጊዜም በጦርነት ሥነ ልቡና ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡    
የምንታገለው ለመሸነፍ መሆን አለበት፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ የመጨረሻዎቹ ዘመናት የአፓርታይድ መሪዎች ለድርድር ሲጋብዙት ፈቃደኛ በመሆኑ ከሌሎች የኤ ኤን ሲ መሪዎች ክርክር ገጥሞት ነበር፡፡ የአፓርታይድን ፍጻሜ ‹በፈረስ አንገት፣ በጦር አንደበት› ማምጣት ስንችልና ሲገባን ለምን? የሚል ሙግት፡፡ የማንዴላ መልስ የተለየ ነበር፡፡ ‹የታገልነው በሁላችንም ፍላጎት ላይና በሁላችንም ድርድር የምትገነባ ደቡብ አፍሪካን ለማምጣት እንጂ የአንድ ወገን የነበረችውን ሀገር የሌላ ወገን ለማድረግ አይደለም፡፡ የሁላችንም የምትሆነውን ሀገር ሁላችንም እንድንፈጥራት ለማድረግ ነው› ነበር ያለው፡፡
ትግሉ ተሸናፊዎች ወደሚገቡበት አዳራሽ ለመግባት ማንም በማንም ላይ በሩን እንዳይዘጋ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ወገቡን እንጂ መዳፉን ይዞ እንዳይመጣ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ መዳፍ የጨበጡትን አላቅቆ ወገብ እንዲይዙ ለማስቻል መሆን አለበት፡፡ ዮሐንስ ሐፂር ‹አንተ ስትገባ እርሱ ወጣ› እንዳለው አንዱ ሲገባ የሚወጣ ሌላ መኖር የለበትም፡፡ ሁሉም በገቢ ደረሰኝ የሚመዘገብበትን አካውንት ነው መክፈት ያለብን፡፡
የካናዳ ጥንታውያን ሕዝቦች ‹የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ መቅመስ አለባቸው› ካሉት በላይ በአንድ ወገን አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ትግልና አብዮት የሚያስከትለውን ጣጣ በሚገባ ቀምሰነዋል፡፡ ዩሩባዎች ‹የፀሐይ መጥለቂያ የጨረቃ መውጫ ነው› እንደሚሉት የአንዱ ወገን ትግል መጨረሻ ለሌላው ወገን የትግል መጀመሪያ እየሆነ ስንገላበጥ ኖረናል፡፡ የሺ ዓመታት ታሪክ አለን የምንል ሕዝቦች ስንት ጊዜ የነጻነት ቀን፣ ስንት ጊዜ የሕዝብ መዝሙር፣ ስንት ጊዜ የባንዴራ ዓርማ፣ ስንት ጊዜ ሕገ መንግሥት፣ ስንት ጊዜ የየአካባቢዎቻችንን ስያሜ እንደቀያየርን እናውቀዋለን፡፡
አንድ ጊዜ አንዱ ባላባት በሌላው ባላባት ርስት ይሾምና ይሄዳል፡፡የተሾመው ባላባት ግብር አውጥቶ ሕዝብ ይጋብዛል፡፡  በዚያ ግብር ላይ የተሿሚው ወገኖች ‹ዓይናማው ገዳየ› እያሉ ሲዘፍኑ የተሸናፊው ወገኖች ‹አሃው ገዳይ› በማለት ፋንታ ‹አለን ጉዳይ› ይሉ ነበር አሉ፡፡ ልባቸው እንደሸፈተ ሲናገሩ፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዞም ‹ዓይናማው ገዳይ› ብሎ አንዱ ሲዘፍን ሌላው ‹አለን ጉዳይ› የማይልበትን ሥርዓት ለመዘርጋት መሆን አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የአሸናፊነት መዳፋችንን አላቅቀን የተሸናፊነትን ወገብ ይዘን ወደ ውይይቱ አዳራሽ በነጻነት ከገባን ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ከአሸናፊዎች መዳፍ ሳይሆን ከተሸናፊዎች ወገብ መገኘት አለባት፡፡
አርኅው ኆኃተ መኳንንተ፡፡
 ቫንኮቨር፣ ካናዳ













ኩሬአውያን

$
0
0
ትውፊታውያን የሀገራችን ሰዓሊዎች የማያመዛዝንን ሰው ሲስሉ አንድ ዓይና አድርገው ይስሉት ነበር፡፡ ሰፋ አድርጎ የማያይ፤ እውነትን በከፊል ብቻ የሚቀበላት፤ ከሚያውቀው ውጭ ሌላ ነገር ያለ የማይመስለው ነው ማለታቸው ነው፡፡ ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል› የሚል አባባልም አለ፡፡ ዕውቀትህን፣ አመለካከትህንና አካሄድህን ባሻሻልክ ቁጥር ያላየኸውን ታያለህ፣ ያልሰማኸውን ትሰማለህ፤ ያልተገለጠልህ ይገለጥልሃል፤ የረቀቀው ይጨበጥልሃል፤ እውነት ነው ያልከው ውሸት፣ ውሸት ነው ያልከውም እውነት ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ ሲሉ ነው፡፡


ቀደምት ሊቃውንት ሁለት ዓይን የተሰጠን በአንዱ የራሳችን በሌላው የሌላውን ለማየት ነው፡፡ ሁለት ጆሮ የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን በሌላው የሌላውን ለመስማት ነው፡፡ ሁለት እጅ የተሰጠን በአንዱ ለመስጠት በሌላው ለመቀበል ነው፡፡ ሁለት እግር የተሰጠን በአንዱ ወደራሳችን በሌላው ወደ ሌላው ለመሄድ ነው ይሉ ነበር፡፡  

ሞንጎልያውያንም ከዚህ ጋር የሚሄድ ብሂል አላቸው፡፡ 

በአንዲት የሞንጎልያ ትንሽ መንደር ውስጥ በምትገኝ ኩሬ አንዲት ዓይን ብቻ ያለቺው ዕንቁራሪት ይኖር ነበር፡፡ ለእርሱ ዓለም ማለት ያቺ ኩሬ፣ ንጉሥም ማለት እርሱ ነው፡፡ ከእርሱ ኩሬ የተሻለ ቦታ፣ ከእርሱም የበለጠ ዕድለኛ የለም፡፡ የሚመኘው ነገር ቢኖር እርሱ ያገኘውን ይህንን ታላቅ ነገር የሚካፈለው ጓደኛ እንዲያገኝ ብቻ ነበር፡፡

አንድ ቀን በአካባቢው ከባድ ዝናም ጣለ፡፡ ምድሪቱንም የሚገለባብጣት መሰለ፡፡ ዕንቁራሪቱ በዚያች ለእርሱ ምርጥ በሆነችው ኩሬ ውስጥ በመሆኑ ምንም ነገር አይመጣብኝም ብሎ አመነ፡፡ ዝናቡ ግን አካባቢውን ደበላልቆ ከኩሬው ማዶ የሚገኘውንና ዕንቁራሪቱ መኖሩን የማያውቀውን ኡቩስ ኑር የተባለውን ጨዋማ ባሕር እንዲሞላ አደረገው፡፡ ባሕሩ ሲሞላ በውስጡ የነበሩትን እንስሳት ተፋቸው፡፡ አንዱ የባሕር ዔሊም በጎርፉ ተወስዶ የማያውቀው ቦታ ወደቀ፡፡

ዔሊው የኡቩስ ኑር ባሕርን ሊያየው አልቻለም፡፡ የት ቦታ እንዳለም አላወቀም፡፡ ወደየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበትም ግራ ገባው፡፡ ነገር ግን በቆሙበት ቦታ ከመሞት እየሄዱ መሞት ይሻላል ብሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ ቢሄድ፣ ቢሄድ፣ ቢሄድ መንገዱ ሊያልቅለት ባሕሩንም ሊያገኘው አልቻለም፡፡እንዲያውም እየደከመውና እየራበው መጣ፡፡ ሙቀቱንም መቋቋም አልቻለም፡፡ ወደ ኡቩስ ኑር ባሕር ሳልደርስ ልሞት እችላለሁ ብሎ ሠጋ፡፡ 

ወደ ባሕሩ በቀላሉ ሊደርስ እንደማይችል የተረዳው ዔሊ ነፍሱን ሊያድንለት የሚችል አንዳች ውኃ እየፈለገ ሳለ የዕንቁራሪቱን ኩሬ ተመለከተ፡፡ በዔሊ ፍጥነት ተንከላውሶ እዚያ ኩሬ ውስጥ ተወርውሮ ዘፍ አለ፡፡ ዔሊው ኩሬው ውስጥ ዘፍ ሲል የኩሬው ውኃ ከጥፋት ውኃ ባልተናነሰ ተናወጠ፡፡ ዕንቁራሪቱም ሰምቶት የማያውቀውን በመስማቱና አይቶት የማያውቀውን በማየቱ በድንጋጤ ልቡ ቀጥ አለች፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሲረጋጋ አንዳች የሚያህል ፍጡር በኩሬው ውስጥ ሲንከላወስ ተመለከተ፡፡

‹ለመሆኑ ማነህ? ከየትስ መጣህ? እዚህስ ምን ታደርጋለህ?› የጥያቄ መዓት አወረደበት፡፡ ዔሊው ጥሙን የሚያስታግሥለትን ውኃ ከተጋተ በኋላ ‹እኔ ዔሊ ነኝ፡፡ የመጣሁትም ከኡቩስ ኑር ባሕር ነው፡፡ እዚያ በተከሠተ ጎርፍ ከባሕሩ ወጥቼ ጠፋሁ፡፡ ወደ ባሕሩ እመለሳለሁ ብዬ ስጓዝ በውኃ ጥም ልሞት ደረስኩ፡፡ ፈጣሪ ይመስገን እዚህ ኩሬ ውስጥ ጣለኝ› አለው፡፡

‹ታድያ አሁን ምን እያሰብክ ነው?› አለው ዕንቁራሪቱ፡፡ ‹እኔ ወደ ባሕሩ መመለስ ነበር የምፈልገው፡፡ ነገር ግን መንገዱን አላውቀውም፡፡ በመካከልም በውኃ ጥም እንዳልሞት ፈራሁ፡፡ እናም ካላስቸገርኩህ በጋው እስኪያልፍ እዚህ አንተ ጋ ብከርም ምን ይመስልሃል?› አለው፡፡ ለብዙ ዘመናት ብቻውን የኖረው ዕንቁራሪት ጓደኛ ስላገኘ ደስ ብሎት ፈነጠዘ፡፡ ይህን እርሱ በኩሬው ውስጥ ያገኘውን ልዩ ደስታና ርካታ የሚያካፍለው ጓደኛ አገኘ፡፡

ዔሊው የበጋውን ወቅት የሚያሳልፍበት ቦታ በማግኘቱ እፎይ ያለ ቢመስለውም ዕንቁራሪቱ ግን በጥያቄዎች ያጣድፈው ነበር፡፡ ከኩሬው ውጭ ያለውን ዓለም የማያውቀው፤ በዓለም የመጨረሻው፣ ትልቁና ምቹው ቦታ ኩሬው የሚመስለው ዕንቁራሪት የጥያቄ ናዳ አወረደበት፡፡ ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር እንደዚህ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዔሊውም ዕንቁራሪቱን ላለማስከፋት ብሎ ‹ያንተ ኩሬ ውብና ምቹ ነው› አለው፡፡ ዕንቁራሪቱም በዚህ ተደሰተና ‹ለመሆኑ ያንተ ባሕር ከእኔ ኩሬ ይበልጣል› አለው፡፡ ዔሊውም ‹የኡቩስ ኑርን ባሕር ከዚህ ትንሽ ኩሬ ጋር ማነጻጻር የማይታሰብ ነው፡፡ ወርድና ቁመቱን ማንም ሊለካው አይችልም፤ አጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ምቹ ነው፡፡ አያሌ የባሕር እንስሳት ይገኙበታል› አለና መለሰለት፡፡
 
ዕንቁራሪቱ ደነገጠ፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የገባው እጅግ ውሸታም ዔሊ ነው ብሎ አመነ፡፡ ከዚህ ኩሬ የበለጠ ነገር በዓለም ላይ ሊገኝ አይችልም፡፡ ዕንቁራሪቱ በአንድ ዓይኑ ሲያያት የእርሱ ኩሬ ለእርሱ እጅግ ሰፊ፣ ማንም ሊደርስባት የማይቻላት ናት፡፡ ለመሆኑ በዓለም ላይ ከዚህ የሚበልጥ ምን ምቹ ቦታ ይገኛል? ብሎ አሰበና ‹የኡቩስ ኑር ባሕር የሚባል ነገር የለም፡፤ ቢኖርም ከዚህ ኩሬ ፈጽሞ ሊበልጥ አይችልም፡፡ አንተ ውሸታም ነህ፡፡ ሆን ብለህ እኔን ለማስደነቅና ከዚህ እንድወጣ ለማድረግ ነው እንጂ ከዚህ የሚበልጥ ባሕር ፈጽሞ የለም፡፡ በዓለም ላይ ያለው ብቸኛው፣ ታላቁና ምቹው ውኃ ይሄ ኩሬ ነው› አለው፡፡ 

ዔሊውም ‹ወዳጄ ሞኝ አትሁን፡፡ የማታውቀውን ነገር ሁሉ የለም አትበል፡፡ አንተ በአንድ ዓይንህ ስለምታያት ይቺ ኩሬ ትልቅ ትመስልሃለች እንጂ እንኳን ከዚህ ኩሬ ከኡቩስ ኑር ባሕር የሚበልጡም አሉ፡፡ እኔ የያዝኩት ብቻ የመጨረሻው ነው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ዕውቀቴ የመጨረሻው ነው ብሎ እንደሚያስብ ፍጡር የሚጎዳ የለም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዕንቁራሪቱ ክፉኛ ተቆጣ ‹ሞኝ አልከኝ፡፡ አንተ ከሌላ ዓለም የመጣህ ፍጡር ነህ፡፡ ከዚህ ኩሬ የሚበልጥና የተሻለ ነገር አለ ብሎ የሚለኝ ለእኔ የመጨረሻው ውሸታም ነው፡፡ ይህን ኩሬ እስካሁን እኔ ዋኝቼ አልጨረስኩትም› እያለ አመናጨቀው፡፡

ዔሊው ይህንን ንግግር ለማመን አልቻለም፡፡ የዕንቁራሪቱን ደኅነኛ ዓይን እያየ ‹አንተ ይህቺን ኩሬ የዓለም መጨረሻ አድርገህ ማየትህ አይገርመኝም፡፡ ያለህ አንድ ዓይን ብቻ ስለሆነ፡፡ የሚገርመው በሁለት ዓይኑ የሚያየውን ሁሉ መቃወምህ ነው፡፡ ሁላችንም በአንተ አንድ ዓይን ልናይ አንችልም፡፡ ላንተ ያልታየህ ሁሉ የለም፤ አንተ ያልደረስክበት ሁሉ አልተፈጠረም፤ አንተ ያልኖርክበት ሁሉ ምቹ አይደለም ብለህ ታስባለህ፡፡ ዓለምን በልክህ ቀደህ ሰፍተሃታል፡፡ ሁላችንም ደግሞ ባንተ ልክ እንድናሰፋት ታስባለህ፡፡ ይህ የመጨረሻው ሞኝነት ነው፡፡ እኔ ብቻ እና የኔ ብቻ ትክክል ነው ብሎ ማሰብ ነው ከዚህ ኩሬ እንዳትወጣ ያደረገህ፡፡ ሁሉንም ነገር በኩሬው ልክ ታስበዋለህ፡፡ በእውነትም አንተ የመጨረሻው ሞኝ ነህ፡፡ 

ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላውና ሌላውንም ለመስማት ትፈልግ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የሚያንስም፣ ካንተ የሚስተካከልም፣ ካንተ የሚበልጥም መኖሩን አምነህ ትቀበል ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ስለ ሌላው ዐውቀህ ኅሊናህን ታሰፋው ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ካንተ የተለየ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ታዳምጥ ነበር፡፡ ብልህ ብትሆን ኖሮ ለመናገር ብቻ ሳይሆን ለመስማት ዕድል ትሰጥ ነበር፡፡ በል ይመችህ፤ እዚሁ ኩሬህ ውስጥ ኑር፡፡ እውነትም ከዚህ የተሻለ ላንተ አይገኝም፡፡ እዚህ ኩሬ ውስጥ የምትኖረው ኩሬው ከሁሉም የሚበልጥ ስለሆነ ሳይሆን ላንተ ስለሚመጥንህ ነው፡፡ ቀሪ ሕይወቴን ከሞኝ ጋር ከምኖር ብልሆች ወዳሉበት እየሄድኩ ብሞት ይሻለኛል› ብሎ ከኩሬው ወጥቶ ሄደ፡፡

ዕንቁራሪቱም በአንድ ዓይኑ ሲያይ የኩሬውን ግድግዳ ተመለከተው፡፡ ‹ይህ የዓለም ዳርቻ አይደለምን፡፡ ለመሆኑ ይህ ዔሊ ከዓለም ዳርቻ ውጭ የት ሊሄድ ነው› አለ ይባላል፡፡

ኪችነር፣ ካናዳ

እየላሱ መሞት

$
0
0
click here for pdf 
በርለዓም ወየወሴፍ
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከምናገኛቸው የጥበብ መጻሕፍት አንዱ ‹በርለዓም ወየወሴፍ› የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ 
በርለዓም ወየወሴፍ የተለያዩ ምሳሌዎችንና ተረቶችን የያዘ የሕንድ መጽሐፍ ነው፡፡ የተወሰደውም ከትውፊታዊው የጉተማ ቡድሐ የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ የፍቅር ታሪክ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ቅጅዎች በአይሁድ፣ በማኒያውያን[i]፣ በሙስሊሞች ዘንድና በክርስቲያኖች ዘንድ ይገኛሉ፡፡ 
ዋዳጎስ የተባለ እጅግ ባዕለ ጸጋ የሆነ ኃይለኛ የሕንድ ንጉሥ በሕንድ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ፡፡ አንድ ቀን ዋዳጎስ የወሴፍ የሚባል ወንድ ልጅ ወለደ፡፡ ኮከብ ቆጣሪዎችና ጠንቋዮች ስለ ልጁ ዕጣ ፈንታ ሲጠየቁ ልጁ ወደፊት ክርስቲያን እንደሚሆንና የክርስቶስን ሃይማኖትንም ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ይህንን በመፍራት ንጉሡ ልጁን በአንድ ቤተ መንግሥት ውስጥ ወስኖ አስቀመጠው፡፡ ኀዘን፣ ድክመት፣ ሞት የሚባሉትን ነገሮች እንዳያውቅ እርሱንም ከደስታ የሚያወጣውን ነገር እንዳያጋጥመው አደረገው፡፡ 
እያደገ ሲሄድ ግን መስፍኑ ከዚያ ቤተ መንግሥት ውጭ ያለውን ዓለም ለማወቅ ፈለገ፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ውጭም ኃዘን፣ በሽታ፣ ልቅሶ፣ ረኃብና ሞት መኖራቸውን ተረዳ፡፡ ታዋቂው መናኝ መምህር በርለዓምም መስፍኑን አገኘው፡፡ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ክርስትናም አስተማረው፡፡ ይህንንም ያስተማረው የተለያዩ ታሪኮችንና አባባሎችን በመጠቀም ነበር፡፡ 



መስፍኑ የወሴፍ ዓለምን ለመካድ ከበርለዓም ጋር ያለውንም ግንኙነት አባቱ ሳይሰማ ለማቆም ፈለገ፡፡ አባቱ ነገሩን ከመስማቱ በፊትም በርለዓም ከእርሱ ተለየ፡፡ ንጉሡም ነገሩን ሲሰማ እጅግ ተበሳጨ፡፡ የወሴፍን ወደ ጥንት እምነቱ ለመመለስም የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡ የመንግሥቱን አንድ ሦስተኛ ለመስጠት ቃል እስከ መግባትም ደረሰ፡፡ የወሴፍ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በመጨረሻም ንጉሡ ራሱ ስሕተቱ ገባው፡፡ አማካሪዎቹ ሁሉ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላም ንጉሡም ክርስትናን ተቀበለ፡፡ 
አባቱ ከሞተ በኋላ የወሴፍ መንግሥቱን ተወ፡፡ እጅግ ለሚያምነው ተከታዩ ዙፋኑን በመስጠትም መምህሩ በርለዓምን ለመፈለግ ወደ በረሐ ሄደ፡፡ እዚያ በርለዓምን ሲያገኘውም ሁለቱም የምናኔ ሕይወታቸውን እስከ ዕለተ ሞታቸው ቀጠሉ፡፡
መጽሐፉን ያስተረጎመው ዐፄ ገላውዴዎስ ሲሆን የተረጎመው ደግሞ እጨጌ ዕንባቆም ነው፡፡ ትርጉሙም የተከናወነው በ1546 ዓ.ም. ነው፡፡ [ii]

አልቫሬዝ እንደሚለው ካህናቱ የበርለዓምንና የወሴፍን መጽሐፍ አምጥተው የበርለዓምን የመታሰቢያ ቀን እንዲነግራቸው ጠይቀውት እንደነበር ጽፏል[iii]፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ መጽሐፈ በርለዓም ወየወሴፍ የተጻፈበት ዘመን 1519 ዓ.ም. ቀደም ይላል ማለት ነው፡፡ ምናልባትም ዕንባቆም መጀመሪያ ተርጉሞት በኋላ ለዐፄ ገላውዴዎስ እንደገና ጽፎለት ይሆናል፡፡[iv]
 
በበርለዓም ወየወሴፍ ከምናገኛቸው ምሳሌያዊ ትምህርቶች መካከል ለዛሬ አንዱን እንጋበዝ፡፡

እየላሱ መሞት
አንድ ሰው ድንገት አውሬ ይመጣበታል፡፡ የአውሬው ጩኸትና ድንፋታ እግሬ አውጭኝ ብሎ እንዲሸሽ ያደርገዋል፡፡ ከአውሬው ሸሸሁ ብሎ ሲሮጥ ጥልቅ ወደሆነ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ወደ ጉድጓዱ ጥልቅ እየተወረወረ እያለ በጉድጓዱ ግድግዳ ላይ የበቀለ ሁለት ቅርንጫፎች ያሉት ዛፍ ያገኝና ያንን በሁለት እጆቹ ይዞ ፋታ ያገኛል፡፡ እግሩም በዛፉ ሥሮች ላይ ያርፋል፡፡ ይህን ዕድል ሲያገኝ እስከ ጊዜው ድረስ ነፍሱ መትረፏን፡፡ ጥቂት በዚህ ሁኔታ ከቆየ ደግሞ ቀስ በቀስ ከዚህ ጉድጓድ ሊወጣ እንደሚችል ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ከሞት መትረፉንም ርግጠኛ ሆነ፡፡
የዛፉን ቅርንጫፎች እንደያዘ፣ እግሩንም በግንዱ ላይ እንዳስደገፈ አንገቱን ዝቅ አድርጎ ሊወድቅበት የነበረው ጉድጓድ ተመለከተው፡፡ በጉድጓዱ ሥር ዓይኑ አንደ እሳት የሚያበራ፣ ሰውነቱ አንደ ሰርዶ የተጠቀለለ፣ ራሱ እንደ ዱባ የሚንከባለል፣ አፉ እንደ ገደል የተከፈተ ዘንዶ ተመለከተ፡፡ በዚያ አጋጣሚ ነፍሱ ጥላው ልትሄድ ስትል ለጥቂት ነው የመለሳት፡፡ ከአንደኛው አውሬ አፍ አመለጥኩ ሲል ወደሌላው አውሬ አፍ እየተሸጋገረ መሆኑን ሲያስበው ልቡ እንደ እማሪት ያለ ማቋረጥ ይመታ ጀመር፡፡
ዓይኑን ከዘንዶው ነቅሎ ወደ ላይ ሲመልሰው እርሱ የተንጠለጠለበትን ቅርንጫፍ አንድ ነጭና አንድ ጥቁር አንበጣዎች ባለማቋረጥ እየበጠሱ ሲጥሉት ተመለከተ፡፡ ሁለቱም እጆቹ ስለያዙ ምን ያድርጋቸው፡፡ አንበጣዎቹ ለየትና ከበድ ያሉ ናቸው፡፡ ይበላሉ፣ ይበላሉ፣ ይበላሉ፣ አያቋርጡም፡፡ እርሱ ተማምኖ አጥብቆ የያዘውን ቅርንጫፍ እነርሱ በበሉት ቁጥር ግንዱ እየመነመነ ይሄዳል፡፡ ይህንን ሲያስብም የተንጠለጠለበት ሰው ተስፋም እየመነመነ ሄደ፡፡ ያ ቅርንጫፍ ተቆርጦ አጆቹ የሚይዙት አጥተው ቢወድቅ የዚያ እሳታማ ዘንዶ ራት እንደሚሆን ሲያስበው ዘገነነው፡፡
የእጆቹ ነገር እንዲህ መሆኑን ሲያይ ያለ የሌለ ጉልበቱን ሰብስቦ እግሩ ያረፈበትን ግንድ ተመለከተው፡፡ አራት እባቦች ከዛፉ ግንድ ስንጥቅ ውስጥ እየወጡ ነበር፡፡ የነዚያ እባቦች ቤት ያ የዛፉ ስንጥቅ ነው፡፡ እነዚያ አራት እባቦች ከዚያ ስንጥቅ ውስጥ ከወጡ እግሩ ወዳረፈበት ቦታ መምጣታቸው ነው፡፡ እንኳንስ አራቱንና አንዱንስ በምኑ ይከላከለዋል፡፡ አራቱ ከአራቱም አቅጣጫ ከመጡበት ደግሞ እግሩን የሚያሳርፍበት ቦታ ፈጽሞ አይኖረውም፡፡ ከላይ አንበጦቹ አጁ ያረፈበትን ይገዘግዛሉ፣ ከታች እባቦቹ ራሳቸው እንደ ባትሪ እየወዘወዙ ከስንጥቁ ይወጣሉ፡፡ ከጉደጓዱ ሥር ደግሞ እሳታማው ዘንዶ አፉን ከፍቶ ይጠባበቃል፡፡
ሰውዬው ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ደርሶ የአንበጦቹን ፍጻሜ ለማየት ቀና ሲል አንዳች ጣፋጭ ነገር አፉ ውስጥ ጠብ አለ፡፡ በዛፉ ቅርንጫፍ ጫፍ ላይ ንቦች ከበው ማር እየሠሩ ነው፡፡ ያ የንች ማር ጠብ፣ ጠብ ይላል፡፡ ከነዚያ ተብታዎች አንዷ ናት ምላሱ ላይ የነጠበችው፡፡ እፎይ አለ ሰውዬው፡፡ የማሩን ወለላ አጣጥሞ፡፡ የማሩን ወለላ ሲያጣጥም ጅቡ ከጉድቃዱ አፍ ቆሞ አንደሚጠብቀው፤ ቅርንጫፉን አንበጦቹ እንደሚገዘግዙት፤ አራቱ እባቦች እግሩ ከረገጠበት ግንድ ስንጥቃት ውስጥ እንደሚወጡ፣ ከጉድጓዱ ሥርም አፉን የከፈተ ዘንዶ እንደተኛ፤ ልጡ የተራሰ፣ ጉድጓዱ የተማሰ መሆኑን ዘነጋው፡፡ ልቡ በማሩ ጣዕም ከጉደጓዱ ወጣች፡፡
በዙሪያው ያለውን እውነታ ዘነጋና በጠብታዋ ማር ጊዜያዊ ርካታና ደስታ ተዋጠ፡፡ በዙሪያው ያለው ሊውጠው የደረሰውን ችግር ትቶ ድንገት ባገኛት ደስታ ሰመጠ፡፡ አንደኛዋን ጠብታ አጣጥም ሌላኛዋን ለመቀበል አፉን እየከፈተ፣ ከገዛ ድርጊቱ ጋር ፍቅር ይዞት ጅቡንም፣ አንበጣውንም፣ እባቦቹንም፣ ዘንዶውንም ረሳቸው፡፡ እየመጣበት ካለው ጥፋት ይልቅ እየተንጠባጠበለት ወደለው ማር ዞረ፡፡
በርለዓም እንዲህ ይተረጉማል፡፡
ጅብ የተባለ ሞትና ጥፋት ነው፡፡ ሰው መጥፊያው ሲያባርረው፣ ሞትም ሲከተለው የሚያመልጥ መስሎት ይሸሻል፡፡ ሲሸሽ ባላሰበው የችግር ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፡፡ መጋፈጥ እንጂ መሸሽ ማሸነፍን አያመጣም፡፡ ጉድጓዱ ሁሉም ዓይነት ችግር የተጠራቀመበት ነው፡፡ አንዱን ችግር በብልጠት አልፋለሁ ብለህ ከሸሸህ የባሰው ችግር ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ አንዱን መፍታት ካቃተህ ችግሮች በማኅበር ይመጡብሃል፡፡ አንዱን ቸላ ካልከው ከመከራ መንጋ ጋር ትጋፈጣለህ፡፡ ሰውዬው የተንጠለጠለበት ባለሁለት ቅርንጫፍ ዛፍ የተሰጠን የእድሜ ዘመናችን ነው፡፡ ዘመን ስትሠራበት አንጂ ስትንጠለጠልበት መከራ ይጎትታል፡፡ ሁለቱን ቅርንጫፎች ነጭና ጥቁር አንበጦች ባለማቋረጥ ይገዘግዟቸው ነበር፡፡ እነዚህም ቀንና ሌሊት ናቸው፡፡ አንተ የተንጠለጠልክበት ጊዜ የሚባለውን ዛፍ ቀንና ሌሊት የተባሉ አንበጦች በየቀኑ እየገዘገዙ ያመናምኑታል፡፡ የያዝከው ይመስሃል እንጂ የያዝከው እስከጊዜው ብቻ ነው፡፡
አራቱ ከዛፉ ስንጥቃት ውስጥ በየተራ የሚወጡት እባቦች አራቱ የሰዎች ጠባዮች ናቸው፡፡ ነፋስ፣ እሳት፣ ውኃና አፈር፡፡ እነዚህ በየተራ ከጊዜ ውስጥ እየወጡ ልጅነትህን፣ ወጣትነትህን፣ ጉልምስናህንና እርጅናህን እየበሉ ይጨርሱታል፡፡ አራቱም በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አራቱም የእድሜ ምዕራፎች በዘመንህ ውስጥ አሉ፡፡ እሳቱ ከውኃው ጋር፣ ነፋሱም ከአፈሩ ጋር ተሰጥቶሃል፡፡ በየዘመናቱ ካልሠራህባቸው ግን ከጉደጓዳቸው እየወጡ መምጣታቸው እንደሆነ አይቀርም፡፡
በጉደጓዱ መጨረሻ የነበረው ዘንዶ ሞት ወይም ጥፋት ነው፡፡ በስተመጨረሻ የሚጠብቀው ይህ ነው፡፡ የምንዘነጋውም ይህን ነው፡፡ ከታች ያንን የመሰለ ዘንዶ እየጠበቀው ሰውየው ድንገት ባገኛት የማር ጠብታ ነገር ዓለሙን ሁሉ ዘነጋው፡፡ ችግሮችህ ከበውህ፣ ዙሪያህንም እየገዘገዙህ፣ ወደ መጨረሻው ጥፋትም እየወሰዱህ፣ ጉድጓድ ውስጥ መውደቅህን አያወቅህ፤ ከእውነታው ጋር ስትጋፈጥ ድንገት እንደ ማር ጠብታዋ ያለች ጊዜያዊ ድል፣ ርካታና ፋታ ታገኛለህ፡፡ ያን ጊዜ ጅቡንም፣ አንበጣውንም፣ እባቡንም ዘንዶውን ትረሳዋለህ፡፡ ከእውነታው ጋር ከመጋፋጥ ይልቅ እውነታውን መርሳትን ትመርጣለህ፡፡ ጅቡም፣ አንበጣውም፣ እባቦቹም፣ ዘንዶው ባሉበት አሉ፡፡ ጅቡ እየጮኸ ነው፤ አንበጦቹም እየገዘገዙ ነው፣ እባቦቹ ከስንጥቃቱ እየወጡ ነው፤ ዘንዶው አፉን ከፍቶ ሊያጣጥምህ እየቋመጠ ነው፡፡ ሁሉም ነገር አልተቀየረም፡፡ የተቀየረው የአንተ ልቡና ብቻ ነው፡፡ እውነታውን ረሳኸው፡፡ የማሩን ጠብታ ስትልስ ከጉድጓድ የወጣህ መሰለህ፡፡ ሁሉም ነገር የተቀየረ፣ ሰላም የሆነና የተረጋጋ መሰለህ፤ ጉድጓዱን ሜዳ፣ ዘንዶው በግ፣ አንበጣውን ቢራቢሮ፣ እባቦቹን ርግቦች፣ ጅቡንም ፈረስ አድርገህ ቆጠርከው፡፡
እውነታውን መርሳት እውነታውን አይቀይረውም፡፡ አንተ የማሩን ጠብታ ስላጣጣምክ ጅቡም፣ አንበጦቹም፣ እባቦቹም ዘንዶው ሥራቸውን አያቆሙም፡፡ ምናልባት እየተራቡና እየተማረሩ ከመሞት የማር ወለላ እያጣጣሙ መሞት ይሻላል ካላልክ በስተቀር፡፡



[i]ማኔ በ3ኛው መክዘ በኢራን የተነሣ የግኖስቲክ አራማጅ ነው፡፡ የማኒ ዋናው እምነት ምንታዌ ነው፡፡ ክፉና ደግ ነገሮች በተለያዩ ፈጣሪዎች የተፈጠሩ ናቸው የሚል፡፡
[ii]Encyclopedia Aethiopica, Vol. 1, P. 472-473
[iii]The Preseter John of the Indies, p. 312
[iv]ስለ ተርጓሚው ስለ እጨጌ ዕንባቆም ለማወቅ ‹ እጨጌ ዕንባቆም - ከየመን እስከ ደብረ ሊባኖስ› የሚለውን መጽሐፍ ያንብቡ፡፡

ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ

$
0
0
ሠፈራችን አንድ ሠርግ ቤት ውስጥ ልጃገረዶቹ ተሰባስበው
‹ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ
ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ
ይጠቀለላል እንደ ሠርዶ
ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ›
እያሉ ያስነኩታል፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ እንዳቀነቀኑ እናትዬዋ ወገባቸውን እየሰበቁ ወጡና
‹‹አቁሙ፤ እርሱን ዘፈን አቁሙ›› አሉና ተቆጡ፡፡
‹‹ለምን እማማ?›› ልጃገረዶቹ ከዘፈን ትንፋሽ ባልወጣ ድምፃቸው ተንጫጩ፡፡
‹‹ምነው ሸዋ፤ የኔ ልጅ ከነ ፀጉሯ እንድትኖርልኝ እፈልጋለሁ ልጄ፤ ሐሳብ የለሽ ሁላ›› አሉ እማማ፡፡
‹‹ታድያ እኛ ዘፈንላት እንጂ ምን አረግናት›› ልጃገረዶቹ እየሳቁ ጠየቁ፡፡
‹‹እናንተ ምን ታደርጉ፡፡ ቴሌቭዥን አትከታተሉማ፤ ምን የዛሬ ልጆች ወይ ቃና ወይ ምርቃና ላይ ናችሁ፡፡››
‹‹ምን ተባለ ደግሞ እማማ፤ ተከለከለ እንዴ›› አለች አንዲት ወጣት አታሞውን እንደያዘች፡፡
‹‹ቻይናና ጃፓን ዶላር ሲያጡ የሴቶችን ፀጉር እንደሸጡ አልሰማችሁም›› እማማ በልጆቹ አለማሰብ ተናደዋል፡፡
‹‹ታድያ ቻይናና ጃፓን ቢሸጡ እኛ ምን አገባን፤ እንዝፈን ባካችሁ›› አለች ልጂቱ፡፡

‹‹ዛሬ ለጃፓንና ለቻይና የተባለውኮ ነገ ለኛም ይመጣል፡፡ ‹ድሮም ከቆሮንቶስ ተጀምሮ ነው እኛ ዘንድ የሚደርሰው› አሉ እትዬ ስንዱ›፡፡
‹‹በሞቴ እማማ ይህን ታሪክ ይንገሩን›› አሉ ወ/ሮ አያህሉሽ ሽንኩርት መላጡን ትተው፡፡ እማማም በዚያው ዘፈኑ እንዲረሳላቸው ፈለጉና ‹እይውልሽ መምሩ የቆሮንቶስ ሰዎች አመንዝሮች ናቸው፡፡ አመንዝራነት ጥሩ አይደለም፡፡ እያሉ ሕዝቡን ይወቅጡት ጀመር፡፡ ታድያ እትዬ ስንዱ መረራቸውና ‹አሁን እኛ አመንዝራ አይደለን ለምን ይወቅሱናል?› ብለው መምሩን መጠየቅ፡፡ መምሩም ደነገጡና ‹አይ እኔኮ የቆሮንቶስ ሰዎችን እንጂ እናንተን አላልኩም› ይሏቸዋል፡፡ እትዬ ስንዱም ‹ድሮም ከቆሮንቶስ ተጀምሮ ነው እኛ ዘንድ የሚደርሰው እንጂ ለኢትዮጵያ ብሎ ድሮስ ማን ጻፈ› አሉ አሉ፡፡››
ልጆቹም ወ/ሮ አያህሉሽም ሳቁ፡፡
‹‹ምናለ ታድያ ሴቶቹን ትተው እነዚህን ፀጉራቸውን እንደ ገመድ የሚያስረዝሙትን ወንዶች እያጨዱ አይሸጡልኝም ነበር›› አሉ ወ/ሮ አያህሉሽ፡፡
‹‹እርስዎ ደግሞ፤ የሴቶቹ እንጂ የወንዶቹ በዶላር ተሸጠ ማን አለ፡፡ የተባለውን ነው መስማት፡፡ መጀመሪያ የተባለውን በትክክል መስማት ነው፡፡ ቀጥሎ አስተካክሎ መተርጎም ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ አስተካክሎ መጠንቀቅ ነው፡፡ ዛሬ ቻይና ላይ ተደረገ ከተባለ ነገ እዚህ እኛ ቀበሌ አጀንዳ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከውስጥ የተገኘ ዕውቀት እንጂ ከውጭ የተገኘ ልምድ መች ይናቃል፡፡ ይኼ ሁሉ ባለ ሥልጣን ቻይና ጎብኝቶ ጎብኝቶ መዐት ሊያመጣብን ነው መሰል፡፡ ‹መላጣ፣ የሥላሴ ጦጣ፣ አይበላም ሰላጣ› እንዳልተባለ ሁሉ መላጣ የሚመሰገንበት ዘመን ሊመጣ እንዳይሆን፡፡››
‹‹አይ እማማ›› አሉ ወ/ሮ አያህሉሽ ሽንኩርቱን እየላጡ ‹‹መላጣማ ችግር ላይኮ ነው››
‹‹ምንድነው ደግሞ ችግሩ››
‹‹ዘንድሮኮ በከተማው ባዶ ቦታ እንዳይኖር ተብሏል፡፡ ወደፊትኮ ባዶ ቦታ ለማየት ገጠር መሄድ ይኖርብናል፡፡ በዚህ አያያዝ በከተማ ባዶ ቦታ ሲጠፋ ልጆቻችንን ስለ ባዶ ቦታ ማስተማር የምንችለው መላጣ ሰው እያሳየን ብቻ ነው፡፡›› ወይዘሮ አያህሉሽ ብቻቸውን ሳቁ፡፡ ልጃገረዶቹም አብረው ሳቁና ‹‹እና መላጣ የትምህርት መሣሪያ ሊሆን ነው›› ብለው ጨመሩበት፡፡
‹‹አያችሁ ልጆች፣ ለዚህ ነው ‹ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ› ብላችሁ መዝፈኑን ተውት ያልኳችሁ›› አሉ እማማ
‹‹ታድያ ምን ብለን እንዝፈን› ልጃገረዶቹ በቅሬታ ድምፀት ጠየቁ
‹‹እስከ መቼ ድረስ ፀጉር ተበጥሮ
መቀስ የት ይገኛል ቁርጥ ነው ዘንድሮ›› በሉታ፡፡
 

ብቻህን አይደለህም

$
0
0


የቼሮቄ ጎሳዎች በደቡብ ምሥራቅ አሜሪካ የነበሩ ጥንታውያን የአሜሪካ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የቼሮቄ ወጣቶች ለዐቅመ አዳም መድረሳቸውን የሚገልጡበት አንድ ከባድ ፈተና አላቸው፡፡ ወጣቱን አባቱ ይዞት ሊመሻሽ ሲል ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡ ዓይኑን በጨርቅ ይታሠራል፡፡ ምንም ነገር ለማየት አይችልም፡፡ ያንን ጨርቅም ከዓይኑ ላይ ለማንሣት አይፈቀድለትም፡፡ አንድ ቦታ ላይ ይቀመጣል፡፡ ከተቀመጠበት ቦታም መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም፡፡ ጨለማው አልፎ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ በዚያ ጫካ ውስጥ ለብቻው አንድ ቦታ ተቀምጦ ማሳለፍና ‹ወንድነቱን› መፈተን አለበት፡፡ አካባቢው ጸጥ ያለ ነው፡፡ ከአራዊት ጩኸትና ኮሽታ በቀር ሌላ የለበትም፡፡ ሰውም በአካባቢው አይደርስም፡፡ ምግብና ውኃ የሚያቀብለውም የለም፡፡ የልብ ምቱን እያዳመጠ ሌሊቱን በጸጥታ ያሳልፈዋል፡፡ ይህን ሌሊት ያለ ችግር ለማሳለፍ የቻለ ወጣት ለዐቅመ አዳም ደረሰ ማለት ነው፡፡ እንዴት እንዳሳለፈውና ምን እንዳጋጠመው ከእርሱ በታች ላሉት ልጆች ለመናገር አይፈቀድለትም፡፡ እያንዳንዱ ወንድ የራሱን ማንነት በባህሉ መሠረት መፈተሽ አለበትና፡፡
በዚህ ሥርዓት መሠረት አንድ የቼሮቄ ወጣት በምሥራቅ ቴነሲና በሰሜን ካሮላይና ወደሚገኘው የቼሮቄ ደን ተወሰደ፡፡ ፀሐይ እየጠለቀች መሆኑን እያየ ነው የተጓዘው፡፡ አባቱ የዓይን ማሠሪያውን ጨርቅ ይዟል፡፡ ሌሎች ሸኚ የጎሳ አባላት ደግሞ ይከተሉታል፡፡ ጥቅጥቅ ያለውን ደን አቋርጠው ከዛፎቹ ርዝማኔ የተነሣ ፀሐይን ለማየት ወደማይቻልበት ሆድ ውስጥ ገቡ፡፡ ሌሊቱን የማሳለፊያው ቦታ ተመረጠ፡፡ ወጣቱም ዓይኑን በጨርቅ ታሠረ፡፡ ታዛቢዎችም ዓይኑ በሚገባ የታሠረ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ከዚያም አንድ ቦታ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ሰዎች ተራ በተራ እየተሰናበቱት አካባቢውን ለቅቀው ሄዱ፡፡ ኮቴያቸው እየራቀው እየራቀው ሲሄድ ይታወቀዋል፡፡

 አካባቢው ጸጥ ረጭ አለ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የዛፎቹ ንጽውትውታ ይሰማ ነበር፡፡ ነፋሱና ቅጠሎቹ ኅብረት ፈጥረው እያዝናኑት ነበር፡፡ እየቆየ ግን ሁሉም ነገር ረጋ፡፡ እዚህም እዚያም ‹ኮሽ› የሚል ነገር ይሰማል፡፡ ቱርር ብለው የሚያልፉ ነገሮች አሉ፡፡ በቼሮቄ ተረቶች ውስጥ ስለ ቼሮቄ ደን የሰማቸውን ተረቶችና ታሪኮች አስታወሰ፡፡ አዳኞች ወደዚህ ጫካ መጥተው ያፈጸሟቸው ጀብዱዎች፣ ያጋጠሟቸውንም ፈተናዎች፣ ያለፉባቸውንም ውጣ ውረዶች ይተርኩ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ደኑን በእግር አቋርጦ መውጣት ራሱ እንደ ጀግንነት ይቆጠር ነበር፡፡ መጀመሪያ በበትር እየገለጡ ለመሄድ የሚስቻለው ደን እየቆየ ግን ዓይን እስከመውጋት ይደርሳል፡፡ ጥቅጥቅ ይልና ቀኑን ጨለማ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ደን ውስጥ አልፎ አልፎ በጎሳዎች መካከል ውጊያ እንደተደረገ ይወራል፡፡
ሌሊቱ እየጨመረ ሲሄድ ፍርሃት ይመጣበት ጀመር፡፡ ለምን እዚህ እንደመጣ፣ ይህንን ፈተና ሲያልፍ የሚያገኘውን ክብር፣ ክብሩ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡና ለጎሳው ሁሉ እንደሚተርፍ ሲያስበው እንደገና የብርታት መንፈስ ይወረዋል፡፡ 650ሺ ሄክታር በሚደርሰው የቼሮቄ ደን ውስጥ ከ20 ሺ በላይ የእንስሳትና የዕጽዋት ዝርያዎች ይኖራሉ፡፡ ረዣዥም ተራሮች፣ ጫካ አቋርጠው የሚጓዙ ወንዞች፣ ገበታ የመሰሉ ሸለቆዎች፣ አስቸጋሪ ገደላ ገደሎችና ለጥ ያሉ ሜዳዎች በውስጡ አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ወጣቱ ያስባቸዋል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀውና የሚያስፈራው አንድ ነገር ነው፡፡ ብቻውን መሆኑ፡፡ ቼሮቄዎች ‹አሲ› ብለው በሚጠሯቸው ባህላዊ ቤቶቻቸው ውስጥ በአንድ ቤት አብረው የሚያድሩት ብዙ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ብቻውን የሚኖርም ሆነ ብቻውን የሚያድር የለም፡፡ አደን ሲሄዱ በጋራ ነው፤ ወንዝ ሲወርዱም በጋራ ነው፡፡ አሁን ግን ለብቻው በቼሮቄ ደን ውስጥ ያውም በሌሊት ቁጭ ብሏል፡፡ ዕንቅልፉ ይመጣና ይሄዳል፡፡ ብርታቱ ይመጣና በፍርሃት ይተካል፤ እንደገና ደግሞ በጀግንነት ስሜት ይወረራል፡፡ አንዳች አውሬ ቢመጣበት ምን ለማድረግ ይችላል? ሳያየው በድምጹና በአካሄዱ ብቻ ማንነቱን መለየት አለበት፡፡ ዓይኑ እንደተሸፈነ መከላከልና መቋቋምም አለበት፡፡ ያውም ብቻውን፡፡ የሚረዳው የለም፤ ምን እንደሆነ እንኳን ታሪኩን ሊነግርለት የሚችል የለም፡፡ቢቆስል የሚያያክመው፤ አውሬው ይዞት ቢሄድ የሚያስጥለው የለም፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያስብ ፍርሃቱ ያይላል፡፡
በሐሳብ ወዲያና ወዲህ እየተማታ ሌሊቱ ይገሠግሣል፡፡ አራዊቱ ይጮኻሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በአጠገቡ ናቸው፡፡ ከሹክሹክታ፣ እስከ ግሣት፣ ከሲርታ እስከ ፉጨት ድምጻቸው ይመጣል ይሄዳል፡፡ ዙሪያውን እየከበቡ የሚተራመሱ አራዊትም አሉ፡፡ በእግሩ ሥር ሲያልፉ፤ ሰውነቱን ታክከውት ሲሄዱ ይሰማዋል፡፡ ባህሉ ግን ካለበት ቦታ እንዲነቃነቅ አይፈቅድለትም፡፡ በጽናትና በትዕግሥት፣ ያለ ፍርሃትና ያለ ጭንቀት ባለበት እንደተቀመጠ የፀሐይዋን ምጽአት መጠበቅ አለበት፡፡
አራዊቱም፣ ነፍሳቱም፣ የጫካው ግርማም አያስጨንቀውም፡፡ የሚያስጨንቀው በዚያ ከልጅ እስከ ቅመ አያት በአንድነት በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ አድጎ በዚህ ጫካ ውስጥ ብቻውን መሆኑ ነው፡፡ ከአራዊቱ ይልቅ ብቸኝነቱ ያስፈራዋል፡፡ ለአራዊቱ አራዊት፣ ለነፍሳቱም ነፍሳት፣ ለዛፎቹም ዛፍ አላቸው፡፡ እርሱ ግን ብቻውን ነው፡፡ እንደዚህ ሌሊት ሰው ተመኝቶ አያውቅም፡፡ ግን ብቻውን ነው፡፡ እንደዚህ ሌሊት ሰው ናፍቆት አያውቅም፡፡ ግን ብቻውን ነው፡፡
ሌሊቱ እየገሠገሠ ነው፡፡ ድካሙም እየጨመረ ነው፡፡ በዚያ የብርታቱ ሰዓት ያልመጡት አራዊት በዚህ የድካሙ ሰዓት ቢመጡ ምን ሊውጠው ነው? የኦኮናሉፍቴ ወንዝ ከዐለቱ ጋር እየተጋጨ ሲወርድ የሚፈጥረው ድምጽ ይሰማዋል፡፡ ወንዙ ከዐለቱ ጋር የሚጋጭበት ጋ ሲደርስ መልኩ ቡናማ ይሆናል፡፡ ወዲያው ደግሞ አካባቢው ቀስተ ደመና ይፈጥራል፡፡ አሁን ግን ሌሊት ነው፡፡ ምን እየሆነ እንደሆን አያውቅም፡፡
ሸለብ ሊያደርገው ሲሞክር የወፎቹን ድምጽ ሰማ፡፡ እየነጋ መሆኑን ሲያስብ ብርታቱ ተሰብስቦ መጣ፡፡ የመከራው ሌሊት እያለፈ ነው፡፡ ለዐቅመ አዳም የሚደርስበትና ሠፈሩ በከበሮ የሚናወጥበት ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ ጥቂት ከቆየ ፀሐይዋ ብቅ ትላለች፡፡ ዓይኑ የተሸፈነበትን ጨርቅ ማሞቅ ስትጀምር ያን ጊዜ ጨርቁን ይፈታዋል፡፡ ይህንን የብቸኝነት ጫካ እየዘለለ ለቅቆ ጎሳው በጉጉት ወደሚጠብቅበት ሥፍራ ይገሠግሣል፡፡
እንደጠበቃት ፀሐይዋ መውጣቷን ዐወጀች፡፡ ዓይኑ የታሠረበት ጨርቅ መሞቅ ጀመረ፡፡ አሁን ጨርቁን መፍታት ይችላል፡፡ ብርዱ ያቆረፈደውን እጁን አፍታትቶ ጨርቁን በፍጥነት መፍታት ጀመረ፡፡ ቋጠሮዎቹን ቀስ በቀስ አላቅቆ ዓይኑን ነጻ ሲያወጣ፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች አካባቢው ተደናበረበት፡፡ ጸጥ ብሎ ቆየና ዓይኖቹን አሻቸው፡፡ ቀስ በቀስም አካባቢው በብርሃን እየተገለጠለት መጣ፡፡ ፊት ለፊት ወዳለው ጫካ ዓይኑን ሲወረውር ጉብታው ላይ አባቱን አየው፡፡ ውርጩ በላዩ ላይ ዘንቦበታል፡፡ ጦሩን ተክሎ ቀስቱን አንግቶ ተቀምጧል፡፡
ተወርውሮ ሄደና አቀፈው፡፡ ‹መቼ መጣህ?› አለው የልብሱ ቅዝቃዜ እየተሰማው፡፡
‹እዚሁ ነበርኩ› አለው አባቱ፡፡
‹ከመቼ ጀምሮ› አለው ልጁ፡፡
‹ከመጀመሪያ ጀምሬ›
‹ሌሊቱን እዚህ ነው እንዴ ያደርከው›
‹አዎ›
‹እኔኮ ብቻየን የሆንኩ መስሎኝ ነበር›
‹ብቻህን አልነበርክም፡፡ እኔ በንቃት እየተከታተልኩህም፣ እየጠበቅኩህም ነበር፡፡ አንተ ስታሸልብ እኔ ግን አላሸልብም ነበር፡፡ እዚሁ ነበርኩ፡፡ እያየሁህ ነበር፡፡ ምናልባት ግን ስለማታየኝ የሌለሁና ብቻህን የሆንክ መስሎህ ይሆናል፡፡ ግን አልነበርክም፡፡ ይህችን ቅጠል ታውቃታለህ? › አለው አባቱ ጎንበስ ብሎ አንዲት ሸካራ ቅጠል እየቆረጠ፡፡
‹አላውቃትም› አለ ልጁ፡፡
‹ይህቺ ቅጠል እባብና እርሱን የመሰሉትን የምታባርር ናት፡፡ ሽታዋን ከሩቁ ካሸተቱ በአካባቢዋ አይቀርቡም› አለው፡፡ ያንን ወንዝስ ታውቀዋለህ?› አለው በሩቁ ፀሐይዋ የምትንቦጫረቅበትን ወንዝ እያሳየ፡፡ ‹እርሱንማ አውቀዋለሁ፤ የኦኮናሉፍቴ ወንዝ አይደል እንዴ› አለና መለሰለት፡፡ ‹ታድያ የቱ አውሬ ነው ይህንን ገደላማ ወንዝ ተሻግሮ የሚመጣብህ› አለ አባቱ እየሳቀ፡፡ ልጁም ሳቀ፡፡ ‹ይህንን ሌሊት ሌሊት የሚመጣ ወፍስ ታውቀዋለህ› አለና አንድ ሽው ብሎ ያለፈ ወፍ አሳየው፡፡ ልጁ ወፉን ለማየት የሚችልበት ርቀት ላይ አልነበረም፡፡ ወፉም በሽውታ ነው ያለፈው፡፡ 
‹አላየሁትም› አለው ልጁ፡፡
‹ይህ ወፍ ሌሊት ሌሊት ያጉረመርማል፡፡ እርሱ ወደሚያጉረመርምበት ቦታ አራዊት አይቀርቡም፡፡ እነዚህ ሁሉ ሳያውቁህና ሳታውቃቸው አንተን ሲጠብቁህ ነው ያደሩት፡፡ አየህ ልጄ አብረውህ ሲጠብቁህ ያደሩ ብዙ ናቸው፡፡ ወንዙ፣ ዛፉ፣ ተራራው፣ እነዚህ ሁሉ አብረውህ ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔ አባትህ አብሬህ ነበርኩ፡፡ አንተ ግን ብቻዬን ነበርኩ አልክ፡፡ ብቸኝነትህን ያመጣው ብቻህን መሆንህ አይደለም፡፡ አብሮህ ያለውን አለማወቅህ እንጂ፡፡ ከዚህ ሌሊት እንድትማር የምንፈልገው አንዱ ትምህርት ሰው ምንጊዜም ብቻውን እንዳልሆነ እንድታውቅ ነው፡፡ አካባቢህን ካላወቅህ በሰዎች መካከል ሆነህ እንኳን ብቻህን ትሆናለህ፡፡ አካባቢህን ካወቅከው ግን መቼም ብቻህን አትሆንም፡፡›
አባትና ልጅ በደስታ እየተጨዋወቱ ከጫካው ወጥተው በጉጉት ወደሚጠብቃቸው ሕዝብ ተቀላቀሉ፡፡    

ኮርያ ላይ ሆኜ አድዋን ሳስባት

$
0
0



በኮርያ ዋና ከተማ ሶኡል፣ ናምዮንግ ዶንግ፣ ዮንግሳን-ጉ (29 Itaewon-ro, Namyeong-dong, Yongsan-gu, Seoul) በሚገኘው የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግድግዳዎች ላይ በኮርያ ጦርነት ወቅት ከመላው ዓለም ተሰባስበው ሲዋጉ የተሠዉ ወታደሮች ስም ዝርዝሮች ተጽፈዋል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ 121 ወታደሮቿን መሠዋቷ ተገልጧል፡፡ ከሁሉም ሀገሮች ብዙ ወታደሮችን ያሰለፈችውና ብዙ ወታደሮቿንም ያጣችው አሜሪካ ናት፡፡ የአሜሪካ ወታደሮች ዝርዝር በየግዛታቸው ረዥሙን ግድግዳ በሁለት እጥፍ ሞልቶታል፡፡
ይህን ሙዝየም ስጎበኝ ሁለት ነገሮች በሐሳቤ ይመጡ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ እጅግ ብዙ ጦርነቶችን አድርጋለች፡፡ በጦርነቱ ተጎድተናል፤ በጦርነቱም ተጠቅመናል፡፡ የሕይወት ጥፋት፣ የንብረት ጉዳት ደርሶብን፣ ማኅበራዊ ቀውሶችንም በተሸክመን የተጎዳነውን ያህል ሀገራችንን ከጠላት ጠብቀን በማወቆየታችን ነጻነት የሚያስገኘውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥቅምም አግኝተናል፡፡ በነጻነታችን ላይ ቆመን ሌሎች ነጻ እንዲሆኑም ታግለናል፡፡ ጦርነቶቻችን የዛሬዋን ሀገራችንንና የዛሬዎቹን ሕዝቦቻችንን አሁን ባሉበት መልክ ሠርተዋቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም የኢትዮጵያን የጦርነት ታሪክ የሚያሳይ አንድም የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ግን የለንም፡፡

በኢትዮጵያ ምድር የነበሩ ጦርነቶችን፤ ጦርነቶቹ በሀገሪቱ ላይ ያደረሱትን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች፣ በጦርነቶቹ የነበረውን አሰላለፍ፣ ትጥቅ፣ ስንቅ፣ ወታደራዊ አደረጃጀት፣ የጦርነቱ መሪዎችንና ተሳታፊዎችን፣ የተሠዉ ጀግኖቻችንን፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን፣ የወደመ ንብረታችንን፣ የተገኘ ነጻነታችንን ሊያሳይ የሚችል ብሔራዊ ሙዝየም ያስፈልገን ነበር፡፡

በዚህ ሙዝየም ከጦርነት ጋር የተያያዙ መዛግብት ይቀመጡበታል፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ ቅርሶች ይሰበሰቡበታል፣ ከጦርነት ጋር የተያያዙ ፎቶዎች፣ ሥዕሎችና ቪዲዮዎች ይታዩበታል፤ ጀግኖቹ ይከበሩበታል፤ አጥፊዎቹ ይወቀሱበታል፤ ሀገርን ሀገር አድርጎ ለማቆየት የተከፈለው መሥዋዕት ይዘከርበታል፤ ካለፈው ትምህርት ይወሰድበታል፤ለወደፊቱ ጥንቃቄ ይደረግበታል፡፡ የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም ስለሌለን ከጥንት እስከ ዛሬ አባቶቻችን እንዴት ተጋድለው፣ በምን ተጋድለው፣ ምን ለብሰው ተጋድለው፣ ምን ሰንቀው ተጋድለው፣ እንዴት ዘምተው ተጋድለው፣ እንዴት ተደራጅተው ተጋድለው ይህችን ሀገር እንዳቆዩዋት መልክ ባለው ደረጃ ታሪኩን ለመዘከር አልቻልንም፡፡ የቀድሞ መሣሪያዎቻችን እየጠፉ፣ የቀድሞ ወታደራዊ ማዕረጎች እየተረሱ፣ የቀድሞ የስንቅ ማዘጋጃ ሞያዎችና ዕቃዎች እየቀሩ፣ የቀድሞ የጦርነት ዐውዶች ለሌላ ተግባር እየተቀየሩ ይገኛሉ፡፡ 

ካለፈው ለመማር ባለመቻላችን ጦርነቶችን ደጋግመናቸዋል፤ ዛሬም ወደ ጦርነት የሚያመራው መንፈሳችን እንዳለ ነው፡፡ ለግጭቶች መፍቻ የሚሆኑ በቂ መንገዶችንም አልተለምንም፡፡ ካለፈው በሚገባ የማይማር የትናንቱን ስሕተት ለመድገም የተረገመ ነው ይባላልና፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ ለሀገራቸው ሲሉ መሥዋዕት የከፈሉ ጀግኖቻችን ጉዳይ ነው፡፡ ለመሆኑ በአድዋ ጦርነት የተሰለፉ ጀግኖች ስም ዝርዝር ይታወቃል? ተጽፎ ሊገኝበት የሚችል ይፋዊ መዝገብስ አለን? አድዋን ከተራራነት ወደ ታሪካዊ ሙዝየምነት ሳንቀይረው 115 ዓመታት አለፉ፡፡ አድዋና ማይጨው ቦታ እንጂ ሥፍራ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ በኮርያ ጦርነት ጊዜ አሜሪካ 36574 ወታደሮች ሞተውባታል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ወታደሮች ስም ዝርዝር በጦርነት መታሰቢያ ሙዝየሙ ላይ ተጽፏል፡፡ በጉራዕ፣ በጉንዲት፣ በዶጋሊ፣ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በመተማ፣ በሶማልያ፣ በባድሜ የተሠዉት ወታደሮቻችን ለመሆኑ ስንት ናቸው? እነማንስ ናቸው? መቼ ነው ይፋዊ ዝርዝራቸው የሚነገረው? የሰው ዋጋ ተከፍሎ እንደዋዛ የምናልፈውስ እስከ መቼ ነው? የኛን ጦርነቶች ተዋጊዎች ዝርዝር ሁሉን ማወቅ ያስቸግር ይሆናል፡፡ የምናውቃቸውን ዘርዝረን ለረሳናቸው ደግሞ ‹ያልታወቀው ወታደር› የተሰኘውን ሐውልት ማቆም እንችላለን፡፡ ያለፉትን የሚረሳ ሰው ራሱ የሚዘነጋበትን መንገድ የሚጠርግ ነው ይባላል፡፡ መታሰቢያችን ከዘመናችን ማለፍ የሚችለው የቀደሙትን መታሰቢያ ከዘመናቸው ማሳለፍ ከቻልን ነው፡፡ 


የኮርያ የጦርነት ሙዝየም በጀግንነትና በኩራት የሚዘክራቸውን ኮርያውያንንና የየሀገሩን ባለውለታዎች ሳይ የሀገሬ ጀግኖች ያሳዝኑኛል፡፡ ዋጋ በከፈሉባት ሀገር እነርሱን የሚያስታውስና ታሪካቸውን በየትውልዱ ሊቀርጽ የሚችል ክብራቸውንና ደረጃቸውን የጠበቀ መታሰቢያ አላገኙም፡፡ ምናልባትም የሚያዝነው መንፈሳቸው ይሆን ሀገሪቱን በየዘመናቱ አዙሪት ላይ የሚጥላት?

ቃኘው ሻለቃ - የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና

$
0
0



የቃኘው አባላት በኮርያ

አሁንከሴኦልወደቹንቾንከተማእየተጓዝንነው፡፡በትዝታደግሞወደኋላእንሄዳለን፡፡እኤአበሰኔ 1951 ዓም  የቃኘውሻለቃየመጀመሪያዎቹወታደሮችከዚያበፊትኢትዮጵያውያንእምብዛምስሙንሰምተውትወደማያውቁትየሩቅምሥራቅሀገርተንቀሳቀሱ፡፡በሰኔወር 1950 እኤአየተጫረውየኮርያልሳነምድርጦርነትከሁለተኛውየዓለምጦርነትበኋላየመጀመሪያውጦርነትነበር፡፡የሰሜንኮርያውመሪኪምኤልሱንግደቡብኮርያንበመውረርየኮርያንልሳነምድርአንድየማድረግሕልሙንሰሜንኮርያበነበረውየሶቪየትአምባሳደርበኩልከፕሬዚዳንትስታሊንጋርመከረበት፡፡በጉዳዩየተስማማውስታሊንናየታላቋቻይናመሪየነበረውማኦሴቱንግለኪምኤልሱንግቀኝእጃቸውንሰጡት፡፡ሰሜንኮርያምበሶቪየትናቻይናእየተረዳችደቡብኮርያንወረረች፡፡
 
የተባበሩትመንግሥታትድርጅትየጸጥታውምክርቤትበጁን 26 ቀን 1950 ዓምባደረገውስብሰባጠብጫሪነቱበአስቸኳይእንዲቆምወሰነ፡፡ሰሜንኮርያግንውሳኔውንቸልበማለትወረራዋንቀጠለችበት፡፡የተባበሩትመንግሥታትድርጅትየጸጥታውጥበቃምክርቤትምለዓለምሰላምሲባልወረራውእንዲቀለበስወሰነ፡፡በዚህምመሠረትውሳኔውንየደገፉአሥራስድስትሀገሮችወታደሮቻቸውንለመላክወሰኑ፡፡ከነዚህአንዷሀገራችንኢትዮጵያነበረች፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቃኘው ሻለቃን ዝግጅት ሲመለከቱ
በነሐሴ 1948 ዓምከዐሥርመድፈኛሻለቆችየተውጣጣአንድሻለቃተመሠረተ፡፡ስሙምቃኘውሻለቃተባለ፡፡በእንግሊዝአሠልጣኞችጥብቅየሆነሥልጠናለስምንትወራትወሰደ፡፡በመጨረሻምንጉሠነገሥትኃይለሥላሴባሉበትየቃኘውሻለቃአባላትአፕሪል 13 ቀን 1951 (እኤአ) ችሎታቸውንበመስክአሳዩ፡፡ንጉሠነገሥቱምእነሆበጋራደኅንነትመርሕመሠረትእጅግቅዱስለሆነውለዓለምሰላምዘብልትቆሙየዓለምንግማሽየሚሆንጉዞትጓዛላችሁ፡፡  ሂዱናወራሪዎችንድልንሱዋቸው፡፡በኮርያልሳነምድርምሕግናሥርዓትንአስከብሩሲሉልባቸውንበወኔሞሉት፡፡ንጉሡይህንንሲሉለአምስትዓመታትበጣልያንወረራተጋድሎየቆየችውኢትዮጵያየነበሯትወታደሮችናመሣሪያዎችራስዋንለመጠበቅእንኳንየሚያስችሉ አልነበሩም፡፡ሀገርንከፈጣሪበታችየሚጠብቃትየሀገርፍቅርያለውሕዝብነውብለውየሚያምትኢትዮጵያውያንግንየወረራንጽዋያውቁታልናበነርሱየደረሰበደቡብኮርያእንዳይደርስሲሉበተመረቁበማግሥቱበጀግንነትዘመቱ፡፡

ቃኘው ሻለቃ ኮርያ፣ ቡሳን የወደብ ከተማ ሲደርስ
1122 የቃኘውሻለቃአባላትበኮሎኔልከበደገብሬመሪነትየመለየትናፍቆት፣የመተማመንምጀግንነትበተሞላውመንፈስከአዲስአበባተሸኝተውበባቡርወደጅቡቲተጓዙ፡፡ከጅቡቲደግሞቡሳንወደተባለችውየኮርያየወደብከተማበመርከብአቀኑ፡፡21 ቀናትበውቅያኖስላይከተንሳፈፉበኋላበሜይ 6 ቀን 1951 እኤአኮርያደረሱ፡፡የደቡብኮርያፕሬዚዳንትሲንግማንምበደስታተቀበሏቸው፡፡ 
 

የኮርያ ፕሬዚዳንት ሲንግ ማን ሲቀበሏቸው - የቃኘው አባላት ከመርከብ ሲወርዱ
 ከጥቂትቀናትበኋላምቶንግናተዛውረውለስድስትሳምንታትያህልከአሜሪካየጦርመሣሪያዎችናከኮሪያመልክዐምድርጋርየሚያስተዋውቅሥልጠናወስደው 85 መኮንኖችና 1037 ወታደሮችጁላይ 11 ቀንበሰባተኛውየአሜሪካዲቪዚዮንሥርተሰለፉ፡፡የቃኘውሻለቃገድልምበሩቅ ምሥራቅተጀመረ፡፡
ይቀጥላል፡፡
ደቡብ ኮርያ  - ሴኦል

ቃኘው ሻለቃ - የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋ ፋና - 2

$
0
0

እስከ 1956 እኤአ በኮርያ ምድር የቆዩት የቃኘው ሻለቃ አባላት ከአፍሪካ የሄዱ ብቸኛ ወታደሮች ነበሩ፡፡ የአፍሪካውያንን ጀግንነት የሚጠራጠሩትና የቀለም በሽታ ያልለቀቃቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ወታደሮች ሊያሳዩዋቸው የሞከሩትን ንቀት በየግንባሩ በጀግንነት ባስመዘገቡት ገድል አፋቸውን አስይዘው የክብር ሰላምታ እንዲያቀርቡላቸው አድርገዋል፡፡ በኮርያ ምድር ከዘመቱ ምድቦች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ብቻ ነበሩ፡፡ 238 ግዳጅ ተሰጥቷቸው ሁሉንም በድል ነበር የደመደሙት፡፡ ከዚህ በፊት ጥቁር ሰው አይተው የማያውቁት የሰሜን ኮርያ ወታደሮች የኢትዮጵያውያንን የድል በትር ሲቀምሱት ‹ልዩ ፍጡራን ናቸው› እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡ እልከኞች ናቸው፡፡ መማረክን አይቀበሉም፡፡ ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው - ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ› እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፡፡ 


ከሁሉ አስደናቂ ሆነው የሚነገሩላቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የቃኘው ሻለቃ አባላት በጦርነት የተሠዉትን አባሎቻቸውን አስከሬን ለጠላት ጥለው አይሮጡም፡፡ ከላይ እንደ ሰዶም እሳት እየዘነበባቸው የጓዶቻቸውን ክቡር አስከሬን ተሸክመው ይወጣሉ፡፡ እንዲያውም አንድ የኢትዮጵያ ወታደር የቆሰለ ኮርያዊ ወታደርን እንደተሸከመ ተመትቶ ተሠውቷል፡፡ ዛሬም ኮርያውያን ለኢትዮጵያውያን ፍቅር እንደ ልዩ መግለጫ ያወሱታል፡፡ ጦርነቱ አብቅቶ የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ ደቡብ ኮርያ 8343፣ አሜሪካ 4714፣ እንግሊዝ 977፣ ቱርክ 244፣ አውስትራልያ 26፣ ካናዳ 33፣ ፈረንሳይ 12፣ ግሪክ 3፣ ኮሎምቢያ 28፣ ታይላንድ 5፣ ኔዘርላንድ 3፣ ቤልጅየም 1፣ ፊሊፒንስ 97፣ ደቡብ አፍሪካ 9፣ ኒውዚላንድ 1፣ ኖርዌይ 3 ምርኮኛ ሲመለስላቸው ኢትዮጵያ ግን አንድም ሰው ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር ነበረች፡፡
የኮርያ ጦርነት እኤአ ጁላይ 27 ቀን 1953 ዓም ጦርነትን በማቆም ስምምነት ተጠናቀቀ፡፡ በቻይናና ሶቪየት ኅብረት በምትረዳው ሰሜን ኮርያና በአሜሪካና በሌሎች 15 ሀገሮች በተደገፈችው ደቡብ ኮርያ መካከል ድንበር ተሠመረ፡፡ ከድንበሩ ወደ ሰሜንና ደቡብ ሁለት ሁለት ኪሎ ሜትር ገብቶ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከወታደር ነጻ የሆነ ቀጣና (Demilitarized Zone – DMZ) ተመሠረተ፡፡ በዚህ ቀጣና ውስጥ የቃኘው ሻለቃ አባላት እልህ አስጨራሽ ውጊያ አድርገውበታል፡፡ የድል ጽዋንም ተጎንጭተውበታል፡፡ ግን ምን ያደርጋል ጦርነት አስቀያሚ ነውና አንድ ሕዝብ ለሁለት ተከፈለ፡፡ ቤተሰቦች በፖለቲካዊ ካርታ ተለያዩ፡፡ ኮርያውያን ይህንን ከወታደር ነጻ የሆነ ቀጣና ሲያዩ ‹ሰላምም፣ ጦርነትም የሌለበት ቦታ› ይሉታል፡፡ ከወታደር ነጻ በሆነው የደቡብ ኮርያ ቀጣና በኩል ሆኖ ሰሜን ኮርያን ማየት ይቻላል፡፡ ቀጣናው ከደቡብ ኮርያ ዋና ከተማ ሴኡል 35 ማይል ርቆ ይገኛል፡፡ 
ያልተዋሐደው የኮርያ ልሳነ ምድር

የኮርያ ጦርነት መጨረሻው አንድን ሕዝብ ለሁለት መክፈል፣ ሁለት ርእዮተ ዓለም ያላቸው ሁለት ሀገሮች መፍጠር፣ በሰሜን ቻይናና ሩሲያ፣ በደቡብ አሜሪካ በተልዕኮ የሚጎነታተሉበት የጦር ሜዳ ማዘጋጀት ሆነ፡፡ በተለይም ደቡብ ኮርያውያን ከሁለት ቦታዎች በስተቀር ሌላው ሀገራቸው በሙሉ ተወርሮ ስለነበር የነበረው እንዳልነበረ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ጦርነቱ ሲጠናቀቅ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ የፈራረሱትን መገንባት፣ የሕዝቡን የቆሰለ ልብ መፈወስ፣ ዳግም ወደ ስቃይ እንዳይገባ መጠበቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ቃኘው ሻለቃ የሚመረጥ አልነበረም፡፡

የቃኘው ሻለቃ አባላት ከሚረዷቸው ልጆች ጋር
ዛሬም ኮርያውያንና የኮርያ መዛግብት የቃኘው ሻለቃ አባላትን በርኅራኄያቸው ያስታውሷቸዋል፡፡ በጦርነት ውስጥ ሆነው እንኳን ከምግባቸው እየቀነሱ የሚመግቧቸው ብዙ የተጎዱ ኮርያውያን ነበሩ፡፡ያሳደጓቸው ሕጻናት ዛሬ ኮርያን እየመሩ ነው፡፡ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን በገንዘባቸው ገንብተዋል፡፡ የጀግንነት ታሪካቸውን ተጠቅመው ሕዝቡ ተስፋ ሳይቆርጥ ኑሮን እንደገና እንዲጀምር አበርትተዋል፡፡ የዛሬዋ ኮርያ ወደ ዕድገቱ ጎዳና እንድትንደረደር መሠረቱ ሲጣል ስሚንቶ አቡክተዋል፣ ውኃ አቀብለዋል፣ እንዳይፈርስም ጠብቀዋል፡፡ 
ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ለቃኘው ሻለቃ ሰማዕታት ሜዳልያ ሲያበረክቱ
ከጦርነቱ በኋላ የቃኘው ሻለቃ አባላት 3 ዓመት ያህል እየተፈራረቁ በኮርያ ምድር በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር ሰላም እያስከበሩ ቆይተዋል፡፡ ከሙቀት ሀገር የመጡ የአፍሪካ ወታደሮች ወራሪውን ብቻ ሳይሆን ብርዱንና በረዶውን አሸንፈው ከብርዱ ሀገር ሰዎች በላይ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ሕጻናት ሰብስበው አሳድገዋል፡፡
የቃኘው ሻለቃ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ የኮርያን ልሳነ ምድር የለቀቁት በመጋቢት ወር 1956 ዓም እኤአ ነው፡፡ 121 ወታደሮች ተሠዉተው፣ 536 ወታደሮች ቆስለው ነበር፡፡ ዛሬ በእርጅናው የሚገኙ የዚያን ዘመን ኮርያውያን የቃኘው ሻለቃ ምድሪቱን ተሰናብቶ ሲወጣ ሕዝቡ በዕንባ እንዴት እንደሸኘው ያስታውሳሉ፡፡ ከዚህ በዕንባ ሲሸኙ ከወዲያ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ‹ጉሮ ወሸባየ› እያሉ ነበር የተቀበሏቸው፡፡ ዝናቸው በምድረ ኢትዮጵያ ናኝቷል፡፡ ገድላቸው የአፍ ማሟሻ ሆኗል፡፡ ከዐሥር ዓመት በኋላ የመጣው ደርግ ለሰሜን ኮርያ አድልቶ ደማቁ ታሪክ እንዲደበዝዝ ያደረገው ቢመስልም እነርሱ ያበሩት መብራት ግን የሚፍግ እሳት፣ የማይጠፋም ፋና ነው፡፡

በኮርያ ምድር ስትዘዋወሩ ልባችሁ ሞቅ ይላል፡፡ እዚህም እዚያም የጀግኖቻችሁን ገድል በመዛግብቱ፣ በሐውልቱ፣ በሙዝየሞቹ አሸብርቆ ታዩታላችሁ፡፡ የሚነገርላቸው ሁሉ ድንቅ፣ መሳጭና እንኳን ልጃቸው ሆንኩ የሚያሰኝ ነው፡፡ ምናልባት ግን እነርሱ የሞቱላት ኮርያ ባለፉት 61 ዓመታት አድጋና ተመንድጋ በብልጽግና ማማ ላይ ስትቀመጥ፣ የእነርሱ ሀገር ኢትዮጵያ ከችግር አለመውጣቷ እነዚያን ጀግኖች ልባቸውን ሳይሰብረው አይቀርም፡፡   

የቹንቾን ሐውልታችን

$
0
0

የቃኘው ሻለቃ መሥዋዕትነት መታሰቢያ ሐውልት

ዛሬ ከሴኡል ከተማ 75 ኪሎ ሜትር ርቀን ቹንቾን(Chuncheon) ወደምትባል የኮርያ ከተማ እንጓዛለን፡፡ በታሪክ ላይ በእግራችን ለመራመድ፡፡ በበረዶ በተሸፈኑት የኮርያ ተራሮች መካከል እያለፍን በኮርያ የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት ጸጥ ባለው ጎዳና ላይ እንበራለን፡፡ ዛፎቹ ቅጠሎቻቸውን ሸኝተው ግንዶች ብቻቸውን የብርዱን ወቅት ሊጋፈጡት ቆርጠዋል፡፡ መሬቱ ነጭ ሥጋጃ ለብሷል፡፡ ደግነቱ ጎዳናው እንደ ካናዳና አሜሪካ በረዶ አልለበሰም፡፡ 


ወደ ቹንቾን ደርሰን ካንግወን (Kangwon)ወደተባለው አደባባይ አመራን፡፡ እዚያ ለኮርያ ነጻነት ሲሉ መሥዋዕትነት ለከፈሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች የቆመ የመታሰቢያ ሐውልት አለ፡፡ ሐውልቱ በማርች 25 ቀን 1968 ተጀምሮ በሜይ 7 ቀን 1968  እኤአ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት (2018) ሃምሳ ዓመት ይሞላዋል፡፡ ሐዉልቱን በሜይ 19 ቀን 1968  ዓም የመረቁት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ ታሪኩን በአማርኛና በኮርያ ቋንቋ የመዘገቡ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች በዙሪያው ይገኛሉ፡፡ ከሐውልቱ አጠገብ ከ49 ዓመት በፊት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተከሏት ዛፍ የሐውልቱን ቁመት በሚፎካከር ቁመት አድጋለች፡፡
ሐውልቱን ጎብኝታችሁ መንገዱን ስትሻገሩ በሚያዝያ 1999 ዓም ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች መታሰቢያ የተገነባው ‹የጦርነት መታሰቢያ ሙዝየም› ይገኛል፡፡ ሙዝየሙ አዲስ አበባና ቹንቾን እኅትማማች ከተሞች ሆነው የተፈራረሙበትን የ1996 ዓም ስምምነት ተከትሎ የተገነባ ነው፡፡ በሙዝየሙ ውስጥ በኮርያ ጦርነት የተሳተፉ የቃኘው ሻለቃ አባላትን ገድል የሚዘክሩ ፎቶዎችና ወታደራዊ ቁሳቁሶች ሞልተዋል፡፡
ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የተከሏት ዛፍ
ከሙዝየሙ አጠገብ በ1968 እኤአ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐዉልቱን ሲመርቁት አብሮ የተከፈተ ‹የኢትዮጵያ ቤት› የተሰኘ ካፍቴሪያ ይገኛል፡፡ ይህንን ቤት የመረቁት ንጉሠ ነገሥቱ መሆናቸውን በቤቱ ውስጥ የሚገኙት ፎቶዎችና መዛግብት ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ባሕላዊ ዕቃዎች የተጌጠው ይህ ቤት የኢትዮጵያን ቡና አፍልቶ በመሸጥ ይታወቃል፡፡ ያውም ከነጀበናና ረከቦቱ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የነበራቸውን ተጋድሎ፣ ያደረጉትን አስተዋጽዖና የንጉሠ ነገሥቱን ጉብኝት የሚያሳዩ ፎቶዎች ግድግዳውን ሞልተውታል፡፡ 

 
ሙዝየሙ ከውጭ ሲታይ
የቃኘው ሻለቃ ጀግኖች በኮርያ ጦርነት ተሳትፈው አኩሪ ገድል ለመፈጸም የኮርያን ምድር የረገጡት ሜይ 6 ቀን 1951 እኤአ ነው፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ እኤአ በ2021 ዓም 70 ዓመት ይሆናቸዋል፡፡ በኮርያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት ከሚገኙ የኮርያ ዘማቾች ጋር በመሆን አንድ ዐቢይ ኮሚቴ አቋቁመው ሰባኛውን ዓመት በሁለቱም ሀገሮች ለማክበርና አሁን ላለው ትውልድ የታሪክ ውርርስ ለማድረግ ቢነሣሡ ጊዜውን በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም የሚቻል ይመስለኛል፡፡      
የኢትዮጵያ ቤት ባለቤት ቡና ሲያፈላ

Viewing all 266 articles
Browse latest View live


<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>